የፅዳት ሠራተኞች ለተቋሙ ራዕይ ስኬት ይበልጥ መስራት እንዳለባቸው ተገለጸ
- ለተቋሙ የጽዳት ሰራተኞች ስልጠና ተሰጠ
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የጽዳት ሰራተኞች ለተቋሙ ራዕይ ስኬት እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡
የመ/ቤቱ የሴቶችና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት ሀምሌ 28 ቀን 2008 ዓ.ም ለተቋሙ አዲስና ነባር የፅዳት ባለሙያዎች የፅዳት ሥራና የሙያ ደህንነትን አስመልክቶ ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መክፈቻ ላይ የተቋሙ የውጭና የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተርና የስልጠናና ትምህርት ጊዜያዊ ዳይሬክተር አቶ አወቀ ጤናው የፅዳት ሠራተኞች ተቋሙ እ.ኤ.አ. በ2017 በአፍሪካ ካሉ አምስት ምርጥ የኦዲት መ/ቤቶች አንዱ ለመሆን የያዘው ራዕይ አካል መሆናቸውን ተረድተው ለስኬቱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
በወቅቱ የመ/ቤቱ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሙሉ ጥሩነህ የፅዳት ሰራተኞች የሰራተኛውንና የስራ አካባቢውን ደህንት የማስጠበቅ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልጸው ከዚህ አንጻር ደህንነታቸው ተጠብቆ የስራ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ፣ ስራቸውን በቀላሉ እንዲያከናውኑ፣ ከዘመናዊ የፅዳት መሳሪያዎች ጋር እንዲተዋወቁና ብሎም የቡድን የስራ ባህልና መልካም የስራ ግንኙነትን እንዲያዳብሩ ስልጠናው መዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡
በተቋሙ የስራ አካባቢ ደህንንት ጤንነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ታመነ ጌታሁን በጤናና በንፅህና ምንነት፣ የንፅህና መጓደል በሰራተኛው ጤና ላይ በሚያስከትለው ችግር፣ ደህንነቱ ያልተረጋገጠ የፅዳት ስራ በራሳቸው በፅዳት ሰራተኞች ጤንነት ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳትና መወሰድ ስለሚገባው ጥንቃቄ እንዲሁም የፅዳት መጓደል ስለሚያመጡ ምክንያቶችና በተሻለ መንገድ የእጅ ንፅህናን መጠበቅ በሚያስችል የእጅ አስተጣጠብ ዘዴ ላይ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡
በተቋሙ ከፍተኛ ኦዲተር የሆኑት ወ/ሮ ሮማን ተሰማ በበኩላቸው የፅዳት ስራዎች ሊሰሩበት ስለሚገባው ሙያዊ አግባብ፣ በተለምዶ አገልጋሎት ላይ እየዋሉ ስለሚገኙት እንዲሁም ስለዘመናዊ የፅዳት ግብአቶችና ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀም በተግባር የተደገፈ ገለጻ አድርገዋል፡፡
የተቋሙ የፅዳት ሰራተኞች በስልጠናው ጥሩ ግንዛቤ መጨበጣቸውን፣ በሥራቸው ላይ እያጋጠሙዋቸው ስላሉ የግብአት ችግሮችና በቀጣይ የፅዳት ስራውን ይበልጥ ሊያሻሽሉ ስለሚችሉ ጉዳዮች አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን የተነሱትንም ሃሳቦች ለሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች በማሳወቅ ምላሽ ለማሰጠት እንደሚሰሩ የስልጠናው አስተባባሪዎች ገልጸዋል፡፡ በቀጣይም መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እንደሚካሂዱ ወ/ሮ ሙሉ አሳውቀዋል ፡፡
የመድረኩ አስተባባሪዎችና ተሳታፊዎች ስልጠናው እንዲካሄድ በማነሳሳት እንዲሁም በፅዳት ሥራ ላይ በተለያየ አገጣሚ በህይወት ተሞክሯቸው ያካበቱትን እውቀትና ልምድ ለተቋሙ ሠራተኞች በማካፈል ላደረጉት ልዩ ጥረትና አስተዋጽኦ ለወ/ሮ ሮማን ተሰማ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡