News

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፌዴራል ዋና ኦዲተር የቀድሞ አመራሮች ላበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅና ሰጠ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ የስራ ዘመናቸውን ላጠናቀቁት የቀድሞው የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶና ለድጋፍ ዘርፍ ምክትል ዋና አዲተር ክብርት ወ/ሮ ባዩሽ ተስፋዬ ባደረገው የሽኝት ፕሮግራም ላበረከቱት አስተዋፅኦ እውቅና ሰጠ፡፡

ምክር ቤቱ ሰኔ 30/2013 ዓ.ም በሸራተን ሆቴል ባደረገው የሽኝት የእራት ግብዣ ወቅት የምክር ቤቱ አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የምክር ቤቱ ምክትል አፈጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ፣ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ሰብሳቢዎች እንዲሁም የምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ዶ/ር ምስራቅ መኮንን ተገኝተዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ታገሰ ጫፎ በወቅቱ ባደረጉት ንግግር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶና ክብርት ወ/ሮ ባዩሽ ተስፋዬ በመንግስት የተጣለባቸውን ሀላፊነት በጠንካራ የስራ ዲሲፕሊን፣ በጥንቃቄና በታታሪት በመወጣት ተቋሙን በመገንባት እንዲሁም መ/ቤቱ በመንግስት የተሰጠውን ተልዕኮ በአግባቡ በመወጣት በምክር ቤቱና በህዝብ ዘንድ የተመሰከረለት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ለሰጡት አመራር ምክር ቤቱ ያለውን ክብር ለመግለጽ የሽኝት ፕሮግራሙ በተለየ ሁኔታ እንዲዘጋጅ መደረጉን ገልጸው ሁለቱን የቀድሞ

አመራሮች በራሳቸውና በምክር ቤቱ ስም አመስግነዋል፡፡

ክቡር አቶ ገመቹና ክብርት ወ/ሮ ባዩሽ ምክር ቤቱ ለስራቸው ለሰጣቸው እውቅና ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

ክቡር አቶ ገመቹ ባደረጉት ንግግር የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ላከናወነው ስራና ለተገኘው ውጤት የመ/ቤቱ ስራ ሀላፊዎችና ሰራተኞች ከፍተኛ ሚና የነበራቸው በመሆኑ በምክር ቤቱ የተሰጣቸው እውቅናና ክብር ለመ/ቤቱ የስራ ሀላፊዎችና አመራሮችም ጭምር የተሰጠ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ክቡር አቶ ገመቹ ምክር ቤቱ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን ጨምሮ ተጠሪ የሆኑለትን ሌሎች የዲሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከርና ስራቸውን በነጻነትና በገለልተኝነት እንዲሰሩ ማገዝ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡

በመጨረሻም ክቡር አቶ ገመቹ በስራ ዘመናቸው ወቅት እገዛ ላደረጉላቸው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለሌሎች አካላት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

 

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *