የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስትወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በኢንዱስተሪ ሚኒስቴር የ2006 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ሪፖርት፣ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ ምርቶች የወጭ ንግድ አፈጻጸም በተመለከተ የክዋኔ ኦዲት ፣የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቲዩት የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋትና አቅም ለመገንባት የሚሰጠውን ድጋፍና ክትትል በተመለከተ የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ታህሳስ 24 ቀን 2008 ዓ.ም ይፋዊ ስብሰባ (PUBLIC HEARING) አካሄደ፡፡ በይፋዊ ስብሰባው ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እና ኦዲቱን ያከናወኑ የኦዲት ዳይሬክተሮች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ከኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ተገኝተዋል፡፡
የኦዲቱ ውጤቱ በርካታ የኦዲት ግኝቶችን ያመላከተ ቢሆንም በቋሚ ኮሚቴው ለውይይት በተመረጡ ዋና ዋና ጥያቄዎች ላይ ይፋዊ ስብሰባው ትኩረት አድርጎ ተወያይቷል፡፡
1. የኢንዱስተሪ ሚኒስቴር
• ከደንብና መመሪያ ውጭ የተከፈለ 424441.79 ብር አላግባብ ወጪ ሆኖ ተከፍሏል፣
• ለኤም ኤች ኢንጂነሪንግ አማካሪ ኩባንያ ብር 1413949.96 ከውል በላይ እና 114619.06 ከውል ውጭ ክፍያ መፈጸሙ ፣
• ብር 742051501.66 የምክር አገልግሎትና የግንባታ ግዥ ያለጨረታ መፈጸሙ፣
• ለረዥም ዓመታት ተበላሽተው የቆሙ 7 መኪኖች እና 85 የተለያዬ መጠን ያላቸው ጎማዎች መኖር፣
2. በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንዱስትሪ ምርቶች የውጭ ንግድ አፈጻጸም በተመለከተ የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት
• ከባለድሻ አካላት ጋር ያለው ቅንጅታዊ አሰራር የሌለው መሆኑ፣
• የወጭ ምርት ንግድ እቅድ አፈጻጸም በሚ/ር መ/ቤቱ በ2005 እና በ2006 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ሪፖርት ጋር ልዩነት ያለው መሆኑ፣
• በዘርፉ የተሰማሩ ባለሃብቶችን ለማበረታታት ጥሬ ዕቃን ወደ አገር በሚያስገቡበት ወቅት የቀረጥ ተመላሽ በወቅቱ ለተጠቃሚዎች አለመመለስ፣
• የውጭ ዜግነት ላላቸው ባለሃብቶች የቀረጥ ነጻ ማበረታቻ አዋጅ ቁጥር 768/2004 ባልተከተለ መልኩ ከቀረጥ ነጻ ሁሉም ግባቶችና ጥሬ እቃዎችን እንዲያስገቡ ማድረጉና ምርቱን ኤክስፖርት ማድረግ ሲገባቸው ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ገበያ እያከፋፈሉ መሆኑ፣
• የኢንዱስትሪዎችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ስልጠና የማይሰጥ እና የሚሰጡ ስልጠናዎችም ቢሆኑ ያመጡት ፋይዳ የማይገመገም መሆኑ፣
3. የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲቲዩት የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎችን ለማስፋፋትና አቅም ለመገንባት የሚሰጠውን ድጋፍና ክትትል በተመለከተ የተከናወነ የክዋኔ ኦዲት
• ኢንስቲቲዩቱ ወቅታዊ መረጃ አለመያዙና ለህብረተሰቡ አለማስተዋወቅ፣
• በዘርፉ ወደ ኢንቨስትመንት ለሚገቡ ባለሃብቶች የመሬትና የመሰረተ ልማት አገልግሎቶች እንዲያገኙ የትብብር ደብዳቤ ቢጽፍም ድጋፍ ስለማግኘታቸው ክትትል የማያደርግ መሆኑ፣
• ኢንዱስትሪዎች ለሚያመርቷቸው ምርቶች የገበያ ትስስር አለመፈጠሩ፣
• በኢንስቲቲዩቱ እቅድ መሰረት ያዋጭነት ጥናት የማይካሄድ መሆኑ፣
• ኢንስቲቲዩቱ የውዳቂ ብረታ ብረት ክምችትና ግብይት ስርዓት የሚይዝበትን ሁኔታ በማጥናትና በማስፈቀድ ተግባራዊነቱን ያልተከታተለና ተግባራዊ ያላደረገ መሆን በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡
ለተነሱት ጥያቄዎች የመስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች በሰጡት ማብራሪያ በኦዲት ግኝቱ መሰረት በወቅቱ የመውጫ ስብሰባ አልተደረገም በሚል ምክንያት የኦዲት ግኝቶችን ለማስተካከል የወሰዱት እርምጃ አለመኖሩን ገልጸዋል፡፡ በኦዲት ወቅት ያላቀረቧቸው ማስረጃዎች እንደነበሯቸው ነገር ግን እነዚህን ማስረጃዎች ዘግይተው ማቅረባቸውን አስረድተው በአብዛኛው የኦዲት ግኝቶች የመ/ቤቱን ስራ ለማቀላጠፍ በሚል እሳቤ የተሰሩ እንጅ ህግን በመተላለፍ አይደለም በማለት የቀረቡትን ጥያቄዎች ለበቀበል እንቸገራለን በሚል ተከራክረዋል፡፡ ኃላፊዎች አክለውም አላግባብ የተከፈሉ ክፈያዎችን አለማስመለሳቸውን እና በቀጣይም ለማስመለስ እንደሚቸገሩ አብራርተዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የኦዲቱ ዋነኛ ዓላማ ለመደጋገፍ እና ስህተቶችን ለማረም ነው፡፡ ነገር ግን በሰጣችሁት መልስ ኦዲቱን ተቀብሎ ለማስተካከል ያደረጋችሁት ጥረት አለመኖሩን መረዳት ይቻቻላል፡፡ ኦዲት ተደራጊ ተቋማት በህግ በተቀመጠው አግባብ በወቅቱ ሂሳባቸውን ዘግተው ለኦዲት ማቅረብ ያለባቸው ቢሆንም ይህንን ማድረግ አልቻላችሁም፡፡ ስለሆነም ይህን ባለማድረጋችሁ ኦዲቱ እንዲዘገይ ምክንያት ሆናችኋል፡፡ ሒሳብ በወቅቱ አለመዝጋት በህግ እንደሚያስጠይቅ መገንዘብ ይኖርባቸኋል፡፡ ሂሳቡ ተዘግቶ ኦዲት ከተደረገ በኋላም የመውጫ ስብሰባ እንድናደርግ ባስቀመጥነው የአስራ አምስት ቀን ገደብ ተግባራዊ ማድረግ ባለመቻላችሁ እና ሪፖርቱ ለፓርላማው የሚቀርብበት ጊዜ በመሆኑ በእናንተ መ/ቤት ችግር ምክንያት አጠቃላይ ሪፖርቱን ማዘግየት ተገቢ ባለመሆኑ ሪፖርቱን አካትተን መስራታችን ትክከል ነበር ብለዋል፡፡ ከደንብና መመሪያ ውጭ የተከፈሉ ክፍያዎች መመለስ አለባቸው ያሉት ዋና ኦዲተር የኦዲት ግኝቱን መሰረት ያደረገ የድርጊት መርሃ ግብር ተዘጋጅቶ እርምጃ በመውድ ሪፖርት መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙን ከደንብና መመሪያ ውጪ የተከፈሉ ክፍያዎች በኦዲቱ አስተያየት መሰረት ተመላሽ አንዲደረጉ ትኩረት ሰጥቶ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የውስጥ ኦዲተሮችን አቅም በማጠናከር ችግሮች እንይከሰቱ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ማድረግ እንዳለባቸው በጥብቅ አሳስበዋል፡፡ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት በኦዲቱ መሰረት የተቀመጡ አስተያየቶች ላይ እርምጃ መወሰድ አስፈላጊ መሆኑን እና የተሰጡ ማበረታቻዎች ለታለመላቸው ዓላማ መዋላቸውን ማረጋገጥ ለዚህም የተጠናከረ የቁጥጥርና ክትትል ስራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡