News

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ሰራተኞች የግንቦት 20፤ 25ኛ ዓመት የድል በአልን አከበሩ

ተቋሙ ለመልካም አስተዳደርና ለዴሞክራሲ ስርአት መጠናከር የነበረውን አስተዋጽዖ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ባለፉት 25 አመታት በሀገሪቱ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲሰፍን ሲያበረክት የነበረውን አስተዋጽዖ ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች 25ኛውን የግንቦት ሀያ የብር እዮቤልዩ የድል በአል ባከበሩበት ወቅት ገለጹ፡፡
የተቋሙ ሰራኞተኞችና አመራሮች በአሉን ግንቦት 22 ቀን 2008 ዓ.ም “በብዝሀነት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለህዳሴያችን!” በሚል መሪ ቃል በተቋሙ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ባከበሩበት ወቅት ክቡር አቶ ገመቹ በሀገሪቱ ህግ አውጪ አካል የወጡ ህጎች በአግባቡ መተግበራቸውን እንዲሁም የመንግስት ሀብት በተገቢው ሁኔታ ስራ ላይ መዋሉን በመቆጣጠር በኩል ባለፉት 25 አመታት የፌደራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ያከናወናቸው ተግባራት በሀገሪቱ የመልካም አስተዳደርና የተጠያቂነት ስርዓት እንዲሰፍን ቁልፍ ሚና መጫወቱን አመልክተዋል፡፡
ክቡር አቶ ገመቹ ሀገሪቱ በቀጣይ ያቀደቻቸው የልማት፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና የህዳሴ ጉዞ እንዲሳካ የመንግስት ተቋማት አፈጻጸምና የሀብት አጠቃቀም አግባብነት አሁን ካለበት ደረጃ እንዲልቅ የኦዲት አሰራርን በበለጠ ጥልቀት የማከናወን አስፈላጊነት ላይ የተቋሙ ሰራተኞችና አመራሮች ልዩ ትኩረት በመስጠት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ አያይዘውም መንግስት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ለመልካም አስተዳደርና ለዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ያለውን ወሳኝ ሚና በመረዳት ለተቋሙ ስራ ልዩ ትኩረት እንደሰጠ ገልጸዋል፡፡
በበአሉ አከባበር ላይ ከደርግ ስርዓት ውድቀት ማግስት ጀምሮ ባለፉት 25 አመታት የተመዘገቡ ስኬቶችን፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንና በሀገሪቱ የልማትና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ሂደት ውስጥ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት ያበረከተውን አስተዋጽኦ የተመለከተ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ቀርቧል፡፡ የጽሁፉ አቅራቢ የሆኑት የተቋሙ የውጭና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አወቀ ጤናው ባለፉት 25 አመታት ኢትዮጵያ በተከተለችው የልማትና የዴሞክራሲ አቅጣጫ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ልማት እንዲሁም በመልካም አስተዳደርና በዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ፣ በብሄራዊ የጋራ መግባባት፣ በሀገራዊ ገጽታ ግንባታና በዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ሁለንተናዊ እድገት እንደተመዘገበ ገልጸዋል፡፡
አቶ አወቀ ባለፉት አመታት ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች የሀገሪቱ ተግዳሮት በመሆን እንደታዩ ገልጸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት እነዚህን ችግሮች በማስወገድ ረገድ የራሱን ከፍተኛ ሚና መጫወት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በማያያዝም ባለፉት 25 አመታት ውስጥ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት መልካም አስተዳደርን በማስፈንና የመንግስት ማስፈጸም አቅምን በማሳደግ እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችንና ኪራይ ሰብሳቢነትን በመታገል ጉልህ ሚና እንደተጫወተ አስረድተዋል፡፡ በነዚህ አመታት ውስጥ ተቋሙ የፋይናንሻል ኦዲትን 100 በመቶ፣ የክዋኔ ኦዲት ደግሞ በአማካኝ በየዓመቱ 18 መድረሱን እንዲሁም ለመሰረታዊ አገልግሎቶች በሚሰጠው ድጋፍ በየአመቱ እየደገ መምጣቱንና በዚህም በክልሎች እስከ 300 ሪፖርቶች ማውጣት መቻሉን ካስመዘገባቸው ስኬቶች ውስጥ እንደሚካተቱ የውጭና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
በቀረበው የመነሻ ፅሑፍ ላይ ሰራተኞችም ውይይት ያደረጉ ሲሆን ምላሽ በሚፈለጉ ሃሳቦች ላይ ዋና ኦዲተሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በእለቱ ለዚህ ድል ላበቁን የትግሉ ሰማዕታት የህሊና ጸሎት የተደረገ ሲሆን የሻማ ማብራትና የዳቦ ቆረሳ ስነ-ሥርዓትም ተካሂዷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *