News

ተቋሙ በተጣለበት ከባድ ኃላፊነትና በሚያንቀሳቅሰው ግዙፍ ሀብት ልክ ለሀብት አስተዳደሩ ትኩረት መስጠት እንዳለበት ተገለጸ

የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴር ከተጣለበት ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነትና ከሚያንቀሳቅሰው ግዙፍ ሀብት አንፃር ለሀብት አስተዳደር የሚሠጠውን ትኩረት ማሳደግ እንዳለበት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በቀድሞው የግብርና ሚኒስቴር በዋናው መ/ቤትና በግብርና ቴክኒክ ሙያ ትምህርትና ስልጠና ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ በገዋኔ ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ እና በሚዛን ግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጅ ላይ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በተከናወነው የ2007 በጀት ዓመት የፋይናንሺያል ኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ስብሰባ ግንቦት 09 ቀን 2009 ዓ.ም አካሂዷል፡፡

በሚኒስቴር መ/ቤቱ እና በተጠሪ ተቋማቱ ላይ የተከናወነው ኦዲት ተቋማቱ በፋይናንስ እና በንብረት አስተዳደር ላይ በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው አሳይቷል፡፡

በፋይናንስ ረገድ በተሰብሳቢ ፣ በተከፋይና በወጪ ሂሳብ፤ በሂሳብ አያያዝ፣ አመዘጋገብ፣ በገንዘብ አከፋፈልና በበጀት አጠቃቀም ላይ ችግሮች የታዩ ሲሆን በንብረት አስተዳደር ረገድም በንብረት ምዝገባ፣ አያያዝና አወጋገድ ላይ ድክመቶች ታይተዋል፡፡

በተሰብሳቢ ሂሳብ ረገድ መወራረድ ወይም መሰብሰብ ያለበት ገንዘብ በሚኒስቴር መ/ቤቱ በድምሩ 112,130,642.18 ብር፣ በማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ከ1996 ጀምሮ ያልተሰበሰበ ብር 75,882,512.81፣ በገዋኔ ግ/ቴ/ሙ/ት/ስ/ኮሌጅ ብር 1,810,631.70 እና በሚዛን ግ/ቴ/ሙ/ት/ስ/ኮሌጅ ከውስጥ ገቢና ከካፒታል በጀት በድምሩ ብር 1,378,267.02 እንዳለ ሪፖርቱ አሳይቷል፡፡

OFAG Ethiopian (2)በተከፋይ ሂሳብ በኩልም በዋናው መ/ቤት በሁለት የሂሳብ መደቦች ያልተከፈለ ብር 6,542,970.81 እና በማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ብር 22,909,946.60 እንዳለ ታይቷል፡፡ በወጪ ሂሳብ ረገድ በሁሉም ተቋማት ውስጥ ከወጪ አፈፃፀም ወይም የወጪ ማስረጃ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ችግሮች እንዳሉም ኦዲቱ አመልክቷል፡፡ ከዚህ ሌላም ከሂሳብ አያያዝ፣ አመዘጋገብና አከፋፈል ጋር የተያያዙ ስህተቶች በተቋማቱ እንዳሉ ኦዲቱ አሳይቷል፡፡

በበጀት አጠቃቀም በኩልም ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከመደበኛና ከካፒታል በጀት ብር 20,459,820.59፣ ማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ከካፒታል በጀት ብር 5,084,628.84 ገዋኔ ግ/ቴ/ሙ/ት/ስ/ኮሌጅ ብር 6,229,906.90 እንዲሁም ሚዛን ግ/ቴ/ሙ/ት/ስ/ኮሌጅ 5,535,588.11 ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ያሳየ ሲሆን ገዋኔና ሚዛን ግ/ቴ/ሙ/ት/ስ/ኮሌጆች ለሂሳብ መደቦች ከተደለደለው በላይ በጀት የሚመለከተውን አካል ሳያስፈቅዱ እንደተጠቀሙ አመልክቷል፡፡

ከንብረት አስተዳደር ጋር በተያያዘ መጠነኛ ችግር ከታየበት ከማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ በስተቀር ሁሉም ተቋማት በንብረት አያያዝ፣ አስተዳደርና አወጋገዳቸው የተለያዩ ችግሮች እንዳሉባቸው ሪፖርቱ በዝርዝር አመልክቷል፡፡

በተጨማሪም በገዋኔና በሚዛን ግ/ቴ/ሙ/ት/ስ/ኮሌጆች የውስጥ ኦዲት በአንድ ሰው ብቻ የሚከናወን መሆኑና የውስጥ ኦዲት ሥራ ክፍሉ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ እንዳልሆነ ገልጿል፡፡

ከነዚህ ጉዳዮች በተጨማሪም የኦዲት ግኝቱ በየተቋማቱ ላይ የታዩ ሌሎች ድክመቶችን አሳይቷል፡፡

የሁሉም ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች በኦዲት ግኝቶቹ ላይ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ችግሮቹ የተከሰቱበትን ምክንያትና ከግኝቱ በኋላ የተወሰዱ እርምጃዎችን ገልጸዋል፡፡

በዋናነት ግብረ ሀይል በማቋቋም ጭምር ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦችን የማጣራት እንዲሁም ሰነዶችን የማወራረድና ተሰብሳቢ ገንዘቦችን የማስመለስ ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም በሚኒስቴር መ/ቤቱ በኩል 11.3 ሚሊዮን ብር በሰነድ መወራረዱና 964,730 ብር በጥሬ ገንዘብ ተመላሽ እንደተደረገ ተገልጻóል፡፡ የተከፋይ ሂሳብን ለማስተካልም ከ1994 ዓ.ም ጀምሮ ያለውን ሰነድ የሚያጣራ ግብረ ኃይል ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑ ተብራርቷል፡፡

በንብረት ማስወገድ በኩል እንደየተቋማቱ ሁኔታ የንብረት አመዘጋብና አያያዙን የማሻሻል፣ በራስ አቅም የሚወገዱ ንብረቶችን የማስወገድ፣ የሚወገዱና የማይወገዱOFAG Ethiopian (1) ንብረቶችን የመለየት፣ የሚወገዱ ንብረቶችን የማደራጀትና አደጋ የሚያደርሱትን ደህንነታቸው ተጠብቆ ለብቻ የማስቀመጥ ሥራዎች እንደተሰሩና በራስ አቅም የማይወገዱትንም ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ እንደሚገኝ ኃላፊዎቹ ገልፀዋል፡፡

የሥራ ኃላፊዎቹ አብዛኞቹ ችግሮች ከባለሙያዎች የልምድ እጥረትና ከሰው ኃይል እጥረት ጋር እንደመነጩ የገለጹ ሲሆን የሚዛን እና የገዋኔ ግ/ቴ/ሙ/ት/ስ/ኮሌጆች የውስጥ ኦዲት ባለሙያ ለማግኘት ያደረጉት ተደጋጋሚ ጥረት አለመሳካቱን ገልጸዋል፡፡የገዋኔ ግ/ቴ/ሙ/ት/ስ/ኮሌጅ የሥራ ኃላፊም ተቋሙ በአርብቶ አደር አካባቢ ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ የሰው ኃይል እጥረትና የአሰራር ችግሮች መፈጠሩን ገልፀው ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የሌሎች ተቋማት ኃላፊዎችም ሂሳቦችን ከማስተካከልና ከራስ አቅም ውጪ ከሚፈጸም የንብረት ማስወገድ ስራ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመሆን ለማስተካከል እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡

የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስትሩ ዶ/ር እያሱ አብርሃ በሰጡት አስተያየት አመራሩ ነባሩን ችግር እንደራሱ ችግር ወስዶ ፈጥኖ ለ.ማስተካከል በባለቤትነት ስሜት እየሰራ እንደሚገኝ፣ ተሰብሳቢ ሂሳብን በማስመለስ በኩል ያለውን ችግር ለመፍታት በአደረጃጀት ላይ አትኩሮ እየተሰራ እንዳለ፣ አመራሩ የፋይናንስ አስተዳደር ጉዳይን ትልቅ አጀንዳ አድርጎ እንደያዘና የተጠያቂነት አሰራርን አጠናክሮ እየሰራበት እንደሆነ፣ የንብረት አያያዙን ችግር ለመፍታትና ሁኔታውን ለማሻሻል የካይዘን አሰራርን ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን፣ የተጠሪ ተቋማቱን የኦዲት ሪፖርት በጋራ ገምግሞ አቅጣጫ መስጠቱን አስረድተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሰጡት አስተያየት ሚኒስቴር መ/ቤቱ ተጠሪ ተቋማቱን የሚመራበት ሁኔታና ከተቋማቱ ጋር ያለው የቅንጅት አሰራር ሰፊ ክፍተት ያለበትOFAG Ethiopian (3) መሆኑ፣ በኦዲት ግኝቱ ላይ በጋራ በዝርዝር ተወያይቶ ማሻሻያ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ፣ በንብረት ማስወገድ ላይ ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ ከማቅረብ ባለፈ ገፍቶ መሄድ እንደሚያስፈልግ፣ በቀደሙት ዓመታት ኦዲቶች የታዩ ግኝቶች አሁን ድረስ በተደጋጋሚ መታየታቸው ተቋሙን ለኦዲት ግኝት ትኩረት የማይሰጥና የተጠያቂነት አሰራርን በማስፈን በኩል ችግር ያለበት መ/ቤት  መሆኑ እንዲሁም አመራሩ የድርጊት መርሀግብሩን መሰረት አድርጎ የተሰሩና ያልተሰሩ ስራዎችን ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትና ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መላክ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

እንደዚሁም ተሰብሳቢ ሂሳቦችን ለማስመለስ የተጀመረው ሂደት ጥሩ ቢሆንም ረጅም ርቀት የሚቀረው በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው፣ የንብረት አስተዳደር መመሪያን በአግባቡ በመከተል ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚያሻ፣ የሚወገዱ የኬሚካሎችን ሁኔታ አጥንቶ ለሚመለከተው አካል አቅርቦ ውሳኔ ማሰጠት እንደሚገባ፣  ተቋሙ ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት የተጣለበት፣ ሰፊ ሀብት የሚያንቀሳቅስና ትልቅ በጀት የሚመደብለት በመሆኑ ይህንን ግዙፍ ሀብት በአግባቡ በማስተዳደር ላይ ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለበት፣ ለለውጥ ሠራዊት ግንባታ ትኩረት መሰጠት እንደሚኖርበት፣ የገዋኔ ግ/ቴ/ሙ/ት/ስ/ኮሌጅ ከሚገኝበት የአፋር ክልል ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የመንግሥትን ንብረትና በጀት እንዲሁም መመሪያዎችን መተግበር ላይ ተጽዕኖ ካጋጠመው ይህንን ለመፍታት ጥናት ማካሄድና መፍትሄ መፈለግ እንደሚገባው፣ የሰው ሃይል አቅርቦትና ብቃት ጉዳይን ለታዩት ችግሮች እንደ ምክንያት ማስቀመጥ ብቻውን ተገቢ አለመሆኑና መፍትሄ ማፈላለግ ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግ እንደዚሁም ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦችን ከስር ከስር ማጣራት እንደሚገባና ያለፈውን ከማስተካከል ጎን ለጎን በአሁኑ ወቅት ያለው –ም መስራት እንደሚያሻ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አስገንዝበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው ተቋማቱ የድርጊት መርሃ ግብር መላካቸውና እርምጃ ወስደንባቸዋል ያሏቸው ጉዳዮች በቀጣይ የሚጣሩ ቢሆንም እርምጃ መወሰዱ በመልካም ጎኑ እንደሚታይ ገልጸው ሚኒስቴር መ/ቤቱ ሂሳቡን በወቅቱ ዘግቶ ለኦዲት ማቅረብ ላይ ያለበትን ችግር ማስተካከል እንደሚገባው፣ በሰነድ እንደተወራረዱ የተገለጹት ሂሳቦች ማስረጃ እንደቀረበላቸው ማጣራት እንደሚያስፈልግ፣ ገንዘብ የማስመለሱ ሂደት ጥሩ በመሆኑ መቀጠል እንዳለበት፣ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ተከፋይ ሂሳቦቹ የማን እንደሆኑ ማጣራት እንደሚጠበቅበት፣ የተሰበሰበ ተጨማሪ እሴት ታክስና ዊዝሆልዲንግ ታክስን (VAT and withholding tax) በወቅቱ ገቢ ማድረግ እንደሚገባ እና በሂሳብ ምዝገባ ላይ አሁንም የሚታዩ ችግሮች ስላሉ ትኩረት እንደሚያሻው ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ከንብረት ጋር እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች አበረታች ቢሆኑም ብዙ ስራ እንደሚቀርና ከመንግሥት ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጋር ከመፃፃፍ ያለፈ ሥራ መስራት እንደሚገባ፣ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ኬሚካል የሚያስገባና ፈቃድ የሚሰጥ ዋነኛ ተቋም በመሆኑ በአወጋገዱ ዙሪያም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን መስራት እንዳለበት፣ የኦዲት ግኝቱ በናሙና በታዩት ተቋማት ላይ ብቻ የተከናወነ በመሆኑ ኦዲት ባልተደረጉት ላይም ግኝቱን አስፍቶ ማየት እንደሚገባ እንደዚሁም የኮሌጆቹን የውስጥ ኦዲት ክፍል ማጠናከርና የዋናው መ/ቤትንም የውስጥ ኦዲት ክፍል በማጠናከር ለኮሌጆቹ ድጋፍ እንዲሰጥ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ዋና ኦዲተሩ ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በማጠቃለያ አስተያየታቸው የኦዲት ግኝቱን ወስዶ ኮሚቴ አቋቁሞ የእርምት ሥራዎች መሰራት መጀመራቸው፣ ሚኒስቴር መ/ቤቱ የተጠሪ ተቋማት ኦዲት ግኝት ምን ይመስላል ብሎ በጋራ መገምገሙ፣ በፋይናንስና ንብረት ረገድ የተወሰዱ አንዳንድ ማስተካከያዎች መኖራቸውና ከሚኒስትሩ ጀምሮ የመ/ቤቱና የተጠሪ ተቋማቱ አመራሮች በይፋዊ ስብሰባው ተገኝተው ለመማርና ተጠያቂነት እንዲጠናከር በመድረኩ ያደረጉት ተሳትፎ በጥሩ ጎኑ እንደሚታዩ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም ተቋማቱ ለኦዲት ግኝት ትኩረት መስጠትና ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን ተጠያቂ ማድረግ እንዳለባቸው፤ በአጠቃላይ ሲታይ የኦዲት ግኝቶቹን ለማተካከል ፈጣን፣ አጥጋቢና የተሟላ እርምጃ ተወስዷል ሊባል እንደማይቻል፣ ከኦዲቱ በኋላ የተወሰዱ እርምጃዎችን ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አለማሳወቁ ተገቢ አለመሆኑ፣ በቀደሙ ኦዲቶች የተገኙ ግኝቶች አሁንም ደግመው መገኘታቸው የኦዲት ግኝቶችን ተቀብሎ እንዳይደገሙ በመስራት ላይ እጥረት እንዳለ እንደሚያሳይ እና በኦዲት ወቅትና በመውጫ ስብሰባ ላይ መረጃዎችን አሟልቶ በማቅረብ ላይ ችግር እንዳለ ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የኦዲት ግኝቶቹን መልሶ ማየትና አዲሱ አመራርም ከኦዲት ግኝቱ መማር እንዳለበት፣ የተወሰዱ የዕርምት እርምጃዎች ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በአስቸኳይ ሊገለጹ እንደሚገባ፣ በተሰብሳቢና በተከፋይ ሂሳቦች ላይ ስትራቴጂክ አመራሩ ልዩ ትኩረት መስጠትና ልዩ ትኩረቱም የማጣራት ስራውን በኮንትራት ማሰራትን ሊጨምር እንደሚገባ፣ ተቋሙ እንደሚያንቀሳቅሰው ሰፊ ሀብት የውስጥ ኦዲቱ በሚገባው ልክ የማይንቀሳቀስበት መሆኑ አሳሳቢ በመሆኑ ለውስጥ ኦዲት መጠናከር ትኩረት ሰጥቶ በአፋጣኝ መስራት እንደሚገባ፣ በጀትን በፋይናንስ መመሪያ መሰረት ብቻ መጠቀም እንደሚገባና በዚህ ረገድ የሚታዩ ችግሮች ወደፊት እንዳይደገሙ መስራት እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ሚኒስቴር መ/ቤቱና ተጠሪ ተቋማቱ መደጋገፍና የርስ በእርስ ልምድ ልውውጥ ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡

ክቡር አምባሳደር መስፍን አያይዘውም ካለው የተከማቸ ንብረት አንፃር በንብረት ማስወገድ ላይ ገፍቶ መሄድ እንደሚያስፈልግ፣ በኬሚካል ማስወገድ ረገድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በቅርበት መሥራት እንዲሁም ሚኒስቴር መ/ቤቱ እንደ ከፍተኛ ኬሚካል አስገቢነቱና ፈቃድ ሰጪነቱ በአወጋገዱ ላይም ባለቤትና ዘመናዊ አሰራር እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚገባው እንደዚሁም መ/ቤቱ በየዓመቱ ተቀባይነት የሚያሳጣ የኦዲት ግኝት የሚገኝበት መ/ቤት ከመሆን እንዲወጣ አመራሩ መስራት እንደሚጠበቅበትና መ/ቤቱ ከተሸከመው ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነትና ከሚያንቀሳቅሰው ከፍተኛ ሀብት አንፃር ለሀብት አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *