News

የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ያለበትን የአሠራር ችግር በማስተካከል ውጤታማ ስፖርተኞችን እንዲያፈራ ተጠየቀ

የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ያለበትን የአሠራር ችግር በማስተካከል ውጤታማ ስፖርተኞችን እንዲያፈራ ተጠየቀ

በኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ የ2007 በጀት ዓመት የፋይናንሻል የኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ስብሰባ /Public Hearing/ ህዳር 14፣ 2009 ዓ.ም ተካሄደ፡፡ በስብሰባው ተቋሙ ያሉበትን የአሠራር ችግሮች በመቅረፍ ውጤትን መሠረት ያደረገ ስራ እንዲሠራ ተጠይቋል፡፡

በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅራቢነት በቀረበው የውይይት ጥያቄዎች ላይ እንደተመለከተው ስፖርት አካዳሚው ስህተት ፈፅሟል በተባለባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተቋሙ አመራሮች ማብራሪያ እንዲሰጡ በመጠየቅ ሰፊ ውይይት ተደረጎባቸዋል፡፡

አካዳሚው የአስተዳደር ቦርድ ለወንድ ሰልጣኞች ብር 300.00፣ ለሴት ሰልጣኞች ብር 350.00 የኪስ ገንዘብ እንዲከፍል የውሳኔ ሃሳብ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ሳይፀድቅ ብር 552,500.00 ከመመሪያ ውጪ ክፍያ የፈፀመ መሆኑን፣ የምርምር ጥናታዊ ፅሑፍ እና የመሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ ጥናት ላቀረቡ የመ/ቤቱ ሠራተኞች ለማበረታቻ ተብሎ የተያዘ በጀት ሳይኖርና ከሚመለከተው አካል ሳይፈቀድ በድምሩ ብር 177,914.00 ክፍያ የተከፈለ መሆኑንና የክፍያው ትክክለኛነት ሳይረጋገጥ ከቀረበው ማስረጃ በላይ ለምግብ አቅርቦት በብልጫ ብር 5,264.00 ክፍያ የተፈፀመ መሆኑን የኦዲት ሪፖርቱ አሳይቷል፡፡

እንደዚሁም ከገቢ ግብር አዋጅ፣ ደንብና መመሪያ አኳያ አካዳሚው የትርፍ ሰዓት ክፍያ ሲፈፀም መቀነስ የነበረበት ብር 5,538.23 የስራ ግብር ያልተቀነሰ መሆኑን፣ የተለያዩ ግዢዎችና አገልግሎቶች ሲፈፀሙ የቅድሚያ ግብር ተቀናሽና የተጨማሪ እሴት ታክስ ተከፋይ ሒሳብ በአዋጁ በተደነገገው የጊዜ ገደብ ውስጥ ባለመፈፀሙ ብር 20,057.09 ቅጣት ተጥሎበት አካዳሚው የከፈለ መሆኑን የኦዲት ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

ከግዢ ጋር በተያያዘም የስፖርት አካዳሚው የግዢና የጥገና መጠየቂያ ያልቀረበላቸው፣ የዋጋ ማወዳደሪያ ያልተሰበሰበባቸው እና ለተገዙ እቃዎች የንብረት ገቢ ደረሰኝ (ሞዴል 19) ያልተቆረጠላቸው የጥገና እና የአገልግሎት እቃዎች ግዢ በብር 68,406.56 ከመመሪያ ውጪ ግዢ የፈፀመ መሆኑን፤ ከደንብ ልብስ አስፈላጊነት እና ዓላማ ውጪ ለደንብ ልብስ ስፌት በሚል ለሠራተኞች በብር 84,720.00 የጥሬ ገንዘብ ክፍያ ተፈፅሞ መገኘቱን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል በኦዲት ግኝቱ እንደተመለከተው ስፖርት አካዳሚው ለ2007 በጀት ዓመት ከተመደበለት የመደበኛ በጀት ብር 5,291,298.02 (ከ10% በላይ) ሥራ ላይ ያልዋለ መሆኑ፤ ከተደለደለው በጀት በላይ ብር 1,627,005.20 ወጪ ያደረገ መሆኑ እና ተጨማሪ በጀት መኖሩ በበጀት ክፍሉ ሳይረጋገጥ ብር 482,694.45 ለተለያዩ ክፍያዎች መፈፀሙ ተረጋግጧል፡፡

ከንብረት አያያዝና ቆጠራ ጋር በተያያዘም ስፖርት አካዳሚው በ2006 እና 2007 ዓ.ም ባደረገው የንብረት ቆጠራ በስቶክ ካርድ ያለመመዝገብ፣ ከወጪ ቀሪ ያለመመዛዘኑን፣ ለቋሚ ንብረት የመለያ ቁጥር አሟልቶ ያለመስጠት፣ የንብረት ክፍል ሠራተኞች ሲቀያየሩ በትክክል ርክክብ ያለመደረጉን፣ የንብረት ገቢና ወጪ ሞዴል-19 እና ሞዴል-22 በአግባቡ ባለመሰራታቸው ሁለት መኪና አሸዋ በብር 13,000 ተገዝቶ ገቢ ሳይደረግ አስረካቢው ብቻ ፈርሞ ተረካቢው አለመፈረሙን እና ለጥገና አገልግሎት ግዢ ክፍያ ብር 68,406.56  ከግዢ መመሪያ ውጪ መፈፀሙን የኦዲት ሪፖርቱ አመልክቶ ቋሚ ኮሚቴው ከኦዲት ግኝቱ በኋላ የአካዳሚው አመራር የወሰደውን የማስተካከያ እርምጃ እንዲያብራራ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

የስፖርት አካዳሚው ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ፍቃዱ መኩሪያ በቀረቡት ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ በርካታ ችግሮች የተፈጠሩት የስፖርት አካዳሚው ከተመሠረተ አጭር እድሜ ያለው በመሆኑ ከልምድ ማነስ ጋር ተያይዞ የተፈጠሩ እንደሆኑ ገልፀው ዳይሬክተሩ ለደንብ ልብስ ከመመሪያው ውጪ በጥሬ ገንዘብ ክፍያ የተፈጸመበት ምክንያት የግዢ ኤጀንሲ የሚፈለገውን የደንብ ልብስ በጊዜ ሊያቀርብ ባለመቻሉ እንደሆነ፣ የውሎ አበል ፎርሞች በሚመለከታቸው አካላት ሳይፈረሙ የተፈጸመውን ክፍያ በተመለከተም ከኦዲት ሪፖርቱ በኋላ መስተካከሉን፣ ከ10 በመቶ በላይ በጀት ስራ ላይ ያልዋለውም በበጀታቸው ላይ በአግባቡ ቁጥጥር ባለማድረጋቸውና የቁጥጥር ስርዓታቸው ደካማ በመሆኑ እንደሆነ ገልፀው የእርምት እርምጃ መወሰዳቸውን ገልፀዋል፡፡

የንብረት ቆጠራ በአግባቡ ያልተደረገውም በቂ የሰው ሃይል ባለመኖሩ እንደሆነና ከኦዲት ግኝቱ በኋላ ሙሉ በሙሉ የተፈጠረውን ችግር ማስተካከላቸውን፣ በአግባቡ ያልተፈረሙ ሞዴሎችም መፈረማቸውን ገልፀው የበጀት ቁጥጥር አከባቢ ያለውን ችግር ለመቅረፍ አጠናክረው እንደሚሠሩበት እና የውስጥ ኦዲት ችግር ለመቅረፍ ተከታታይ ማስታወቂያ በማውጣት ለመቅጠር የተደረገው ጥረት ባለመሳካቱ አሁንም ችግሩ መኖሩን አቶ ፈቃዱ አስረድተዋል፡፡

ሌሎች የስፖርት አካዳሚው አመራሮች በሌሎች በተነሱ ጥያቄዎች ላይ በሰጡት ምላሽ ተቋሙ ባለበት የሰው ሀይል እጥረት ሳቢያ በስራቸው ላይ ክፍተት እንደተፈጠረ አስረድተዋል፡፡

የስፖርት አካዳሚው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሲራክ ኃ/ማርያም ሲያስረዱ በተቋሙ እየታየ ያለውን የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር ለመቅረፍ በስነ-ምግባርና በለውጥ ሥራ ክፍሎች በተዘጋጁ መድረኮች ሠራተኛው ከብልሹ አሰራሮች ፀድቶ ሥራውን በሚጠበቀው ደረጃ እንዲሠራ የግንዛቤ ማስጨበጫ የተለያዩ መድረኮች እንደተዘጋጁና ለጥናትና ምርምር አካዳሚው ትኩረት በመስጠት እየሰሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

በይፋዊ ስብሰባው የተገኙ ባለድርሻ አካላት የተለያዩ ሃሳቦችን የሰጡ ሲሆን አብዛኞቹ ሠራተኞች የደንብ ልብስ መውሰድ ስለማይፈልጉና በደንብ ልብሱ ምትክ ክፍያ እንዲፈፀምላቸው የማድረግ ፍላጎት በመኖሩ ደንብ ልብሱን ላለመረከብ የመጓተት ሁኔታ እንዳለና አሁንም በጀት መኖሩ ሳይረጋገጥ ክፍያ እየተፈፀመ እንደሚገኝ የገለፁ ሲሆን ስፖርት አካዳሚው አዲስ እንደመሆኑ ያን ያህል የተጠራቀመ ንብረት ስለማይኖረው ንብረት አያያዝ ላይ ከአሁኑ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባና የግዢ ችግርንም ለመፍታት ከመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር አገልግሎት ጋር በመነጋገር የግዢ አገልግሎቱ በጊዜ ሊያቀርብ በማይችላቸው ዕቃዎች ላይ ተቋሙ በራሱ ግዢ ሊፈጽም የሚችልበት አግባብ እንዳለ አስረድተዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በሰጡት ሃሳብ ስፖርት አካዳሚው የሰው ኃይል ማነስን በመረዳት የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የሰራውን ሥራ በጠንካራ ጎን በመውሰድ ስህተቶችን ከተቋሙ አዲስነት ጋር በማያያዝ ለማስረዳት መሞከሩ አግባብ እንዳልሆነና ተቋሙ አዲስ መሆኑን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ወስዶ ሊሠራ እና መንግስት ያወጣቸውን የፋይናንስ ህጎች፣ ደንቦችና መመሪያዎች በአግባቡ ተፈፃሚ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት ሃሳብ የተቋሙ አመራሮች የኦዲት ግኝቱን ተከትለው ለማስተካከል በፍጥነት የወሰዱትን እርምጃ አድንቀው ነገር ግን ለጥናትና ምርምር እንዲሁም መሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ (BPR) ለማሰራት ተብሎ የተፈፀመው ክፍያ በሰነድ የተገኘው ለማበረታቻ ተብሎ መከፈሉን ገልፀው ተቋሙ ለመሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ ጥናት አማካሪ አካላትን ምክር መጠየቅ ቢችልም ቢፒአሩን መስራት ያለበት ተቋሙ ራሱ መሆን እና ከዚህ ጋር ተያይዞ ከመደበኛ ስራ ሰዓት ውጪ ቅዳሜና እሁድ እንዲሁም በዓላትን ጨምሮ ለሠሩበት ተብሎ የተፈፀመው ክፍያ ስለመስራተቸው ማረጋገጫ ያልቀረበበት በመሆኑ የተፈጸመው ክፍያ ተመላሽ መሆን እንዳለበት ገልፀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የገቢ ግብር አዋጅን በመጣስ ተቋሙ ሳይከፍል ለቆየው ክፍያ ቅጣት መንግስት እንዲቀጣ የተደረገው ብር 20ሺ ትክክል ባለመሆኑ መቀጣት ካለበት የተቋሙ አመራር በመሆኑ የመንግስት ብር ተመላሽ ሊሆን እንደሚገባ ገልፀው የበጀት አጠቃቀምን በተመለከተም በጀት ዝውውር ሳይደረግ ጥቅም ላይ የዋለ በጀት ሊስተካከል እንደሚገባ ዋና ኦዲተር አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በመጨረሻ ባስተላለፉት መልዕክት ስፖርት አካዳሚው የኦዲት ግኝቱን ተከትሎ የድርጊት መርሃ ግብር በወቅቱ አዘጋጅቶ መላኩንና በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ የወሰዳቸው የማስተካከያ እርምጃዎች ጥሩ ጅምር መሆናቸውን ገልፀው ተቋሙ በስነ-ምግባር የታነፁ  አካላዊና መንፈሳዊ ጥንካሬ ኖሯቸው በአገራዊና ዓለም ዓቀፋዊ ውድድሮች አገርን የሚያስጠሩ ስፖርተኞችን እንዲያፈራ ትልቅ ኃላፊነት የተጣለበት በመሆኑ ለወጣቶቹ የሚመደበውን ሃብት በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል እንደሚጠበቅበት፤ በጀት አጠቃቀም ላይም እየታዩ ያሉ ችግሮችን ሊያስተካክል እንደሚገባ፤ የሰው ሃይል ማደራጀት በስልጠናም ሆነ በልምድ ልውውጥ የውስጥ አቅምን ማሳደግ እንደሚያስፈልግ፤ የኪራይ ሰብሳቢነትና መልካም አስተዳደር ችግሮች በአግባቡ ተለይተው ሊሠራባቸው እንደሚያስፈልግ፤ የጥናትና ምርምር ስራው በዘርፉ ያለውን የውጤት ችግር ከመቅረፍ አኳያ የጎላ ሚና የሚኖረው በመሆኑ አካዳሚው ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚጠበቅበትና በአጭር ጊዜ የታዩትን ችግሮች ማሰተካከል እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *