በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የመንግሰት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የንግድ ሚኒስቴር መ/ቤትን የ2007 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ይፋዊ ስብሰባ ሚያዚያ 25 ቀን፣ 2009 ዓ.ም ባካሄደበት ወቅት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ህግና ደንብ ማስከበር ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ ገለፀ፡፡
የሚኒስቴር መ/ቤቱን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ የተወሰደውን እርምጃ በተመለከተ ያደመጠው ቋሚ ኮሚቴው ተቋሙ በአዋጅና መመሪያ እንዲያስፈፅም የተሰጠውን ሥራ እንዳይሰራ ያደረገውን ጉዳይ እንዲያብራሩ ለተቋሙ አመራሮች በርካታ ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡
በቋሚ ኮሚቴው ለሚኒስቴር መ/ቤቱ ከቀረቡት ጥያቄዎች ውስጥ ውክልና የሰጣቸውን የክልል ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች የስነ-ልክ ሥራዎች የመከታተልና የመደገፍ ሥራ አለማከናወኑን፤ ክልሎችም የዕቅድ ክንውን ሪፖርታቸውን ለሚኒስቴር መ/ቤቱ እንደማይልኩ፤ የደረጃዎች ፍተሻ አፈፃፀምን ውጤታማነትና ቀልጣፋ የሚያደርግ የአሠራር መመሪያ አውጥቶ በሥሩ ለሚገኙ የቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ሊያሳውቅና ተግባራዊነታቸውንም ሊያረጋግጥ የሚገባ ቢሆንም በናሙና ኦዲት በተደረገባቸው ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች መመሪያው የሌላቸው መሆኑን፤ በስትራቴጂክ ዕቅድና ዓመታዊ ዕቅድ ላይ የሰው ሃብት ቁጥር በእውቀት፣ በክህሎት እና በአመለካከት በማጎልበት የማስፈፀም አቅሙን ወደተሸለ ደረጃ ለማድረስ ቢያቅድም በዕቅዱ መሠረት የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን አፈፃፀም እየተከታተለ አለመሆኑ ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል ሚኒስቴር መ/ቤቱ የወጪ ምርቶች ከአገር ከመውጣታቸው በፊት ደህንነታቸውን እና ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲወጡ በህግ የተደነገገ ቢሆንም በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ጥራታቸው ለመጠበቅ የሚያስችል የምርት ማበጠሪያ መጋዘኖች የሌሏቸው መሆኑን፤ የገቢ እቃዎችን በተመለከተ የደረጃ መስፈርት የማያሟሉ መሆናቸው ተረጋግጦ እንዲታገዱ ከተደረገ በኋላ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በአዋጅ ከተደነገገው በተቃራኒ ደብዳቤ በመፃፍ እንዲለቀቁ የሚያደርግ መሆኑን፤ አስገዳጅ የኢትዮጵያ ደረጃ ያላቸው የንግድ እቃዎችና አገልግሎቶች ከተዘጋጀው ደረጃ በታች ሆነው በተገኙት ላይ እርምጃ እንደማይወስድ፤ ከውጭ የሚገቡ የመለኪያ መሣሪያዎች ወደገበያ ከመግባታቸው በፊት ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸው የማይረጋገጥ መሆኑን፤ የናሙናዎችን መረጃ በጥንቃቄ በባህር መዝገብና በመረጃ ቋት መዝግቦ በመያዝ ወቅቱን የጠበቀ መረጃ በማሰባሰብ፣ በማደራጀትና በመተንተን ለቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችና ለተገልጋዮች ሊያሰራጭ የሚገባው ቢሆንም በናሙና በታዩ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ናሙናዎች በመረጃ ቋት ተመዝግበው አለመያዛቸውን እና በክልል የሚያካሄደውን የሕጋዊ ሥነ-ልክ አተገባበርና አሠራር ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሊገመግምና ድጋፍ ሊያደርግ የሚገባው ቢሆንም ግምገማና ድጋፍ እንደማያደርግ በኦዲት ግኝቱ ተመላክቶ መ/ቤቱ በአዋጅ የተሠጡትን ተግባራትና ኃላፊነቶች በአግባቡ ተግባራዊ ማድረግ ያልቻለበትን ምክንያት የስራ አመራሮቹ እንዲያብራሩ ቋሚ ኮሚቴው ጥያቄዎቹን አቅርቧል፡፡
የሚኒስቴር መ/ቤቱ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር በቀለ ቡላዶ ከሌሎች የስራ ባልደረቦቻቸው ጋር በተነሱት ጥያቄዎች ላይ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን በገለፃቸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ግኝት እውነተኛና ተቀባይነት ያላቸው መሆናቸው ገልፀው መ/ቤታቸውም የኦዲት ግኝቱን መሠረት በማድረግ አሠራራቸውን ለማሻሻል ወደሥራ መግባታቸውንና በዚህም መልካም የሚባሉ ለውጦችን ማስመዝገብ መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡
ክቡር ሚኒስትሩ እንዳሉት ክልሎች ጋር የነበረውን የእቅድ አፈፃፀም ክትትል በማሻሻል በወቅቱ ክትትልና ግምገማ እየተደረገ እንደሚገኝና ግብረመልስም ለክልሎች እየሰጡ እንደሚገኙ፣ የሰው ኃይል ማደራጀትና ለሥራ የሚያስፈልጉ መገልገያዎችን ማሟላት ላይ የነበረውን ችግር ለማስተካከል ሠራተኞችን በማሰልጠንና አዲስ በመቅጠር ክፍተቶችን ለመሙላት ሥራዎች እየተሠሩ እንደሚገኙ፤ ከጥራት ጋር በተያያዘ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡም ሆነ ከአገር በሚወጡ ምርቶች ላይ የሚታየውን የጥራት ችግር ለመቅረፍ የአሠራር ለውጥ መደረጉንና በዚህም የተሻለ ውጤት ያመጣል ብለው እንደሚያምኑ፤ ከደረጃ መስፈርት በታች ያሉ ነጋዴዎች ላይ የተለያዩ የእርምት እርምጃዎችን መውሰዳቸውን ገልፀው ሥራቸውን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የመቆጣጠሪያ መሣሪያዎች እጥረት በመኖሩ እጥረቱን ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ችግሩን ለመቅረፍ እየሠሩ እንደሚገኙ፤ በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫቸው የህግ ማእቀፎችን ማሻሻል ላይ ትኩረት በማድረግ ህጋዊ አሠራርን ለማስፈን እንደሚሠሩ፣ የመረጃ ቋት አደረጃጀት ላይ ጉልህ ችግር መኖሩንና ያለውም መረጃ በውሸት የተሞሉ መሆኑን በመገንዘብ ችግሩን ለመቅረፍ መረጃዎችን በአዲስ መልክ የማደራጀት ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ እንደሚገኙ እና ከስነምግባር ጋር በተያያዘ በየደረጃው የስነምግባር ጉድለቶች ያሉባቸው ፈፃሚዎች እንደሉ ገልፀው እነሱን ተጠያቂ ከማድረግ ባለፈ አእምሮ ላይ ሊሠራ እንደሚገባና ሙስናና ብልሹ አሠራርን የሚጠየፍ ኃላፊዎችና ሠራተኞችን በተለያዩ አግባቦች መፍጠር እንደሚጠይቅ ገልፀው ለተፈፃሚነቱ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡
ሌሎች የተቋሙ አመራሮች ተጨማሪ ማብራሪያዎችና ምላሾችን የሰጡ ሲሆን ከኦዲት ግኝቱ በኋላ ተቋሙ ያለበትን ችግር ለመቅረፍ በመጀመሪያ የአቅም መገንባት ሥራ ላይ እንደተንቀሳቀሱና በዚህም በተቋሙ ውስጥ፣ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እና በክልሎች ያለውን አቅም ክፍተት በመለየት የሰው ሃይል በማሰልጠን፣ አደረጃጀት በማስተካከል፣ ግብዓቶች በማሟላት፣ አሠራር ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመፍታትና የህግ ክፍተቶችን በማሻሻል በተቋሙ የነበሩ ጉድለቶችን ለመሙላት መሞከሩን፤ ከክልሎች ጋር መደበኛ የግንኙነት መድረኮች መፍጠራቸውን፤ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ የግንኙነት መድረኮች ፈጥረው መወያየታቸውን እና የጥራት ደረጃቸውን ሳይጠብቁ ምረቶች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡና እና ከአገር ውጪ እንዲወጡ የተባበሩ ሃላፊዎችን ከስራ ኃላፊነታቸው እንዲነሱ ማድረጋቸውንና በህገወጥ ፎርጅድ ሰርተፍኬት የተስተናገዱ ድርጅቶች ላይ ህጋዊ እርምጃዎች መውሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው አባላትም በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መ/ቤቱ የኦዲት ግኝቱን ተከትሎ የወሰዳቸው የእርምት እርምጃዎች መልካምና ተጠናክረው ሊቀጥሉ የሚገባቸው እንደሆኑ፤ በጥፋት ሥራ ላይ የተገኙ አካላትም ከኃላፊነት ከማንሳት ባለፈ በህግ አግባብ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባበት አግባብ ሊኖር እንደሚገባ፤ የስነ ልክ መለኪያዎች ላይ መ/ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ፤ የባለሙያዎች ስነ-ምግባር ላይ ጥብቅ ክትትል ሊደረግ እንደሚገባ፤ በዘርፉ ያለውን ባለሙያ ማሟላት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ፤ ከባለድርሻ አካላት እንዲሁም ከቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችና ክልሎች ጋር ያለው የቅንጅት ሥራ ተጠናክሮ ሊሠራበት እንደሚገባ እና በረቂቅ ላይ ያሉ መመሪያዎችና ደንቦች ተጠናቀው ወደ ሥራ ቶሎ ማግባት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
ክቡር ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በመጨረሻ በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መ/ቤቱ አሁንም የኦዲት ግኝቱን አስፍተው ሊያዩት እንደሚገባ፤ የሶስተኛ ወገን ፈቃድ አሰጣት ይበልጥ ትኩረትና ቁጥጥር ሊደረገበት እንደሚገባ፤ የወጪ ምርቶች በተለይም ምግብና ኬሚካል በአንድ ቦታ ተቀምጠው የተገኙበት አጋጣሚ በኦዲት ግኝቱ መኖሩን እንዲሁም በጥራት ችግር የተነሳ ወደ አገራቸው የኢትዮጵያ ምርቶች እንዳይገቡ የከለከሉ አገሮች በመኖራቸው ይሄ በአገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ከፍተኛ በመሆኑ በጥንቃቄና በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ፤ ስነ-ልክን በተመለከተም በከፍተኛ ሁኔታ ህብረተሰቡ እየተጎዳ የለበትና ብልሹ አሠራር የሰፈነበት በመሆኑ ህብረተሰቡ እራሱ በአገልግሎት ሰጪው ላይ በቀጥታ ቅሬታ ሊሠፅበት የሚችልበት የቅሬታ ማቅረቢያ አሠራር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ እና የንግዱ ማህበረሰብ ባህል ላይ በወጪና ገቢ እቃዎች ላይ ያለውን ግንዛቤ የማሰሳደጉ ሥራ ትኩረት ተሠጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በስተላለፉት መልዕክት ተቋሙ የኦዲት ግኝቱን በመቀበልና ለተሸለ ሥራ እንደመልካም አገጣሚ ይጠቅመናል ብሎ በመነሳት አሰራራቸውን ለማስተካከል የተጀመሩት ሥራዎች እንዲሁም አሁን ያለውን አሠራራቸውን ይበልጥ ማየት ያስችላቸው ዘንድ ተጨማሪ የክዋኔ ኦዲት እንዲሠራላቸው መጠየቀቸው አመራሩ የተቋሙን አሠራር ለመለወጥ ፍላጎት እንዳላቸው እንደሚያሳይ ገልፀዋል፡፡
ትኩረት ሊሰጥባቸው በሚገቡ ጉዳዮች ላይ ተቋሙ የቅንጅት ሥራውን አጠናክሮ ሊሠራ እንደሚገባ፤ የተጀመሩ የቴክኖሎጂ ማዘመን ሥራዎች ሊጎለብቱና ለጠናከሩ እንደሚገባ፤ የአሠራር ክፍተቶች ለመሙላት የሚያስችሉት የህግ ማዕቀፎች ማሟለት ላይ በአፋጠኝ ሊኬድባቸው እንደሚገባ፤ ህግና ደንብ ማስከበር ላይ ትኩረት ሊሠጥ እንደሚገባና ከአገር የሚወጡም ሆነ ወደ አገር የሚገቡ እቃዎች ጥራት ላይ ህጉን የጣሱ አካላት ላይ ህጉ በሚፈቅደው ልክ ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ማድረግ እንደሚያስፈልግ፤ ወደ ውጪ በሚላኩ ምርቶች ላይ ጥብቅ የጥራት ደረጃ ቁጥጥር ሊደረግባቸው እንደሚገባ እና በተለይም ህብረተሰቡን እያማረሩ ባሉ የስነ-ልክ መለኪያ መሣሪያዎችና ህገወጥ አሠራሮች ላይ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚጠበቅበት የተከበሩ አምባሳደር መስፍን አሳስበዋል፡፡