የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እንዲሁም የክልልና የከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች በተለያዩ ህጎች በተሰጣቸው ሀላፊነት መነሻነት የፌዴራል መንግስት ለክልሎች የሚሰጠውን የድጋፍና ድጎማ በጀት ኦዲት ለማድረግ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሚፈጠርን የኦዲት ድግግሞሽ ለማስቀረት በወጣው የነጠላ ኦዲት አዋጅ ቁጥር 1251/2013 አፈጻጸም ላይ መስከረም 29/2014 ዓ.ም በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ውይይት ተደረገ፡፡ በመድረኩ አዋጁን ለማስፈጸም የሚረዳ የአፈጻጸም ረቂቅ መመሪያ የሚያዘጋጅ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እንዲሁም የክልልና የከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች በተካፈሉበት በዚህ የውይይት መድረክ መክፈቻ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በነሀሴ ወር 2013 ዓ.ም የፌዴራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተሮች በሀዋሳ ከተማ አካሂደውት በነበረው መድረክ ላይ በአዋጁ ላይ መወያየት ያስፈልጋል በሚል ቀርቦ በነበረው አስተያየት መሰረት ውይይቱን ለማድረግና የአዋጁ አፈጻጸም መመሪያ የሚወጣበትን ሁኔታ ለማመቻቸት መድረኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ለውይይት መነሻ እንዲሆን በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በአዋጁ ላይ ገለጻ የተደረገ ሲሆን ተሳታፊዎችም በአዋጁ ድንጋጌዎችና በአዋጁ አፈጻጸም ላይ ያሏቸውን አስተያየቶችና ጥያቄዎች አቅርበው ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱ መጨረሻ ላይ በመድረኩ የተነሱ ሀሳቦችን ባገናዘበ መልኩ የአዋጁ ማስፈጸሚያ መመሪያ እንዲዘጋጅ ከስምምነት ላይ የተደረሰ ሲሆን በፌዴራል ዋና ኦዲተር አስተባባሪነት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤት እንዲሁም የኦሮሚያና የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች አባል የሆኑነት የአፈጻጸም መመሪያ አዘጋጅ ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች ከውይይቱ አስቀድሞ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ውስጥ የተቋቋሙትን ዘመናዊ የመረጃ ማዕከል፣ የስልጠና ማዕከል፣ የህጻናት ማቆያን እና የስፖርት ማዘውተሪያ ጂምናዚየምን ጎብኝተዋል፡፡