የኢትዮጵያ ቤቶች ኤጀንሲ የሚያስተዳድራቸው ቤቶች አስተዳደርና አሠራር ኢኮኖሚያዊ፣ ውጤታማና ቀልጣፋ በሆነ መልኩ መከናወኑን በተመለከተ የ2007 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ስብሰባ /Public Hearing/ ታህሳስ 21፣ 2009 ዓ.ም ተካሄደ፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅራቢነት በቀረበው የውይይት ጥያቄዎች ላይ እንደተመለከተው ኤጀንሲው ስህተት ፈፅሟል በተባለባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የተቋሙ አመራሮች ማብራሪያ እንዲሰጡ በመጠየቅ ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በኦዲት ግኝቱ እንደተመለከተው ከኤጀንሲው ቤት ለመከራየት ውል በገቡና በየዓመቱ ውላቸውን በማያድሱ ደንበኞች ላይ ቅጣት የማይፈጽም መሆኑ፤ ቤት በነፃ እንዲሰጣቸው ከሚፈቅድላቸው ደንበኞች ጋር አጠቃቀሙን በተመለከተ ምንም አይነት ውል የማይፈራረም መሆኑ እና በኤጀንሲው ከሚተዳደሩ ቤቶች ውስጥ የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የሌላቸው ቤቶች እንዳሉና ካርታ ካላቸው ቤቶች ማህደር ውስጥም ቅጃቸው ያልተያያዘ ቤቶች የሚገኙ መሆኑን በክዋኔ ኦዲቱ ሪፖርት ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
ኤጀንሲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ዓመታት የውል ግዴታቸውን ባለማክበርም ይሁን በሌሎች ምክንያቶች ከተከራዮች ሳይሰበሰብ የቆየ ውዝፍ የቤቶች ኪራይ ብር 98,943,642.56 ያልተሰበሰበ መሆኑም በኦዲት ተረጋግጧል፡፡
በኤጀንሲው ስር ያሉ ቤቶችን ጥገናና እድሳት ለማከናወን የዳሰሳ ጥናት ያልተከናወነ መሆኑ፤ ከደንበኞች በሚቀርብ ጥያቄ ብቻ የጥገና ሥራ የሚሰራና ጥገናውም ለረጅም ጊዜ የሚጓተት መሆኑ እንዲሁም በተለያየ ምክንያት የጥገና ጥያቄ ያላቀረቡ ደንበኞች ቤት ደህንነታቸው የማይጠበቅ ከመሆኑም ባሻገር አብዛኛውን ጊዜ የሚጠገኑት የኃላፊዎች ቤቶች ብቻ እንደሆኑ በኦዲቱ ተገልጿል፡፡ ለአስቸኳይ የጥገና እድሳት ስራም ራሱን የቻለ ቡድን አለመኖሩ የቤቶቹን ደህንነት ማረጋገጥ አስቸጋሪ ከማድረጉም በተጨማሪ ለድንገተኛ አደጋ እና ንብረት መጥፋት ምክንያት ሊሆኑ እንደሚችል የኦዲት ግኝቱ አመልክቷል፡፡
ከጥገናና እድሳት ተመላሽ የሆኑ ዕቃዎች በየቅርንጫፍ ተጠራቅመው እንዳሉና በኤጀንሲው ስር ያሉ 19 ትልልቅ መጋዝኖች የተለያዩ ንብረቶችን ስርዐት በሌለው ሁኔታ እንደተከማቹባቸውና ዕቃዎቹም ከጊዜ ብዛት እየተበላሹ መሆኑ በኦዲት ታይቷል፡፡
በተጨማሪም በሲኤምሲ የነዋሪዎች መንደር ለውሃ ፍጆታ ይወጣ የነበረውን ወጪ ለመቀነስ ታስቦ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የከርሰምድር ውሃ ለማሻሻል በኤጀንሲው ተጀምሮ የነበረው ሥራ ያላለቀና አገልግሎት ይሰጥ የነበረውም ጉድጓድ ሥራ ያቆመ መሆኑ በኦዲቱ ተረጋግጧል፡፡
በነዚህ ጉዳዮችና ለኪራይ ሰብሳቢነት ተጋላጭ የሆኑ አሰራሮችን በመለየትና የመከላከያ ስትራቴጂ በማውጣት የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባርን በተጨባጭ ለመታገል ተቋሙ እያደረገ ያለውን ጥረት ምን እንደሚመስል የተቋሙ አመራሮች እንዲያብራሩ በቋሚ ኮሚቴው ተጠይቀዋል፡፡
የኦዲት ሪፖርቱን መሠረት አድረጎ በቀረቡት ጥቄዎች ዙሪያ የኤጀንሲው አመራሮች ምላሽ የሰጡ ሲሆን የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐብታሙ ሲሳይ ኤጀንሲው የኦዲት ግኝቱን መሠረት አድርጎ የሰራቸውን ሥራዎች ሲያስረዱ ኤጀንሲው ከቤት ደንበኞች ጋር በየዓመቱ ውል መዋዋል እንዳለበትና ከዚህ በፊት የመኖሪያ ቤት ከኪራይ ነፃ የሚያገኙ ደንበኞች በየዓመቱ ውል መታደስ እንዳለበት በመታመኑ የውል ሰነድ እንዲዘጋጅ መደረጉንና ውል የመዋዋል ስራ በክልል ከተሞች ሳይቀር እየተከናወነ እንደሚገኝ፣ ካርታ ያልነበራቸውን ቤቶች ካርታ እንዲዘጋጅላቸው ከ10ሩም ክፍለ ከተሞች ጋር በመነጋገር እየተሠራ እንደሚገኝ እና የንብረቶች ምዝገባም በሁሉም ክፍለ ከተሞች መጀመሩን ገልፀዋል፡፡
ውዝፍ ተሰብሳቢ ኪራይን በተመለከተም በ2003 ዓ.ም ተደርጎ በነበረው የኦዲት ግኝት 149.6 ሚሊዮን ገደማ ያልተሰበሰበ ውዝፍ እንደነበረና ከዚህ ውስጥም ኤጀንሲው ወደ 50.6 ሚሊዮን የሚሆነውን ገንዘብ እንዲሰበሰብ ማድረጉንና ወደ 98.9 ሚሊዮን ብር የሚገመተው አለመሰብሰቡን ገልፀው ከነዚህ ካልተሰበሰቡ ገንዘቦች ውስጥ በተለይም ልዩ ቅርንጫፍ ተብለው የሚታወቁት ኢምባሲዎችና ዲፕሎማቶች ላይ ያለውን ተሰብሳቢ ሂሳብ በቀላሉ ለመሰብሰብ ኤጀንሲው መቸገሩንና ይህን ችግር ለዘለቄታው እልባት ለመስጠት በምክትል ዋና ዳይሬክተር የሚመራ ኮሚቴ በማዋቀር ሒሳቡ እየተሠራ እንደሚገኝና ለመንግስት በማቅረብ ውሳኔ እንዲሠጥበት ለማድረግ ኤጀንሲው በሂደት ላይ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል አቶ ሐብታሙ ሲገልፁ ከባለሙያ ማነስ ጋር በተያያዘ መደረግ የነበረበት ክትትል በሁሉም ቤቶች ላይ እየተደረገ አለመሆኑን፣ የጥገናና እድሳት ሥራዎች በተመለከተም ኤጀንሲው በዋናነት የማደስ ኃላፊነት ያለው ትላልቅ ህንፃዎችን ቢሆንም ማደስ እንዳልቻለ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው የተቀመጡ የኤጀንሲው ንብረቶችን በጨረታ የመሸጥ ሥራ መሰራቱን፣ የቤቶች መረጃ አያያዝ ችግርን ለመቅረፍ ከኢንሳ /ከመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ/ ጋር በመነጋገር 75% የሚሆን የኔትወርክ ዝርጋታ ሥራ ማከናወናቸውንና በመላው አገሪቱ በአጠቃላይ ወደ 15ሺ የሚሆኑ ቤቶችን መረጃ ወደ መረጃ ቋት የማስገባት ሥራ እያከናወኑ እንደሚገኙ እንዲሁም ኤጀንሲው ቤት የመገንባት ስልጣን በአዋጅ ቢሰጠውም ቤቶቹን መገንባት ባለመፈቀዱ የተገልጋዮችን ፍላጎት በሚፈለገው ደረጃ ለማርካት እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡
አቶ ሙደር ሰማን የኢጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር በበኩላቸው የኦዲት ሪፖርቱን መሠረት አድረገው በዝርዝር ወደሥራ መግባታቸውና ያልተሰበሰበ ውዝፍ ሒሳብ በኦዲቱ ግኝቱ ከተጠቀሰው በላይ እንደሆነ ገልፀው መፍትሔ ሊሰጠት ከፍተኛ ርብርብ ላይ መሆናቸውንና ከንብረት አወጋገድ ጋር ተያይዞ በ19 መጋዘኞች ይገኝ የነበረውን ንብረት በማስወገድ ረገድ ከፍተኛ ሥራ መሠራቱንና በተለይም ብረት ነክ የሆኑትን በሙሉ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ሲያስወግዱ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ አባላት ተጨማሪ ማብራሪያ ያስፈልጋል ባሏቸው ጉዳዮች ላይ ጥያቄና አስተያየት የሰጡ ሲሆን ተቋሙ በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ያለበትን ችግር እንዴት ሊፈታ እንዳሰበ፣ የኤጀንሲው ቤቶች ላይ የሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር ዝቅተኛ መሆኑን ተረድቶ እየሰራ ስላለው ሥራ፣ ኤጀንሲው በስሩ የሚከናወኑ ግንባታዎችን ስለሚከታተልበት መንገድ፣ በኪራይ ቤቶች ኤጀንሲ ነዋሪዎችን ህጋዊነት የሚከታተሉበት ሥርዓት ስለመኖሩ፣ በአዲስ አበባ የራሳቸው መኖሪያ ቤት ኖሯቸው በተጨማሪ ከኤጀንሲው ቤት የወሰዱ አካላትን ስለሚቆጣጠርበት አሠራር እንዲያብራራ የጠየቁ ሲሆን በአሠራሩም ኤጀንሲው ቤት ማደስ ላይ የሚከተለው መንገድ በመፈተሽ ነዋሪው በራሱ የሚያድስበትን የእድሳት ፈቃድ በቀላሉ የሚሰጥበት አሰራር ሊኖረው እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
አቶ ሐብታሙም በተጨማሪ በተነሱት ጥያቄዎቸችና ሃሰቦች ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ አስካሁን ባላቸው አሠራር የመንግስት ቤት ነዋሪዎች ጥፋት አጥፍተው በሚገኙበት ወቅት ከቤቱ እንዲወጡ ከማድረግ ያለፈ ሌላ የሚወሰድ እርምጃ አለመኖሩን፤ የኤጀንሲውን ቤቶች ጥገና በውጭ አካል (Outsource) እንዲሠሩ ሲደረግ ችግር እያጋጠመ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ እንደሚገኙ፣ ልዩ ጥገናን በተመለከተም አሠራራቸውን በመፈተሽ እንደሚያስተካክሉ፤ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትን ለመቅረፍ የተቀናጀ የሙስና መከላከያ ሰነድ በማዘጋጀት ለፕሮሰስ ካውንስል መቅረቡንና እደሳን በተመለከተ ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጠውን ሃሳብ እንደግብዓት በመውሰድ የሚያስተካክሉ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ አቶ ሙደር ሰማን ለተነሱት ተጨማሪ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የውል እደሳን በተመለከተ መመሪያዎችን ማሻሻል እንደሚያስፈልግና የማስተካከያ ሥራ እንደሚሠሩ፤ የመረጃ አያያዝ ሥርዓታቸውን ለማሻሻል ትኩረት ሰጥተው በቀጣይ እንደሚሠሩ፤ ቤቶች ኤጀንሲ ሥር ያሉትን ቤቶች በአግባቡ ቆጠራ በማካሄድ ምን ያህል ቤትና ህጋዊ ተከራይ እንዳለ በማወቅ በዳታ ሲስተም ለመያዝ እንደሚሠሩ፣ በየቦታው የሚገኙ ንብረቶችን በተመለከተም ከዚህ በኋላ አጀንዳ ሆኖ ሊቀርብ በማይችልበት ደረጃ መፍትሔ ለመስጠት እንደሚሠሩ ገልፀው ላለፉት ዓመታት ኢጀንሲው ቤት እንዳይገነባ መከልከሉን በመግለፅ ኢጀንሲው የራሱን ቤቶች መገንባት የሚችልበት አሠራር ቢፈቀድለት አሁን ያለውን የቤት ችግር ከመቅረፍ ባለፈ ለመንግስት ሠራተኛው ቤት ማዳረስ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚፈጠር አስረድተዋል፡፡
ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የፌዴራል ዋና ኦዲተር በመጨረሻ በሰጡት አስተያየት የቤቶችን ሁኔታ በተመለከተ ግልፅ የሆነ ሥርዓት ሊዘረጋ እንደሚገባ፤ የቤቶች ጥገናን በተመለከተም ግልፅ የሆነ ስታንዳርድ ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግ፤ ንብረት ተከማችቶባቸው የነበሩ 19 መጋዘኖችን ንብረቶቹን አስወግዶ ባዷቸውን ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን ለሌላ አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ፤ የተሰብሳቢ ሒሳብን በተመለከተ ለብዙ አመታት ሲዘዋወሩ የነበሩና መፍትሔ ያላገኙትን ከመዝገብ ከማሰረዝ ባሻገር አሁንም ቢሆን መሰብሰብ ያለባቸው ተሰብሳቢ ሒሳቦች ተለይተው መሰብሰብ እንደሚገባቸው እና የመረጃ ሥርዓት ማጠናከር ላይ እየተሰራ ያለው ሥራ በምልዓት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አምባሳደር መስፍን ቸርነት እንደገለፁት ኤጀንሲው ያለበትን ችግር ተረድቶ ለማስተካከል የጀመረው ተግባር በጥሩ ጎኑ እንደሚታይ፤ የኦዲት ግኙቱን እንደ አንድ የለውጥ ግብዓት ወስዶ ችግሮችን ለማስተካከል የተኬደባቸው ርቀቶች ጥሩ እንደሆኑና ከንብረት ማስወገድ ጋር በተያያዘ ኤጀንሲው የሠራው ሥራ የሚያስመሰገነው እንደሆነ በጠንካራ ጎን አንስተዋል፡፡
በሊላ በኩል ሰብሳቢው የኤጀንሲው የቤቶች አስተዳደር ሥርዓት በቴክኖሎጂ የታገዘ ሊሆን እንደሚያሻው፤ ተቋሙ ከተመሠረተ ጀምሮ ሲንከባለል የመጣ ተሰብሳቢ ሒሳብን እልባት እንዲያገኝ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ፤ የቤቶች አስተዳደር ፖሊሲና ስትራቴጂዎች ቀረፃ በፍጥነት ተጠናቆ ወደሥራ ሊገባ እንደሚገባ፤ የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓቱ ወደ ላቀ ደረጃ ማሳደግ እንደሚያስፈልግና የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መንስኤዎችን ለመፍታት በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ፤ በመንግስት ቤት ውስጥ የተለያዩ ሥራዎችን በሚሠሩ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ፤ በአዲስ አበባ መኖሪያ ቤት ኖሯቸው ከኤጀንሲው ቤት የወሰዱ አካላት ላይ ቁጥጥር በማድረግ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚያስፈልግ፤ የሰው ሃብት አደረጃጀት ላይ ትኩረት በማድረግ ማስተካከል እንደሚያስፈልግ፤ ከቋሚ ኮሚቴውና ከሌሎች ባለድርሻ አካላትን ጋር ያለው ቅንጅት ይበልጥ ሊጠናከር እንደሚገባ እና ኤጀንሲው ያካሄዳቸውን በርካታ ጥናቶች ወደ ተግባር መለወጥ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡