News

በግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ የኦዲት ግኝቶች ላይ ይፋዊ ስብሰባ ተካሄደ

በግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ  የኦዲት ግኝቶች ላይ ይፋዊ ስብሰባ ተካሄደ

በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ በ2004-2006 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝቶች ሪፖርት ላይ ይፋዊ ስብሰባ /Public Hearing/ ጥር 18፣ 2008 ዓ.ም አካሄዷል፡፡
የኦዲት ሪፖርቱ በቀረበት ወቅት በኤጀንሲው የግል ድርጅቶች የጡረታ መዋጮ እንዲከፍሉ የሚያደርግ አስገዳጅ ህግ የሌለ መሆኑን፣ የፈንድ አስተዳደርና የሒሳብ አያያዝ ማንዋል አለመዘጋጀቱን እና የግል ድርጅቶች ውዝፍ መዋጮ እንዲከፍሉ የሚያደርግ አሠራር አለመኖሩ ተገልጿል፡፡
ከገንዘብ አሰባሰብ ጋር በተያያዘም ኤጀንሲው የጡረታ መዋጮ ሂሳቦች ወደሌላ አካውንት ገብተው መገኘታቸውንና የማን እንደሆነ የማይታወቅ ሂሳብ በኤጀንሲው አካውንት ገቢ ተደርጎ መገኘቱ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
የኦዲት ሪፖርቱን ተከትሎ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመንግስት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ዶ/ር አድሃነ ኃይሌ ሲገልፁ የኦዲት ግኝት ሪፖርት ከወጣ በኋላ ኤጀንሲው ብዙ ማስተካከያ እርምጃዎች መውሰዱን አድንቀው አሁንም መረጃዎችን አደራጅቶ መያዝ ላይ እና ከሠራተኞች ማህበራት ተቀናጅቶ መሰራት ላይ ትኩረት ተሠጥቶ ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሌሎች የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው ኤጀንሲው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ከመስራት ባለፈ ደንብና መመሪያዎች ተፈጻሚነታቸውን ሊከታተል እንደሚገባና ከባንኮችና ጉሙሩክ መ/ቤቶች ጋር ተያያዞ የሚፈጠረውን የገቢ አሰባሰብ ችግር መፍታት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓታቸውን ማስተካከል እንዳለባቸውና የጡረታ መዋጮ በተመለከተም በወቅቱ ወይም ፈፅሞ የማይከፍሉ ተቋማትን በመለየት ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የግል ድርጅት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ገ/ሚካኤል በኦዲት ሪፖርት ለተገኘው ግኝት እና ከቋሚ ኮሚቴው ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ የኦዲት ሪፖርቱን ተከትሎ በርካታ ማስተካኪያዎች መደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
ማህበራት በዕቅድ ዝግጀት ላይ በመሣተፍ እየሰሩ እንደሚገኙ፤ የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓት ማጎልበትን በተመለከተም እስከ ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶች ድረስ ኦዲተሮች እንዳሉ በተዋረድ የቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሪፖርት ለሪጅን ፅ/ቤቶች ከዚያም ለኤጀንሲው እንደሚደርስ አስረድተዋል፡፡ የቁጥጥር ሥርዓት በተመለከተም እስታንዳርድ ማንዋል ማዘጋጀታቸውንና የቁጥጥር ሥርዓቶቹ በየደረጃው በተዋረድ መቀመጣቸውን አቶ ፀጋዬ ገልፀዋል፡፡
ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው የመረጃ አሰጣጥ ሥርዓት ለማጎልበት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሠሩ ያሉትን ሥራ እንዲሁም የኦዲት ሪፖርቱን ወስደው አክሽን ፕላን ማዘጋጀታቸውን አድንቀው አሁንም የጡረታ መዋጮ የማይከፍሉ፣ ያልተመዘገቡ እንዳሉ ገልፀው አስፈላጊው የመንግስት ግብር እንዲከፍሉ ማድረግ እንደሚጠበቅ አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በበኩላቸው ኤጀንሲው የቁጠባ ባህል እንዲዳብር ከማድረግ አኳያ ሊሰራ እንደሚገባ፤ የመረጃ ሥርዓቱም የዘመኑን ቴክኖሎጂ በአግባቡ ተግባራዊ ያደረገ ሊሆን እንደሚገባና ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ቅንጅት በመፈተሽ በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አክለውም አምባሳደሩ የግል ሠራተኞች ቅጥር በተመለከተ አሁንም ብዙ ችግሮች የሚስተዋሉበት በመሆኑ የተቀናጀ ሥራ ከማህበራትና ድርጅቶች ጋር በመሥራት ማስተካከል የግድ እንደሚል፤ በአዋጁ መሠረት ህጋዊ መንገድ ተከትለው በማይሰሩት ድርጅቶች ላይ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባና ለመልካም አስተዳደር ችግር ብሎም ለኪራይ ሰብሳቢነት በር የሚከፈፍቱ አሰራሮችን ማስተካከል እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡

Office of the Federal Auditor General, Ethiopia's photo.
Office of the Federal Auditor General, Ethiopia's photo.
Office of the Federal Auditor General, Ethiopia's photo.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *