News

የኢፌዴሪ ህዝብ ተወዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የ2006 በጀት ዓመት ሂሳብ ኦዲት ላይ የጂግጂጋ እና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎች በወሰዷቸው የማስተካከያ እርምጃዎች ላይ ይፋዊ ስብሰባ (PUBLIC HEARING) አካሄደ፡፡

በይፋዊ ስብባው ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እና ኦዲቱን ያከናወኑ ዳይሬክተሮች፣ ከከፍተኛ ትምህርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር፣ ከትምህርት ሚኒስቴር እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
በኦዲቱ አስተያየት መሰረት ምን የማስተካከያ እርምጃ ተወሰደ በማለት ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው ቋሚ ኮሚቴው ለዩኒቭርሲቲዎች የስራ ኃላፊዎች ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡
የጂግጂጋ ዩኒቨርስቲ
• ከተለያዩ የገቢ ምንጮች የተገኘውን ገቢ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ማሳወቅ ሲገባ ወደ ውስጥ ገቢ አካውንት ገቢ በማድረግ ሳይፈቀድ ጥቅም ላይ መዋሉ፣
• የጨረታ ኮሚቴ የመረጣቸው አሸናፊ የተጨማሪ አሴት ታክስ ተመዝጋቢ ሆነው እያለ ግዥው ሲፈጸም ከተጨማሪ አሴት ታክስ ደረሰኝ ውጭ ተራ ፋክቱር መቅረቡ እና ይህም የመንግስትን ጥቅም ያሳጣ መሆኑ፣
• ከመመሪያ ውጪ ለደመወዝ፣ ለውሎ አበል፣ ለትርፍ ሰዓት ክፍያ እና ለግዥ ክፍያ ተፈጽሞ መገኘቱ፣
• ያልተወራረደ ተሰብሳቢ እና ተከፋይ ሂሳብ መኖር፣
• በንብረት አያያዝ እና አጠባበቅ መመሪያ መሰረት ንብረቶች በአግባቡ አለመያዛቸው፣
ድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ
• ከአንድ አቅራቢግዥ ያለ ውድድር መፈጸሙ እና ይህም ግዥ አስቀድሞ በጨረታ ተወዳድሮ ግዥው ውድቅ ከተደረገበት አቅራቢ መፈጸሙ፣ በተመሳሳይም የሆቴል መስተንግዶ አገልግሎት ከአንድ አቅራቢ የሚፈጸም መሆኑ፣
• በተለያዩ የኦዲት ጊዜያት አስተያየት የተሰጠበት ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ወቅቱን ጠብቆ ያልተወራረደ ተሰብሳቢ ሂሳብ መኖሩ፣
• ከአንድ ዓመት በላይ የቆየ ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን መ/ቤት መከፈል የነበረበት ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱ፣
• የበጀት ዝውውር ሳይፈቀድ ከተደለደለው መደበኛ በጀት ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ከበጀት በላይ መጠቀም እንዲሁም ለካፒታል ወጪ ከተመደበው በጀት ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ስራ ላይ ያልዋለ በጀት መገኘቱ፣
• ቋሚ ንብረቶች ቁጥር ያልተሰጣቸው መሆን ፣ ቋሚና አላቂ እቃዎች ቢን ካርድ የተዘጋጀ ቢሆንም ምዝገባው ያልተከናወነ መሆኑ፣
• የመንግስትን መመሪያና ደንብ ያልጠበቀ ግዥ መፈጸም፣
• ለትምህርት ክፍያ በተማሪዎች ወደ ባንክ ለሚገቡ ገንዘቦች ደረሰኝ ወደ ፋይናንስ ክፍል እንዲመጣ አለመደረጉ እና ከባንክ የሚመጣው የባንክ እስቴትመንት ላይ በሚታየው ድምር መሰረት የገቢ ደረሰኝ ባለመቆረጡ ብዙ ግድፈቶች የታዩ በመሆናቸው የሂሳቡን ትክክለኛነት ማረጋገጥ አለመቻሉ የሚሉ ናቸው፡፡
የዩኒቨርስቲው የስራ ኃላፊዎች በተነሱት ጥያቄዎች ላይ የወሰዷቸውን የማስተካከያ እርምጃዎች አብራርተዋል፡፡
የጂግጂጋ ዩኒቨርስቲ ፕረዚዳንት ዶ/ር አብድርናስር አህመድ እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች በሰጡት ማብራሪያ የውስጥ ቁጥጥር ችግር የውስጥ ኦዲት የሰው ኃይል እጥረት እና የአቅም ችግር በመኖሩ የተከሰተ ችግር መሆኑ፣ አላግባብ የተከፈሉ ክፍያዎች ደግሞ የስራ ጫና ላለባቸው የአስተዳደር ሰራተኞች በመሆናቸው የሰራተኛ ፍልሰትን ለመከላል የተፈጸመ መሆኑን በአሁኑ ጊዜ ማስቆማቸውን ነገር ግን የተከፈለውን ወደኋላ ሂዶ ማስመለስ መቸገራቸውን አብራርተዋል፡፡ የንብረት አያያዝ ስርዓት በተሻለ ሁኔታ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ፕረዚዳንት ዶ/ር ግርማ ጎሮ እና የስራ ባልደረቦቻቸው በሰጡት ምላሽ የሆቴል አገልግሎት ግዥን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲኖር በዙር ሆቴሎችን እንደሚጠቀሙ፣ ከአንድ አቅራቢ የተፈጸመው ግዥ በጨረታ ለመግዛት የታሰበው ግዥ በጥራት ምክንያት ውድቅ በመደረጉ እና ተማሪዎችን ተቀብለው ስለነበረ በመቸገራቸው የተፈጸመ መሆኑን፣ የበረሃ አበል ክፍያ መመሪያው ሳይጸድቅ በቦርድ አስወስነው መፈጸማቸውን ፣ ያልተጠቀሙበት ያካፒታል በጀት በአማካሪ ድርጅቱ መዘግየት የተፈጠረ መሆኑን፣ የንብረት ቆጠራ ስራ የተጀመረ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ዩኒቨርስቲዎች ማስተካከል አለባቸው ያሏቸውን ጉዳዮች አንስተዋል፡፡ በዚህም መሰረት የጂግጂጋ ዩኒቨርስቲ ላይ የተነሳው ገቢን እና ወጪን አጣፍቶ የተጣራውን ብቻ ሪፖርት ማድረግ መንግሰት ምን ያህል ገንዘብ እንደሰበሰበ እና ወጪ እንደደረገ በግልጽ የማያሳይ አሰራር ሰለሆነ ሪፖርቱ ውስጥ ገቢ እና ወጪው ተካትቶ ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መቅረብ ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ግዥ ሲፈጸም ህጋዊ ያልሆነ ደረሰኝ መቀበል የመንግስትን ገቢ የሚደብቅ በመሆኑ ለዚህ ህገ ወጥ ተግባር ተባባሪ እንዳንሆን ያስፈልጋል በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡አላግባብ የተከፈሉ ክፍያዎች በኦዲቱ አስተያየት መሰረት መመለሳቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ያሉት ዋና ኦዲተር ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ገቢ ያልተደረገው የተሰበሰበ ተጨማሪ እሴት ታክስ ትክክል አይደለም፣ ገቢ መደረግ አለበት እናንተ የመንግስትን ገቢ በወቅቱ በመፈጸም ለሌሎች ምሳሌ መሆን ነበረባችሁ በማለት አሳስበዋል፡፡
ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ በድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ላይ የተስተዋለው ከአንድ አቅራቢ የተፈጸመ ግዥ ትክክል አለመሆኑን ገልጸው ለዚህም ምክንቱ በእቅድ አለመመራት በመሆኑ ወደፊት መስተካከል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው ከሚመለከተው አካል ከመፈቀዱ በፊት የከፈለው የበረሃ አበል በፍጹም ስህተት በመሆኑ እንዲመለስ እና ይህንን ስህተት የሰራ አካልም ተጠያቂ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡
የተከበሩ ወ/ሮ አልማዝ መሰለ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በበኩላቸው በተሰጠው የኦዲት አስተያየት መሰረት ዩኒቨርሲቲዎች የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ የተጀመረው ጥረት ጥሩ መሆኑን ገልጸው የተሟላ የድርጊት መርሃ ግብር ማዘጋጀትና በመርሃ ግብሩ አግባብ ክትትል በማድረግ ማስተካከል ትኩርት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ዩኒቨርሲቲዎች ተቸግረናል በማለት ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት እገዛውን ማጠናከር አለበት ያሉት የተከበሩ ወ/ሮ አልማዝ አብዛኛው የተመለከትነው ችግር ደንብና መመሪያን አክብሮ የመስራት ችግር በመሆኑ ደንብና መመሪያ ሊከበር ይገባል፣ ስለሆነም አላግብብ የተፈጸሙ ክፍያዎች ተመላሽ መደረግ አለባቸው፤ ለመንግስት መግባት ያለባቸው ገቢዎች ፈጥነው ገቢ መደረግ አለባቸው፤ ችግሩን የፈጠሩ አካላትም ተጠያቂ መደረግ አለባቸው በማለት አስጠንቅቀዋል፡፡የንብረት አያያዝና አወጋገድ ደንብና መመሪያ ተጠብቆ መፈጸም ገልጸው ለዚህም ይረዳ ዘንድ የውስጥ ኦዲተሮችን አቅም በመገንባት ሁለገብ አጋዥ ኃይል እንዲሆኑ ማድረግ ይኖርባችኋል በማለት አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *