News

የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት አሰጣጥ በበቂ የግንዛቤ ማስጨበጥና ቅንጅታዊ አሠራሮች የበለጠ መጠናከር እንዳለበት ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከ2009 በጀት ዓመት አስከ 2012 የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ድረስ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ባቀረበው የካፒታል ዕቃዎች ኪራይ የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ውጤታማነት ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ያካሄደውን የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት መሠረት ያደረገ ውይይት ተካሄደ፡፡

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አማካይነት መጋቢት 22 ቀን 2013 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ የባንኩ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተው በኦዲት ወቅት የተከለሱ ማስረጃዎችንና የናሙና ጥናቶችን መሰረት በማድረግ ተዘጋጅቶ በቀረበው የኦዲት ሪፖርት መነሻነት ከቋሚ ኮሚቴው ለቀረቡ ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት አዲስ አሠራር እንደመሆኑ በተገልጋይ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም በባለድርሻ አካላትና በባንኩ ሠራተኞችም ጭምር ስለ አሰራሩ በቂ ግንዛቤ ያለመኖሩ፣ በቅንጅት አሠራር ክፍተት ምክንያት አገልግሎቱን ሊያገኙ የሚገባቸው ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ኢንተርፕራይዞችን በመመልመል ሂደት ችግር መኖሩና ወጥ የሆነ የአሠራር ፖሊሲ ባለመኖሩ በተገልጋዮች ዘንድ ቅሬታ መፈጠሩ፣ የካፒታል ዕቃዎች ለኢንተርፕራይዞቹ ከመቅረባቸው በፊት በሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊ የሆኑ የመሰረተ ልማቶች መዘጋጀታቸውን የማረጋገጥ ክፍተት መኖሩ እና ከሚቀርቡት  ማሽነሪዎች ውስጥ በዓይነት ያልተለዩና መስፈርት የሌላቸው እንዲሁም ውስብስብ፣ ትልልቅና ለመትከል አስቸጋሪ የሆኑ በመኖራቸው በተለያዩ ምክንያቶች ማሽነሪዎቹን ለሶስተኛ ወገን ማስተላለፍ ቢፈለግ ከቦታ ቦታ በቀላሉ ማንቀሳቀስ የማይቻል መሆኑ በቋሚ ኮሚቴው በቀረቡ ጥያቄዎች ውስጥ እንደ ክፍተት ተነስተዋል፡፡

በተጨማሪም ለኢንተርፕራይዞች የሚቀርቡ የካፒታል ዕቃዎች ምዝገባ በበሚመለከታቸው አካላት ስም በአግባቡ ሳይመዘገቡ ለተከራዮች የሚተላለፉ መሆኑ፣ ከውጭ ለሚገቡ ዕቃዎች አስፈላጊውን የጉምሩክ ሰነድ በቅድሚያ ያለማዘጋጀትና በዚህም ዕቃዎችን በወቅቱ ከወደብ የማንሳት ክፍተት በመኖሩ ተገልጋዮች ለተጨማሪ ወጪና እንግልት መዳረጋቸው፣ የዋና ብድርና የወለድ ክፍያዎች በወቅቱ ያለመሰብሰብ ችግር መኖሩ፣ ባንኩ የግዥ መመሪያ የሌለው በመሆኑ የግዢ መመሪያን ባልተከተለ ሁኔታ ግዥዎች መፈጸማቸውና የመድህን ዋስትና ያልተገባላቸው ዕቃዎች መኖራቸው እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት የጎላ ክፍተት መኖሩን የኦዲት ግኝቱ እንደሚያሳይ በቀረቡት ጥያቄዎች አማካይነት ተጠቅሷል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶ.ር ዮሀንስ አያሌው ለቀረቡት ጥያቄዎች ማብራሪያና ምላሽ የሰጡ ሲሆን በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ሪፖርት መሠረት የቀረቡት አብዛኞቹ ጉዳዮች ትክክለኛና ለወደፊት የባንኩ አሠራርም ጠቃሚ ግብአት የሚሆኑ ናቸው ብለዋል፡፡ አክለውም ባንኩ ቀደም ሲል በነበረበት ብልሹ አሠራር በርካታ ችግሮች የነበሩበት በመሆኑ ከሪፎርሙ በኋላ በአዲስ አመራርና ቦርድ ችግሮቹን ለመቅረፍ የሚያስችሉ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው ክፍተት የነበረበት መሆኑን የጠቆሙት ዶ.ር ዮሀንስ በአሁኑ ወቅት ክልሎችን ጨምሮ ለተለያዩ ባለድርሻ አካላትና ለተገልጋዮች እንዲሁም ለባንኩ ሰራተኞች ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ለተውጣጡ 2500 አዳዲስና ነባር ኢንተርፕራይዞች በአደረጃጀት፣ በፋይናንስ፣ በአስተዳደርና በሌሎች ተዛማጅ የባንኩ አሠራሮች ዙሪያ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆናቸውን በማሳያነት የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ ኢንተርፕራይዞች የባንኩን አገልግሎት የሚያገኙት በአነስተኛ ወለድና ከማሽነሪያቸው ውጪ ሌላ ማስያዣና ዋስትና ሳይሳፈለጋቸው መሆኑንም ግንዛቤ እየተሰጠ እንደሚገኝ ጨምረው አብራርተዋል፡፡

ብቁ የሆኑ ኢንተርፕራይዞችን በመመልመል ሂደት ክፍተት እንደነበረና ወጥ የሆነ የአሠራር ፖሊሲ ያልነበረ መሆኑን በመጥቀስም በአሁኑ ወቅት ከስልጠና ስራው ጋር ይኸው ተግባር እየተከናወነ መሆኑንና የፖሊሲ ክለሳ ስራ መሰራቱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

በመሰረተ ልማት አቅርቦት ረገድ ኢንተርፕራይዞቹ ከሚገኙባቸው የአስተዳደር አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ የመስራት ችግር እንደነበርና በዚህም የግንዛቤ ክፍተት እንደነበረ የጠቆሙት ዶ.ር ዮሀንስ የካፒታል ዕቃዎቹ ከመቅረባቸው በፊት መሰረተ ልማቶች በሚመለከታቸው አካላት የተሟሉ ስለመሆናቸው ቴክኒካዊ ክትትል በማድረግ ረገድ ባንኩ ክፍተት የነበረበት ቢሆንም በአሁኑ ወቅት የክትትልና ቁጥጥር ስራውን ለማጠናከር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ከማሽነሪዎች ተከላ፣ ውስብስብነትና ከባድነት አንጻር  ከቦታ ቦታ አንቀሳቅሶ ለሶስተኛ ወገን ለማስተላለፍ የነበረውን ችግር በመንግስት መጠለያ ሼዶች ያሉትን ከነመጠለያ ሼዳቸው እንዲሁም ፈቃደኛ በሆኑ የግል ቤቶች ያሉት ከነቤቱ ለሶስተኛ ወገን በማስተላለፍ ለመፍታትና ወደፊት ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ በማይመች መልኩ የማሽነሪዎች ተከላ እንደማይካሄድ ጨምረው አብራርተዋል፡፡

የካፒታል ዕቃዎች ምዝገባን በተመለከተም የትና በማን ስም እንደሚመዘገብ የግንዛቤ ክፍተት እንደነበር የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮዎች ጋር በጋራ እየሰራን በመሆኑ ችግሩ ይስተካከላል ብለዋል፡፡

የሰነዶች ቅድመ ዝግጅት የተጓተተ ስለነበር ከውጪ ተገዝተው የሚመጡ ዕቃዎች ያላግባብ በወደብ ላይ እንደሚቆዩና በዚህም ተገልጋዮች ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት የሚዳረጉበት አሠራር እንደነበር ጨምረው ያስረዱት ዶ.ር ዮሀንስ ይህም ቀደም ሲል ከነበረው የባንኩ ብልሹ አሠራር የተፈጠረ መሆኑን ገልጸው ይህንን ችግር የሪፎርሙ አንድ ጉዳይ በማድረግ ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል በነበረው የባንኩ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ወጥ የሆነ አሠራር ያልነበረና የባንኩ ሰራተኞችም ጭምር የተሳተፉባቸው የተንዛዙና ብልሹ አሰራሮች የነበሩ መሆኑን የጠቆሙት ፕሬዚዳንቱ ከብልሹ አሰራሮች ጋር ግንኙነት በነበራቸው ሰራተኞች ላይ እርምጃ የመውሰድ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል፡፡ አክለውም በተንዛዛ እንዲሁም በብልሹ አሠራርና በግንዛቤ ጉድለት ምክንያት ዋና ብድርና ወለድን በወቅቱ ያለመሰብሰብ ችግር በባንኩ አሠራር ላይ ሲታይ የነበረ መሆኑን በመጥቀስ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ በተካሄደው የሪፎርምና የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ እንዲሁም በተደረገው ከፍተኛ ጥረት ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ መሰበሰቡን በዋቤነት አንስተው የተበላሸ የብድር መጠንም በፊት ከነበረበት ዝቅ እንዲል መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

ዕቃዎችን ለመግዛት በግዥ መመሪያ መመራት አስፈላጊ መሆኑንና ከመመሪያ ውጪ የተፈጸሙት ግዥዎችም አግባብ ያለመሆናቸውን የገለጹት የባንኩ ፕሬዚዳንት ቀደም ሲል የግዥ መመሪያ ያልነበረ  በመሆኑ አዲስ መመሪያ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል፡፡ የመድህን ዋስትና ያልተገባላቸው የካፒታል ዕቃዎች በመድን ዋስትና እንዲታቀፉ ለማድረግም ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑንና ለዚህም የክትትልና የቁጥጥር ስራው በህጋዊ አግባብ እንዲጠናከር ለማድረግ የባንኩን ቅርንጫፎች ደረጃ በማሳደግና የቅርብ ክትትል በማድረግ ችግሮቹ እንደሚፈቱ አመላክተዋል፡፡

በተለያዩ የባንኩ አሠራሮች ዙሪያ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት ሂደቱን ለማሻሻል ከክልሎችም ሆነ ከከተማ መስተደዳሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ኮሚቴዎች ተቋቁመው የተጠናከረ የትብብር ስራ ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ዶ.ር ዮሀንስ የኦዲት ሪፖርቱን መሰረት በማድረግ የድርጊት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ያለመላኩና የተወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎች ሪፖርት ያለመደረጋቸው ክፍተት በመሆናቸው ወደፊት የሚስተካከሉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው የክዋኔ ኦዲት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክብርት ወ/ሮ ወይንሸት ገለሶ በበኩላቸው ባንኩ የነበሩበትን ችግሮች በሪፎርም ውስጥ አካቶ ለመቅረፍ እያደረገ ያለው ጥረት በበጎ መልኩ የሚታይና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቅሰው ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በወቅቱ መላክ የነበረባቸው የድርጊት መርሀ ግብርና የማስተካከያ እርምጃ ሪፖርቶች ያለመላካቸው ክፍተት በመሆኑ ወደፊት መስተካከል የሚገባው ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ባንኩ እያደረገ ያለው የሪፎርም ስራ ፈጣን ለውጥ ሊያመጣ የሚችል መሆን እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ም/ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የባንኩ የሪፎርም እንቅስቃሴና ለለውጥ ያለው ፍላጎት አበረታች መሆኑን ገልጸው የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት በሀገሪቱ አዲስ አሰራር እንደመሆኑና የታዩት አብዛኞቹ ክፍተቶችም ከግንዛቤና ከሌሎች አካላት ጋር ተቀናጅቶ ባለመስራት የተፈጠሩ በመሆናቸው በአሠራሩ ዙሪያ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጥና ተቀናጅቶ የመስራት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡

የባንኩ የክትትልና የቁጥጥር ስራ በሚፈለገው ደረጃ ላይ ያለመሆኑን የኦዲት ግኝቱ የሚያሳይ መሆኑን የገለጹት ም/ዋና ኦዲተሯ ኢንተርፕራይዞችን ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ ለማሸጋገርና ባንኩን ወጥ በሆነ ፖሊሲና የአሠራር መመሪያ ለመምራት ያለው ዝግጁነት የበለጠ መጠናከር እንደሚኖርበት ጠቁመዋል፡፡ ማሽነሪዎች የሚቀመጡበትና የሚተከሉበት ቦታና የመሰረተ ልማት ያለመሟላት ችግሮች አገልግሎት አሰጣጡን ዋጋ የሚያሳጡ በመሆናቸው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር በመስራት በአፋጣኝ መፍትሔ ሊፈለግላቸው እንደሚገባ ጨምረው የገለጹት ክብርት ወ/ሮ መሠረት በንብረት አመዘጋገብ እና አስፈላጊ ሰነዶች ቀድመው ባለመዘጋጀታቸው ዕቃዎች በወደብ ላይ ያላግባብ በመቀመጣቸው በተገልጋዮች ላይ የተፈጠሩት ተጨማሪ ወጪዎችና እንግልቶችም በባንኩ አሠራር ላይ አመኔታን የሚያሳጡ በመሆናቸው ጊዜ ሳይሰጣቸው መታረም ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡ ዋና ብድርንና ወለድን በጊዜ ያለመሰብሰብ እና ከግዥ መመሪያ ውጪ ግዥ መፈጸም የመንግስትንና የህዝብን ሀብት የሚያባክን ከመሆኑም ባሻገር ለህገ ወጥ አሠራር በር የሚከፍት በመሆኑ ሊወገድ እንደሚገባው አሳስበው የመድህን ዋስትና ያልተገባላቸው ንብረቶችም በሽፋኑ እንዲታቀፉና በዋስትናው የታቀፉትም ቢሆኑ ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ባንኩ በቂ መረጃ ሊኖረው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሐመድ የሱፍ ባንኩ ያሉበትን ችግሮች ለማስተካከል ጥረት እያደረገ መሆኑን በቀረበው ማብራሪያና ምላሽ ለመረዳት የተቻለ መሆኑን ጠቅሰው ችግሮቹን በዳሰሳ ጥናት በማስደገፍ ለመቅረፍ ቀጣይ ጥረቶች ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ የባንኩን ዓላማ ለማሳካትም በተለይ ከክልሎች ጋር ያለውን አሠራር የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባ አክለው ገልጸዋል፡፡ አሠራሩ አዲስ እንደመሆኑ የተለያዩ ተሞክሮዎችን በመውሰድ ከሀገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማሳለጥ የባንኩን የሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት ማጠናከር እንደሚገባ በማጠቃለያ ንግግራቸው የጠቀሱት ሰብሳቢው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በየጊዜው የሚሰጠውን አስተያየት በግብአትነት በመውሰድ የባንኩን አሠራር ማጎልበት እንደሚገባ ጨምረው አሳስበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከ100 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው የሀገሪቱ ብቸኛ የፖሊሲ ባንክ መሆኑና የተቋቋመበት ዓላማም ለሀገሪቱ ልማት ወሳኝ ድርሻ ያላቸውን የግብርናና የኢንዱስትሪ ዘርፎች ለመደገፍና ለማሳደግ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *