News

የውጤት ተኮር ስርዓት (BSC) ስልጠና ተሰጠ

የውጤት ተኮር ስርዓት ስልጠና ተሰጠ

በለውጥ ስራ አመራር ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀና በውጤት ተኮር ስርዓት (BSC) ላይ ያተኮረ ስልጠና በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተለያዩ የስራ ክፍሎች ውስጥ ለሚሰሩ የስራ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች ከታህሳስ 13-14/2009 ዓ.ም ተሰጠ፡፡

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የክቡር ዋና ኦዲተሩ ልዩ ረዳት አቶ ሻሾ መኮንን በተቋሙ ስትራቴጂክ እቅድ የተቀመጡ ስራዎች ለእያንዳንዱ ፈጻሚ ወደታች ወርደው በBSC እየተለኩ ባለመሆኑ እንዲሁም በውጤት ተኮር ስርዓት ላይ ተመጣጣኝ ግንዛቤ በሁሉም የስራ ክፍሎች ኃላፊዎችና ሰራተኞች ዘንድ ባለመኖሩ ስልጠናው መዘጋጀቱ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አቶ ሻሾ አያይዘውም ሰልጣኞች ስለውጤት ተኮር ስርዓት በቂ ግንዛቤ ጨብጠው ስርዓቱን ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡

ስልጠናውን የሰጡት የለውጥ ስራ አመራር ዳይሬክተር አቶ አበራ ተፈራ በተቋሙ የውጤት ተኮር ስርዓት መጠናቱንና ወደ ሁሉም የስራ ክፍልና ባለሙያ ባይወርድም በአንዳንድ የስራ ክፍሎች እስከ ከፍተኛ ባለሙያ ድረስ የBSC ስልጠና መሰጠቱን አስታውሰው ስልጠናውን ያልወሰዱት ሌሎች የስራ ክፍሎች በBSC ምንነት፣ ጠቀሜታ፣ የጥናት ሂደት፣ አተገባበርና ውጤት ላይ ግንዛቤና ክህሎታቸውን በማሳደግ ስርዐቱን በአስተማማኝነት ለመዘርጋት ስልጠናው መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

ውጤት ተኮር ስርዓት ስትራቴጂክ የስራ አመራር፣ የአፈጻጸም ምዘናና የስርዐተ ተግባቦት መሳርያ ሆኖ እንደሚያገለግል የገለጹት አቶ አበራ በምንነቱ፣አስፈላጊነቱ፣ በታሪካዊ አመጣጡና እድገቱ፣ በግንባታና ትግበራ ደረጃዎቹ እንዲሁም ስርአቱን ከማሳካትና ቀጣይነቱን ከማረጋገጥ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡ አቶ አበራ የተቋሙን የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ በማቅረብም የስራ ክፍሎች እንደየስራ ድርሻቸው ተቋማዊ ስትራቴጂያዊ ግቦችን እየወሰዱ የክፍላቸውንና የባለሙያዎቻቸውን የBSC ስኮር ካርድ (እቅድ) እንዴት እንደሚያዘጋጁ አስተምረዋል፡፡

በስልጠናው መዝጊያ ላይ አቶ ሻሾ በቀጣይ በመ/ቤቱ ውስጥ የሚከናወኑ ስራዎች በውጤት ተኮር ስርዓት እንደሚመዘኑ ገልጸው ስልጠናውን የወሰዱ የስራ ክፍሎች የተቋሙን የBSC ጥናትና የሲቪል ሰርቪስ የሰራተኞች አፈጻጸም ምዘና መመሪያን መሰረት አድርገው የዳይሬክቶሬት እና የግለሰብ የBSC እቅድ አዘጋጅተው በማጸደቅ  በፍጥነት ወደ ስራ መግባት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በስልጠናው ላይ የዕቅድ ዝግጅትና ግምገማ ዳይሬክቶሬት፣ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት፣ የኦዲት ጥራት ዳይሬክቶሬት፣ የህግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት፣ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት፣ የኢንፎርሜሽን ሲስተም ሰርቪስ ዳይሬክቶሬት የውስጥ ኦዲት ዳይረክቶሬት እና የውጭና ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ተካፍለዋል፡፡

_dsc0022

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *