በክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የፌዴራል ዋና ኦዲተር የተመራ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት የስራ አመራር የልዑካን ቡድን የሱዳን ሪፐብሊክ መንግስት ኦዲት ቻምበር ባደረገለት ግብዣ መሰረት በሱዳን ካርቱም የስራ ጉብኝት አደረገ፡፡
የሱዳን ሪፐብሊክ መንግስት የሱዳን ኦዲት ቻምበር ዋና ኦዲተር ክቡር አልጣሂር አብደላዮም ማሊክ የልዑካን ቡድኑን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት የስራ ጉብኝቱ ዓላማ በሁለቱ ጎረቤት አገሮች የኦዲት መ/ቤቶች መካከል አንዱ ከሌላው ልምድ እንዲቀስም እና ተቋማዊ አፈጻጸምን በተከታታይ ለማሻሻል ታስቦ የተደረገ በመሆኑ ለሁለታችንም እጅግ ጠቃሚና ወቅታዊ ነው ብለዋል፡፡
የኢፊዴሪ መንግስት ፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው የሱዳን ሪፐብሊክ መንግስት ኦዲት ቻምበር በሁለታችን መካከል የልምድ ልውውጥ እንድናደርግ ላደረጋችሁልን ግብዣ በእጅጉ አመሰግናለሁ ካሉ በኋላ ሁለቱ አገራት በጋራ የምንጋራቸው ልምድና ባህል ያለን ጎረቤት አገሮች ነን፤ በኦዲት ዘርፍ አሰራር አንዳችን ለሌላችን የምናካፍለው ልምድ ያለን ቢኖርም እስካሁን ይህንን አላደረግንም፡፡ ይህንን ግምት ውስጥ በማስገባት የሱዳን ኦዲት ቻምበር ልምድ እንድንለዋወጥ ቀዳሚ ፍላጎቱን በማሳየት ስለጋበዘን በድጋሜ አመሰግናለሁ፡፡ ስለሆነም ከዚህ በኋላ በምናደርጋቸው የእርስ በእርስ የጋራ መድረኮች በርካታ የአሰራር ልምዶችን መለዋወጥና መደጋገፍ እንችላለን ብለዋል፡፡ በሁለቱ የኦዲት መ/ቤቶች በጋራ ስምምነት በተመረጡ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያሉ የኦዲት አሰራሮችን በተመለከተ በሁለቱም መ/ቤቶች በኩል የመወያያ ጽሑፎች ቀርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በውይይቱ አንዱ ለሌላው ልምድ ማካፈል የተቻለበትን እድልም የፈጠረ ነበር፡፡
በሁለቱም ወገን በኩል ቀርበወ ውይይት ከተደረገባቸው ዋና ዋና ርዕሰ ጉዳዮች መካከል፡-
• የተቋም ታሪካዊ ዳራ እና ህጋዊ ማዕቀፍ፣
• የተቋም አቅም ግንባታ ስልጠና እና የማበረታቻ ስርዓት፣
• የኦዲት ስልትና ደረጃዎች፣
• የኦዲት ሂደትና ክትትል፣
• የፋይናንሺያልና ህጋዊነት ኦዲት፣
• የክዋኔና የአካባቢ ኦዲት፣
• የመንግስት ልማት ድርጅቶች ኦዲት፣
• ድህረ ኦዲት ክትትልና እርምጃ አወሳሰድ፣
• የባለድርሻ አካላት ግንኙነትን መምራት የሚሉ ናቸው፡፡
የልዑካን ቡድኑ የሱዳን ኦዲት ቻምበር ጥቅምት 22/2008 ዓ.ም ለፓርላማ ያቀረበውን ሪፖርት በፓርላማው የመሰብሰቢያ አዳራሽ በመገኘት መከታተል ችሏል፡፡የሪፖርት አቀራረብ ሂደቱን መከታተል መቻሉ በአገራችን ከሚከናወነው የሪፖርት አቀራረብ አንጻር ያለውን እድነትና ልዩነት ለመገንዘብ እድል የፈጠረ እንደነበር የልዑካን ቡድኑ አባላት ገልጸዋል፡፡
የሁለቱ አገራት የኦዲት መ/ቤቶች የልምድ ልውውጥ በቀጣይነት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን በጋራ ተስማምተዋል፡፡ስለሆነም ግንኙነቱ የሚመራበት የጋራ መግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡ በተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ መሰረት የሁለቱን ኦዲት መስሪያ ቤቶች የመፈጸም አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል እንደሚሆን ታምኖበታል፡፡
በተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ መሰረት በኦዲት አሰራሮች ዙሪያ የልምድ ልውውጦች ይደረጋሉ፣ የእውቀትና የስልጠና እድሎችን መጠቀም እንዲቻል በጋራ ይሰራል፣ የአገልግሎት አሰጣጥ መረጃዎችን እና የአስተዳደር አሰራር ልምዶችን መለዋወጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል፡፡
ስለሆነም በሁለቱ አገሮች መካከል የሚደረገው የስራ ልምድ ልውውጥ በቀጣይነት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ከተደረገው አጠቃላይ ውይይትና ከተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ መረዳት ተችሏል፡፡