የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ትምህረት ጽ/ቤት የተለያዩ መፅሐፍትን እና ቦርሳዎችን የወረዳው ስራ አመራር ኃላፊዎች በተገኙበትና ቦርሳዎቹን እንዲወስዱ የተመረጡ ተማሪዎች ባሉበት የካቲት 17 ቀን 2008 ዓ.ም አስረከበ፡፡
በርክክቡ ስነሥርዓት የዋና ኦዲተር መ/ቤት የውጭና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አወቀ ጤናው መፅሐፍቱንና ቦርሳዎቹን ባስረከቡበት ወቅት መ/ቤቱ በአዋጅ ከተሠጠው ሥልጣንና ሓላፊነት በተጨማሪ መህበራዊ ግዴታውን መወጣት እንደሚያስፈልግ በመግለፅ በተቋሙ ቤተ መፀሐፍት ተመሳሳይ ኮፒ ከሆኑት ውሰጥ 287 መፅሐፍትን እንዲሁም 169 ቦርሳዎቸን በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ትምህረት ጽ/ቤት በስጦታ ለመስጠት እንደወሰነ አስረድተዋል፡፡
የወረዳው ፋይናንስና ኢኮኖሚክስ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሁሴን ጀማል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለወረዳው መፅሐፍቱንና ቦርሳዎቹን በስጦታ ማበርከቱን አመስግነው ተቋሙ መህበራዊ ግዴታውን ለመወጣት እያደረገ ያለውን ድጋፍ በማድነቅ በቀጣይም መሰል ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
ዋና ኦዲተር መ/ቤት ያደረገልን ስጦታ ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን የገለፁት በወረዳው የሥርዓተ ፆታና ባለዘርፈ ብዙ ባለሙያ አቶ ሻንበል አበራ በዕለቱ ከጥቁር አንበሳ ት/ቤት ለመጡ መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች ቦርሳዎቹን አድለዋል፡፡ መፅሐፍቱም በወረዳው ለሚገኙ የተለያዩ የህዝብ ቤተመፅሐፍት እንደሚተላለፍ ገልፀዋል፡፡
በዕለቱ የተገኙ ተማሪዎችም ስማቸው እየተጠራ ቦርሳዎቹ የተሰጣቸው ሲሆን ተማሪዎቹም በተደረገላቸው ድጋፍ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡