አነስተኛ ገቢ ላላቸው ሴት ሰራተኞች መሰረታዊ የንግድ ክህሎት ስልጠና ተሰጠ
በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት አነስተኛ ገቢ ላላቸው የመ/ቤቱ ሴት ሰራተኞች መሰረታዊ የንግድ ክህሎት ስልጠና ከነሀሴ 30 አስከ ጷጉሜ 04 2008 ዓ.ም ድረስ ተሰጠ፡፡
ስልጠናው ከራስ አገዝ ሴቶች ድርጅት ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በጽዳት፣ በመልዕክት ስራና ሌሎች የስራ ዘርፎች የተሰማሩ 30 ሴት ሰራተኞች ተካፍለዋል፡፡
በስልጠናው መክፈቻ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ስልጠናው የመስሪያ ቤቱን ሴቶች አቅም በመገንባት የስራ አፈጻጸማቸውን ለማሳደግ እና በተጨማሪም ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማሳደግ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው ሰልጣኞቹ እድሉን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት አሳስበዋል፡፡
በራስ አገዝ ሴቶች ድርጅት በኩል ስልጠናውን የሰጡት ወ/ሮ ወርቅነሽ ልንገርህ ሰራተኞች ጥቃቅን ንግድን ለማከናወን የሚረዳ መሰረታዊ የንግድ ስራ ፈጠራ ክህሎትን እንዲጨብጡ ማድረግ፣ በንግድ ስራ ውስጥ ተሰማርተው ያሉትም ንግዳቸውን እንዲመረምሩና ያሉ ችግሮችና መልካም እድሎችን እንሚመለከቱ ማስቻል እንዲሁም ስለንግድ ስራ አመራር እርስ በርስ የልምድ ልውውጥ ማድረግ የስልጠናው አላማዎች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ስልጠናው ሰራተኞቹ በተለያዩ ንግድ ነክ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ መሰረታዊ ግንዛቤ እንዲያገኙ ያስቻለ ሲሆን የራስ ሀብትን በመለየት ኑሮን ለማሻሻል ስለሚቻልበት መንገድ፣ የንግድ ስራን ለማከናወን ስለሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች፣ ስለ ንግድ ምንነት፣ አይነቶች፣ ዑደት፣ እቅድ፣ ስለ ገበያና ግብይት፣ እንዲሁም የንግድ ሀሳብን ስለማመንጨት፣ ስለቁጠባና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች እውቀት እንዲጨብጡ አድርጓል፡፡
በስልጠናው ማብቂያ ላይ ሰራተኞቹ የንግድ ስራን እንዴት ማከናወንና ኢኮኖሚያዊ ደረጃቸውን ማሻሻል እንደሚችሉ ግንዛቤ እንዳገኙ ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት በስልጠናው የመዝጊያ ስነስርአት ላይ ለሰልጣኞች የምስክር ወረቀት በሰጡበት ወቅት ሰራተኞቹ ከስልጠናው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር መለወጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡ በወቅቱ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሙሉ ጥሩነህ ስልጠናው ምን ውጤት እንዳመጣ በቀጣይ ክትትል እንደሚደረግ የገለጹ ሲሆን ሰራተኞች ተግባብተው በመስራት፣ ሀብታቸው የሆነውን ጊዜን በአግባቡ በመጠቀም እንዲሁም በራስ አገዝ የሴቶች ድርጅት የተመቻቹ የብድርና ቁጠባ እድሎችን በመጠቀም ህይወታቸውን ማሻሻል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ ዳይሬክተራ አክለውም ለራስ አገዝ ሴቶች ድርጅትና ለአሰልጣኟ ለወ/ሮ ወርቅነሽ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
የራስ አገዝ የሴቶች ድርጅት የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ደረጃ እንዲሻሻል ከንግድ ስራ ጋር የተያያዙ ስልጠናዎችን በመስጠት እንዲሁም የብድርና ቁጠባ እድሎችን በማመቻቸት ዙርያ የሚሰራ ተቋም ሲሆን ስልጠናውን ለፌሬራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሰራተኞች በነጻ ሰጥቷል፡፡