የአገሪቷን የእግር ኳስ ችግር ለመቅረፍ ስፖርቱ በዘመናዊ የአሰራር ስርዓት ሊመራ እንደሚገባው ተጠቆመ
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2007 የእግር ኳስ ስፖርትን ለመምራት እና ለማስፋፋት እያከናወነ ያለውን የአሠራር ሥርዓት በተመለከተ የክዋኔ ኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ስብሰባ /Public Hearing/ ህዳር 14፣ 2009 ዓ.ም ስብሰባ ተደረገ፡፡ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ውጤትን መሠረት የደረገ ሥራ በመስራት ለህዝብ የውጤት ጥማት ምላሽ ሊሰጥ እንደሚገባ ተጠይቋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በፌዴሬሽኑ ላይ ያከናወነውን የክዋኔ ኦዲት ግኝት መሰረት በማድረግ በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ፌዴሬሽኑ ስህተት ፈፅሟል በተባለባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተቋሙ አመራሮች ማብራሪያ እንዲሰጡ በመጠየቅ ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡
በኦዲት ሪፖርቱ እንደተመላከተው ፌዴሬሽኑ በ2006 ዓ.ም የዓለም ዓቀፍ አደረጃጀትን መነሻ በማድረግ የውስጥ መዋቅራዊ አደረጃጀትና የሰው ኃይል ፍላጎት ጥናት ያስጠና ቢሆንም ጥናቱን ተግባራዊ አለማድረጉን፤ በትምህርት ቤቶች እግር ኳስ ሁኔታ፣ በብሔራዊ ቡድኖች ውጤት፣ በወደፊቱ የአገሪቱ እግር ኳስ ላይ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በመስራት ተግባራዊ ማድረግ ቢጠበቅበትም በየዓመቱ የሚሠራቸውን ጥናቶች በእቅድ በመያዝ እንዲተገበሩ አለማድረጉ በኦዲቱ ተጠቅሷል፡፡
ፌዴሬሽኑ በሁሉም ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የሚገኙ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኖች፣ ክለቦችና ፕሮጀክቶች እንዲቋቋሙና እንዲደራጁ ድጋፍና ክትትል ያላደረገ መሆኑ፤ የክልል ፌዴሬሽኖችና ክለቦች በፌዴሬሽኑ መተዳደደሪያ ደንብ ላይ የተቀመጡ የአባላት ግዴታዎችን ስለመወጣታቸው የሚከታተልበት ሥርዓት ያልዘረጋ መሆኑ እና በሁሉም እድሜ ክልል የሚገኙ ሴቶችን ተሳትፏቸውን የሚያጠናክርበት ሥርዓት የሌለው መሆኑን የኦዲት ግኝቱ አመልክቷል፡፡
እንደዚሁም በኦዲቱ ወቅት በናሙና የታዩ የኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ፌዴሬሽኖች ብስራት በሚል ተሰጥቷቸው ፌዴሬሽኑ ያቋቋማቸው የታዳጊ ወጣቶች ልማት ፕሮግራሞች የአፍሪካ እግር ኳስ ማህበር የፍቃድ አሰጣጥ ደንብ ላይ የተቀመጡትን የሰው ሃይል፣ የስልጠናና የውድድር እንዲሁም የፋይናንስ ምንጭና የተጨዋቾች የህክምና አቅርቦቶች መስፈርት ሳያሟሉ የተቋቋሙ መሆናቸው፤ በ2006 ዓ.ም ለእነዚህ ክለቦች ለአሰልጣኞች ክፍያና የመጫወቻ ኳሶችን ከመስጠት ያለፈ ምንም አይነት ክትትልና ድጋፍ ያልተደረገላቸው መሆኑ በኦዲት ግኝቱ ተገልጿል፡፡
የአፍሪካና የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማህበራት ደረጃና ፈቃድ አሰጣጥ ደንብ በሚጠይቀው ቅድመ ሁኔታ መሠረት የተሟላ ጽ/ቤት፣ በሙያው የሰለጠነ ባለሙያ፣ በቂ በጀትና የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ እንዲሁም የባንክ አካውንት በሟሟላት መቋቋም እንዳለባቸው በደንቡ የተቀመጠ ቢሆንም በኦዲቱ ወቅት በናሙና ከታዩት የእግር ኳስ ክለቦች ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ቡራዩ፣ ሰበታ፣ ወልወሎ እና መቀሌ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ አሟልተው ያልተቋቋሙ ስለመሆናቸው እና ከእነዚህ ክለቦች ውስጥ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ከኢትዮጵያ ቡና ክለቦች በስተቀር በውጭ ኦዲተር ሂሳባቸውን የማያስመረምሩ መሆናቸው በኦዲት ግኝቱ ተመላክቷል፡፡
ፌዴሬሽኑ ከአራት ዋና ዋና ባለድርሻ አካላት ከፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር ትምህርት ሚኒስቴር እና የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በህፃናት እግር ኳስ ልማት ዙሪያ በጋራ ለመስራት የሚያስችል ሰነድ በ2006 ዓ.ም የተዘጋጀ ቢሆንም ተፈርሞ ወደ ተግባር ያልተገባ መሆኑ፤ በታዳጊ ፕሮጀክቶች የታቀፉት ታዳጊ ሰልጣኞች ከስልጠና ጋር በተያያዘ ለሚያጋጥማቸው ጉዳት የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዳልሆኑ በሪፐርቱ ተጠቁሟል፡፡
ፌዴሬሽኑ በሲኤምሲ አከባቢ የሚገኘውን የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ለምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገሮች የእግር ኳስ አካዳሚ ህንፃ ፕሮጀክት ግቢ አጥር ለማስገንባት የተላከውን የ250 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ያለጨረታ ለአንድ ድረጅት የተሠጠ መሆኑ በኦዲቱ ተጠቅሷል፡፡
ፌዴሬሽኑ ለአሰልጣኖች የሚሰጠው ደረጃ ከዓለም አቀፍ ደረጃ ጋር የማይጣጣም መስፈርቱን የማያሟላና በሁለቱም ፆታ ብሔራዊ ቡድኖች የሚያሰለጥኑ አሰልጣኞች ለመምረጥ የሚያስችል ግልፅ የሆነ የመመልመያ መስፈርት ባለማዘጋጀቱ የቴክኒክ ኮሚቴው በየጊዜው እንደአስፈላጊነቱ በሚያመጣቸው መመዘኛዎች የሚመርጥ መሆኑ እና የፀረ-ዶፒንግ /አበረታች መድሃኒት/ ቁጥጥር ተግባራዊ የሚያደርግባቸው ሥርዓት ተግባራዊ ያላደረገ መሆኑ ኦዲቱ ሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
ፌዴሬሽኑ በሁለቱም ፆታዎች የሚያዘጋጃቸው ውድድሮች የሁሉም ሊጎች የአገር አቀፍ የእግር ኳስ ማህበር የጊዜ ሰሌዳን መሠረት የማያደርጉና በየውድድር ዓመቱ የሚያወጣቸው የሊጎች የውድድር መርሃ ግብር የሁሉንም ክልሎች ተጨባጭ ሁኔታን ያላገናዘቡ መሆናቸውን፣ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ያሉ መረጃዎችን ተሰብስበውና ተደራጅተው በዘመናዊ የመረጃ ቋት ያልተያዙና የመረጃ መረብ የሌለው መሆኑንና የራሱ የሆነ ብሔራዊ ስታዲየም ለመገንባት በዕቅድ ይዞ ያልገነባ እና ከዓለም አቀፍ የእግር ኳስ ማህበር (ፊፋ) ለቢሮ ግንባታ እ.ኤ.አ 2015 የተመደበለትን 500 ሺህ ዶላር ለግንባታ አለማዋሉ በኦዲት ግኝቱ ተረጋግጧል፡፡
በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በነዚህ የኦዲት ግንቶች ላይ የተቋሙ አመራሮች ማብራሪያ እንዲሰጡባቸው ጥያቄዎችን አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁኔይዲ በሻ በተነሱት ጥያቄዎች ላይ ምላሽ ሲሰጡ የኦዲት ግኝቱ በተቋሙ ውስጥ ያለውን ችግር ለማወቅና መፍትሔ ለመስጠት እንደጠቀማቸው ገልፀው በተቋሙ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የ5 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ በማዘጋጀት የባለሙያውንና፣ የፋይናንስ አቅምን እንዲሁም የውጭ ግንኙነትን ማሳደግ፤ በአገር ውስጥ ያሉ ውድድሮችን ለማሻሻል እና የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ላይ ጥኩረት ሰጥተው እየሰሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ለክልሎች የሚያደርገው አነስተኛ እንደሆነ ለተገለፀው ሃሳብ ምላሽ ሲሰጡ ፌዴሬሽኑ በተለያየ ጊዜ ለክልሎች ድጋፍ ማድረጉን፣ ጥናትና ምርምርን በተመለከተ ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር ግንኙነት መፍጠራቸውን በመግለፅ በጥናት ላይ የተመሰረቱ ሥራዎች ለመተግበር እየሰሩ እንደሚገኙ፣ በህፃናት እግር ኳስ ትኩረት በመስጠት ከ20 ዓመት በታች፣ ከ17 ዓመት በታች እና ከ15 ዓመት በታች ውድድሮችን በማድረግ እንዲሁም ከኮካ ኮላ ድርጅት ጋር በመተባበር እየተሠራ ያሉ በርካታ ሥራዎች መኖራቸውን፤ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ትሳተፍባቸው የነበሩ መድረኮች እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በሁለት ዘርፍ ብቻ እንደነበረ አስታውሰው በአሁን ሰዓት የሚሳተፉበት ውድድር መድረኮች ወደ 8 ማደጋቸውን እና በሲኤምሲ አከባቢ የሚገነባውን የእግር ኳስ አካዳሚ በጀቱንም ሆነ ሥራውን የሚከታተለው ድጋፉን ያደረገው አካል እንደሆነ አቶ ጁኔይዲ በሻ አስረድተዋል፡፡
ሌሎች የፌዴሬሽኑ ከፍተኛ አመራሮች በሰጡት ምላሽ ፌዴሬሽኑ በአገር አቀፍ ደረጃ ባወጣው የውድድር ሰሌደ መሠረት ሊመራ ያማይችለው በበርካታ ምክንያቶች እንደሆነ ገልፀው በተለይም የአዲስ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም በተለያዩ አገራዊ መድረኮች የሚያዝበት ሁኔታ እንዳለና በተቻለ አቅም ሊጎች በጊዜ ተጅምረው ክረምት ሳይገባ እንዲጠናቀቁ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ፣ የልምድ ለውውጥ ለማድረግ ብራዚል ድረስ በመሄድ መደረጉን፤ ሽልማት በተመለከተ ስፖርቱ የወጣቶች እንደመሆኑ ወጣቶቹን ለማነቃቃትና ለማበረታታት ከፍተኛ የሽልማት ገንዘብ እንደሚጠይቅ ገልፀው ሽልማት አሰጣጡ የሚከናወነው በቴክኒክ ኮሚቴው ታይቶ እንደሆነ፤ ዛሬም ክለቦች ለሴቶች ተሳትፎ የሚሠጡት ቦታ ዝቅተኛ ቢሆንም የተለያዩ ህጎችና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ተሳትፎ እንዲጨምር እየተሰራ መሆኑን፤ በእግር ኳሱ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ቅንጅት በመፍጠር እየሰሩ እንደሚገኙ እና ስልጠና ትውልድን የማስቀጠል ሚና እንዳለው ግምት ውስጥ በማስገባት የተለያዩ አይነት ስልጠናዎች እየተሰጡ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላት እንደገለፁት ፌዴሬሽኑ የኦዲት ግኝቱን ለቀጣይ ስራቸው ጠቃሚ እንደሆነ መቀበላቸውን አድንቀው ከህፃናት እግር ኳስ ልማት ጋር በተያያዘ ከሚመለከታው አካላት ጋር በመቀናጀት የበለጠ ሊሰራ እንደሚገባ፣ የሴቶችን ተሳትፎ በስፖርቱ ለማጎልበት አሁንም ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ፣ ከፀረ-ዶፒንግ መድሃኒት ጋር ተያይዞ በእግር ኳሱ ላይም ጥላውን እንዳያጠላ አስቀድሞ ሊሰሩ የሚገቡ ስራዎች ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ እና ከዳኞችና አሰልጣኞች መመዘኛ መስፈርት አንጻርም ያለውን ችግር ለመፍታት ወጥ የሆነ መመሪያ ማዘጋጀት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ሲናገሩ ስፖርቱ የገፅታ ግንባታና የኢኮኖሚ ጉዳይ እንዲሁም የጠቅላላ የኢትዮጵያ ህዝብን ፍላጎት ያያዘ እንደመሆኑ ወጥ የሆነ ስርዓት መዘርጋት እንደሚጥይቅ፤ የመንግስትንም ሆነ የህዝብን ድጋፍ ለማምጣት ስፖርቱን ወደ ቢዝነስ መለወጥና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ግብ መሆን ያለበት አገሪቱን እንዴት ወደ እግር ኳስ አገር /Football Nation/ መለወጥ ወይም ማሳደግ እንደሚቻል አስቦ መስራት እንደሚያስፈልግ እና እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ እንደ አትሌትክስ ፌዴሬሽን ሁሉ እራሱን በባለሙያ የሚያደራጅበት ስርዓት ቢዘረጋ ስፖርቱን ለማሳደግ እንደሚረዳ አስገንዝቧል፡፡
የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በመጨረሻ ባስተላለፉት መልዕክት የኦዲት ግኝቱን መሠረት አድረጎ ፌዴሬሽኑ የወሰዳቸውን የማሻሻያ እርምጃዎች በማድነቅ ስፖርቱ እንዲያድግ የውድድር አይነቶቹን እንዲሰፉ መደረጉን፣ የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ብሔራዊና የፕሪሚየርሊግ ክለቦች ሴቶችን እንዲያቅፉ ተደረጎ መሠራቱን እና ለውጭ ግንኙነትና ገጽታ ግንባታ እንዲሁም ልምድ መቅሰም ከአገር ውጪ የሚደረጉ ውድድሮችና ስልጠናዎች የሚበረታቱ እንደሆኑ ግልፀዋል፡፡
ሰብሳቢው በቀጠይ በፌዴሬሽኑ ትኩረት ይሻሉ ባላቸው ጉዳዮች ሃሳብ የሰጡ ሲሆን የሁሉም ስፖርት ስኬት የሚለካው ባስመዝገበው ውጤት በመሆኑ ፌዴሬሽኑ ውጤትን መሠረት ያደረገ ሥራ ሊሰራ እንደሚገባ፣ የክልልና የፌዴራል የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ግንኙነት በመደጋገፍ እና አቅም በመገንባት ላይ የተጠናከረ ቅንጅት ሊፈጠር እንደሚገባ፤ ፌዴሬሽኑ ስፖርታዊ ስነ-ምግባር /discipline/ ላይ እየሰራ ያለውን ሥራ አጠናክሮ ሊሠራ እንደሚገባ፤ ስፖርቱ ሳዊንሳዊና በእውቀት የተደገፈ እንዲሆን የተጠናከረ ሥርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ እና ለእግር ኳስ ውጤት የተለያዩ አካላት ቅንጅት ወሳኝ በመሆኑ የሚመለካታቸው አካላት በሙሉ እንዲሠሩ ማደረግ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል፡፡