News

የመድሀኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን በወቅቱና በፍጥነት ለማቅረብ ኤጀንሲው አሰራሩን ማሻሻል እንዳለበት ተገለጸ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በመድሀኒት ፈንድና አቅርቦት ኤጀንሲ የመድሀኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ግዥ አፈጻጸም ላይ ባከናወነው የክዋኔ ኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ስብሰባ /Public Hearing/ ህዳር 19፣ 2009 ዓ.ም ስብሰባ ተደረገ፡፡ በወቅቱ  በኦዲቱ አማካይነት  በኤጀንሲው አሰራር ላይ የተገኙ ችግሮች በዝርዝር ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ተቋሙ አሁን ባለበት ሁኔታ ለህብረተሰቡ መድሀኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን በወቅቱና በፍጥነት ለማድረስ የማይችል በመሆኑ አሰራሩን ማሻሻል እንዳለበት ተገልጿል፡፡

በስብሰባው ላይ እንደተገለጸው ኤጀንሲው ከፌዴራሉ መንግስት የግዥ አዋጅ ጋር የሚጻረር የግዥ መመሪያ አውጥቶ ጥቅም ላይ ማዋሉ፣ አመታዊ የመድሀኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች የግዥ ጥያቄ ከጤና ተቋማት የሚሰበስብ ቢሆንም ፍላጎቶቹ በበጀት መደገፋቸውን የማያረጋግጥ ጥያቄዎቹንም በመጠን፣ በጊዜና በገንዘብ ተንትኖ የግዥ እቅድ ያላዘጋጀ መሆኑ፣ የሚፈጸሙ ግዥዎች በየበጀት አመቱ ለሚመለከተው አካል ቀርቦ እንዲጸድቅና እንዲፈቀድ ስለመደረጉ እንዲሁም የተዘጋጀው የግዥ እቅድ ለመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ስለመላኩ መረጃ አለመቅረቡን፤ የተፈቀደውም በትክክል ስራ ላይ ስለመዋሉ ክትትል የማይደረግ መሆኑን ኦዲቱ አመልክቷል፡፡

እንደዚሁም ኤጀንሲው ከእቅድ ውጪ ለሚያከናውናቸው ግዢዎች የአስቸኳይ የመድሀኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ግዥ አፈጻጸም መስፈርት ሳያዘጋጅ በድምሩ 16,863,333,00 ብር የሚያወጣ የአስቸኳይ የመድሃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ግዥ መፈጸሙ ተመልክቷል፡፡

በተጨማሪም ከ2005-2007 በጀት አመታት የመንግስት የግዥ መመሪያን ባለመከተል በመመሪያው ከተፈቀደው የገንዘብ መጠን በላይ በውስን ጨረታ ከ11.3 ቢልየን ብር በላይ፣ በቀጥታ ግዥ ከአንድ አቅራቢ ከ692.2 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም በዋጋ ማቅረቢያ ከ12.2 ቢሊዮን ብር በላይ ግዥ በመፈጸም ከፍተኛ ሀብትን ለህገወጥ አሰራር፣ ለምዝበራና ለብክነት ማጋለጡ ብሎም በጥቅል ግዥ የሚገኘውን ጥቅም ማሳጣቱና የግዥውን ሂደት የሚገልጽ ማስረጃ እና የግዥው መንገድ የተመረጠበት ግልጽ ምክንያት ተሟልቶ ግዥው ስለመከናወኑ ማስረጃ አለማቅረቡን ኦዲቱ አመልክቷል፡፡

 

ከዚህም ሌላ አሰራር መመሪያ ሳይኖርና በእቅድ ሳይያዝ ከ2005-2007 በጀት አመታት ከ245 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው መድሃኒቶችና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች መንግስታዊ ላልሆኑ የግል የጤና ተቋማት ማከፋፈሉ፣ ከአንድ አቅራቢ ለሚፈጸም ግዢ የዋጋ ተደራዳሪ ኮሚቴ ሳያቋቁምና የድርድር ማድረጊያ የአትኩሮት ነጥቦች አዘጋጅቶ ሳይሰጥ ከስድስት አቅራቢዎች በድምሩ ከብር 21.2 ሚሊዮን በላይ ግዢ መፈጸሙ፣ በመንግስት የግዥ መመሪያ መሰረት ግዥ የተፈጸመበት ገንዘብ፣ የጨረታው ውጤት እንደዚሁም ሌሎች መረጃዎች በኤጀንሲውና በመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ድረ ገጽ ላይ መቀመጥ እንዳለበት ቢገጽም ይህን አለመፈጸሙ በኦዲት ግኝቱ ላይ ታይቷል፡፡

ኤጀንሲው የጥራት ጉድለት በተገኘባቸው መድሀኒቶችና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች እንዲመለሱ ሲደረግ መመለሳቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ለኢትዮጵያ የምግብ የመድሀኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ከማሳወቅ ባለፈ ስለመመለሳቸው ቁጥጥር የማያደርግ መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የጤና ተቋማት በአመቱ መጀመሪያ የመድሀኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያ ፍላጎታቸውን ቢያሳውቁም ኤጀንሲው ከ30 በመቶ በላይ ፍላጎታቸውን ማሟላት አለመቻሉ እንዲሁም ለሆስፒታሎች አገልግሎት የመጡ መሳሪያዎች የመለዋወጫና የኬሚካል እጥረት ያለባቸው በመሆኑ አገልግሎት የማይሰጡ መሆኑን ሆስፒታሎቹ ከሚጠይቋቸው መድሃኒቶች ውስጥ ከ2005-2008 ዓ.ም ድረስ 986 አይነት የተለያዩ መድሀኒቶችን ኤጀንሲው ማቅረብ አለመቻሉ በናሙና በተመረጡ የጤና ተቋማት የተሰበሰበ መረጃ ማሳየቱን፣ በአዲስ አበባ ባሉና በናሙና ተመርጠው  ለታዩ  የተለያዩ ሆስፒታሎች ኤጀንሲው መድሃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያ በወቅቱና በጠየቁት መጠን ማቅረብ ባለመቻሉ ተቋማቱ በድምሩ ከ105.4 ሚሊዮን ብር በላይ ግዥ  ከግል አስመጪ ድርጅቶች መግዛታቸውም በኦዲቱ ተመልክቷል፡፡  

ኤጀንሲው የጥራት ፍተሻቸው የተጠናቀቀ መድሀኒቶችን በወቅቱ ባለመረከቡና ለ76 ቀናት ከተራገፉበት ቦታ ባለማንሳቱ የገንዘብ መጠናቸው ያልታወቀ መድሃኒቶችና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች  ከአገልግሎት ውጭ ሆነው በተለያዩ መጋዘኖች መከማቸታቸው፣ ምርቶችን ከመድሀኒት አምራቾች በወቅቱ የማይረከብ መሆኑ፣ መድሃኒቶችንና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን በተሰበሰበው ፍላጎት መሰረት የግዥ እቅድ አውጥቶ ግዥን በመፈጸም በወቅቱ ማከፋፈል ሲገባው ባለማደረጉ በአዲስ አበባ ለማንና መቼ እንደተገዙ የማይታወቁ ከ256 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ በአዳማ ቅርንጫፍ ደግሞ የጥራት ችግር ያለባቸው ከ34.8 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድሃኒቶችና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች በመጋዘን ተከማችተው እንዳሉ እንዲሁም ከ2005-2007 ዓ፣ም ድረስ በ11 ቅርንጫፎች በድምሩ ከ569 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የአገልግሎት ጊዜያቸው ያለፈባቸው መድሃኒቶችና ህክምና መገልገያ መሳሪያዎች መኖራቸውን ኦዲቱ አሳይቷል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው እነዚህን ጥያቄዎች በማንሳት ችግሮቹ ለምን እንደተፈጠሩ፣ ኤጀንሲው ከኦዲት ግኝቱ በኋላ ምን የማስተካከያ እርምጃዎችን እንደወሰደ እንዲሁም ኪራይ ሰበሳቢነትን በመታገልና ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ ያለበት ሁኔታ እንዲብራራለት ጠይቋል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሀላፊዎች በሰጡት መልስ ኤጀንሲው በጣም አስፈላጊ መድሃኒቶችንና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን ለመለየትና ፍጆታን፣ ክምችትንና በግዥ ሂደት ላይ ያለን መረጃ መሰረት ያደረገ የፍላጎት ትንበያን ለማከናወን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰራ መሆኑን እንዲሁም የመድሀኒቶችንና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ፍላጎት ተጠቃሎ በኤጀንሲው እንዲከናወን የተለያዩ በሽታዎችን የተመለከተ ኮሚቴ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በማቋቋም የሚገዙ አቅርቦቶችን ምንነት ከነዋጋ ዝርዝራቸው የያዘ እቅድ አዘጋጅቶና በቦርድ አጸድቆ ግዥ ለመፈጸም እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ከመድሂቶችና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች ብክነትና በወደቦች ላይ ቶሎ ካለመረከብ ችግር ጋር በተያያዘ መንስኤ ያሏቸውን ምክንያቶች በመግለጽ እነዚህን ለማስተካከል እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን አስረድተዋል፡፡

በመሰረታዊ መድሃኒቶች አቅርቦት ላይ ነበረውን አቅርቦት ክፍተት ለመሙላትም ከ2007ዓ.ም ጀምሮ ሆስፒታሎችን ጨምሮ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የተለያዩ አካላት በአባልነት ያሉበት ኮሚቴ አቋቁሞ ለሆስፒታሎች አገልግሎት የሚውሉ 1105 መድሀኒቶች ፍላጎት ትንበያ በማከናወን በመጀመሪያ ዙር ጨረታ ከ600 መድሃኒቶች በላይ እንደተገዙና ሌሎቹንም ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን በዚህም ለአብነት በአማኑኤል እና አለርት ሆስፒታሎች እጥረቱን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡

በመመሪያ ረገድም ኤጀንሲው ሲቋቋም መድሃኒቶች ካላቸው ልዩ ባህሪ የተነሳ በኤጀንሲው የስራ አመራር ቦርድ የሚቀረጽ የራሱ የሆነ የግዥ መመሪያ እንዲያዘጋጅ በአዋጅ በተሰጠው ሀላፊነት መሰረት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ የራሱን መመሪያ አጸድቆ ተግባራዊ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው መመሪያው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ቴምፕሌትን የማይከተልና ጣርያ የሌለው በመሆኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር የመንግስት የግዢን መመሪያ መከተል እንደጀመረና በዚህ መመሪያ የማይስተናገዱ ልዩ ሁኔታዎችን ለሚመለከተው የመንግሰት አካል በማስፈቀድ ግዥ እየፈጸመ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ከአስቸኳይ ግዥ መመሪያ አለመኖር ጋር ተያይዞ ለተነሳው ጥያቄም በኤጀንሲው ግዥ መመሪያ ውስጥ ስለአስቸኳይ ግዥ የሰፈረ መሆኑን ነገር ግን መዳበር እንዳለበት አስረድተው በመንግስት ግዥ መመሪያ ውስጥ ስለ አስቸኳይ ግዥ የተደነገገውን በመከተል እንዲሁም ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በወረደ ትዕዛዝ መሰረት ግዢዎችን መፈጸማቸውን ገልጸዋል፡፡ የሥራ ሀላፊዎቹ በተለያዩ የግዢ መንገዶች ስለተገዛበት ምክንያት ሰፊ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ተቋሙ ከግዥ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በድረገጽ ላይ ያላሰፈረበት ምክንያትም ተቋሙ ድረ ገጽ ስላልነበረው በመሆኑ ገልጸው አሁን ግን ችግሩ መፈታቱን አስረድተዋል፡፡

በስራ ሀላፊዎቹ ምላሽ ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን የምክር ቤቱ አባላትም ሆኑ የፌዴራል ዋናው ኦዲተር ምላሾቹ አጥጋቢ እንዳልሆኑና በዋናነት ከመመሪያ ውጪ ስለሰሩበትም ሆነ የተለያዩ የግዥ መንገዶች ስለተመረጡበትና ስለ ግዥው ሂደት ኤጀንሲው ማስረጃ ማቅረብ እንዳልቻለ አጽንኦት ሰጥተው በመግለጽ አሰራሩ መንግስት ያወጣቸውን ህጎች የሚጻረርና ለኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚከፍት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ተቋሙ የኦዲት ግኝቱን መሰረት አድርጎ ማስተካከያ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያደረገውን ጥረት በመልካም ጎኑ አንስተው ነገር ግን ተቋሙ ከተጣለበት ትልቅ ሀገራዊ ሀላፊነት ጋር የተጣጣመ ስራ መስራት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ በዚህ ረገድ የኤጀንሲውን የግዥ መመሪያ ከመንግስት የግዥ መመሪያ ጋር ማጣጣም፣ የአስቸኳይ ግዢ መመሪያውንም በዝርዝር ማዘጋጀት፣ የመድሃኒትና የህክምና መገልገያ መሳርያዎች አቅርቦት የግዥ እቅድ ጥራት ችግርን በማስተካከል እንዲሁም ስርጭትና ክምችትን በመፈተሽ ብክነትን በመቀነስ ፈጣንና ወቅቱን የጠበቀ ግዥና ስርጭት ማካሄድ፤ ለሚያከናውናቸው ግዥዎችም የግዥው መንገድ የተመረጠበትንና ግዥው የተከናወነበትን ሂደት የሚያሳይ ማስረጃ ማቅረብ እንዲሁም ለተበላሹና በጥራት ጉድለት ምክንያት ለሚመለሱ መድሀኒቶችና ህክምና መገልገያ መሳሪያዎች አወጋገድና አመላለስ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት አክለውም ስትራቴጂክ ተቋም በመሆኑ ያለበትን ድክመቶች ለማረምና የተጣለበትን ከፍተኛ ሀላፊነት ለመወጣት በአደረጃጀትና በአመራር ራሱን መፈተሽ እንደሚገባው፣ በተቋሙ ላይ የሚደረገውም ክትትል መጠናከር እንዳለበት፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ የሆኑ አሰራሮችን ለይቶ ማስወገድ እንደሚጠበቅ አጽንኦት በመስጠት አሳስበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ኤጀንሲው አጠቃላይ የክምችትና ስርጭት ስርዓት በመገንባት፣ ከመንግስት የግዥ መመሪያ አንጻር የተቋሙን ግዥ መመሪያ ፈትሾ በማስተካከል፣ በአስቸኳይ ለሚፈጽመው ግዥና ለግል ህክምና ተቋማት መድሃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን በሚያቀርብበት አግባብ ላይ ግልጽ መመሪያ በማዘጋጀት፣ የግዥ እቅድ በፍላጎት ላይ እንዲመሰረት በማድረግ፣ ከአንድ አቅራቢ ለሚፈጸም ግዥ የመደራደሪያ የትኩረት ነጥቦች በማዘጋጀት፣ የመድሃኒትን ክምችት በመለየት እስከታች ድረስ የሚደርስበትን ስርዓት በማጠናከር፣ የጥራት ጉድለት ያለባቸው መድሃኒቶች ወደገበያ እንዳይገቡ ቁጥጥር በማድረግ፣ ጥራት የሚጎድላቸው መድሃኒቶች እንዲተኩ አልያም በባንክ ሌተር ኦፍክሬዲት (Letter of Credit) የተያዘው ገንዘብ እንዲመለስ በማድረግ፣ አሁን ለብክነት እየዳረጉ ያሉ ሁኔታዎችን በመለየት ብክነትን በመቀነስ እንዲሁም የመረጃ አያያዝና አስተዳደር ችግሩን በመፍታት ላይ አትኩሮ መስራት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ክቡር አምባሳደር መስፍን ቸርነት በማጠቃለያ ሀሳባቸው ትንበያን አጠቃሎ ኤጀንሲው ለመስራት፣ አዲስ አበባ ካሉ ሆስፒታሎች ጋር በመሆን አቅርቦቱን ለማሳደግ የጋራ ኮሚቴ አቋቁሞ በመስራት የተጀመሩ ስራዎችን በበጎ ጎን እንደሚታዩ ገልጸው በአንጻሩ ግን ኤጀንሲው ለኦዲት ግኝቶች ትኩረት ሰጥቶ በወቅቱ እንዳልተንቀሳቀሰ፣ መረጃዎችንም ያለማቅረቡና በቴክኒካል ጉዳዮች ላይ በወቅቱ መግባባት ላይ መድረስ ሲገባው ይህንን አለማከናወኑ፣ መስሪያ ቤቱ በኦዲት ግኝቱ መነሻነት ሲታይ ይህንን ያህል የሀገር ሀብት የሚያንቀሳቅስ ስትራቴጂክ ተቋም ተሸክሞ የሚያንቀሳቅስ ፕሮፌሽናል ባለሙያዎች ሊኖሩት እንደሚገባ  ፣ ከሀገሪቱ የግዥ ስርዓት ጋር አብሮ ያለመሄድ ችግር የሚስተዋልበት በመሆኑ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ ማረም እንዳለበት፣ በመረጃ፣ በመመሪያና በህግ ያልተደገፉ ግዥዎችና ወጪዎችን ትክክለኛና ጤናማ ናቸው ብሎ ቋሚ ኮሚቴው ለመቀበል እንደሚቸገር፣ በቀጣይ በኦዲት ሰነዱ ላይ ከዋና ኦዲተር መ/ቤቱ ጋር በሚደረግ ውይይት ትክክለኛ ማስረጃዎችን በማቅረብ መተማመን እንደሚያስፈልግ ትክከለኛ መረጃ ያልቀረበባቸውና በህግ ያልተደገፉትም በህግ መታየት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ከክልሎችና ከጤና ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅት መፈተሽ የተቋማቱን  የሰው ሀይል ፣ የመድሃኒት ፍላጎት፣ ክምችትና ስርጭት ወርዶ በማየት በመናበብ፣ በመቀናጀት አስፈላጊውን  ድጋፍ መስጠትና ስረ መሰረታዊ የችግር መንስኤዎችን መፍታት እንዳለበት፣ በኤጀንሲው ተገዝተው የቀረቡና በመንግስት የጤና ተቋማት የሉም የሚባሉ መድሃኒቶች በግል የህክምና ተቋማት የሚገኙበት መልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት መጣራት እንደሚገባው፣ ለአደረጃጀትና ለአሰራር የተሰጠውን ትኩረት አጠናክሮ መቀጠል ለቢኤስ ሲና ቢፒአርን ትኩረት ሰጥቶ ችግሮችን ለመፍታት በፍጥነት መጣር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር የውስጥ ኦዲትን በማጠናከር ችግሮችን በቅርበት እንዲያርም ማድረግ፣ ሰነዶች በጥራት ታይተው የተሰወዱ እርምጃዎች በዋና ኦዲተር ተረጋግጠው በአጭር ጊዜ ውስጥ ለኮሚቴው ማሳወቅ፣ ተቋሙ ለኪራይ ሰብሳቢነት ተጋላጭ እና አደጋ ላይ ያለ በመሆኑ በህገወጥ የተሰሩ ጉዳዮች ሁሉ እንዲጣሩ፣ መ/ቤቱ የቋሚ ኮሚቴው፣ የስራ አመራር ቦርዱ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የሚመለከታቸው አካላት ክትትልና ቁጥጥር የሚያስፈልገው በመሆኑ ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ እንደሚገባ ገልጸው በአጠቃላይ ሲታይ ኤጀንሲው ቀልጣፋ፣ ውጤታማ፣ ወጪ ቆጣቢ የመድሃኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎችን እያቀረበ ነው በሚባልበት አቋም ላይ ባለመሆኑ ፈጣን ለውጥ ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *