News

በኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ የማይወስዱ አካላት እንዲጠየቁ ምክር ቤቱ ክትትሉን ማጠናከር እንዳለበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ገለጸ

በኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ የማይወስዱና የመንግስትን ሀብት በአግባቡ የማያስተዳድሩ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ክትትሉንና ቁጥጥሩን ማጠናከር እንዳለበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ አስገነዘቡ፡፡

ክብርት ወ/ሮ መሰረት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በፌዴራል መንግስት መ/ቤቶች ላይ ያካሄደውን የ2012 በጀት አመት የፋይናንስና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 22/2013 ዓ.ም ባቀረቡበት ወቅት በኦዲት ተደራጊዎች ላይ ለበርካታ አመታት በኦዲት ግኝትነት የሚጠቀሱ ችግሮች አሁንም ሳይታረሙ እንደቀጠሉ ገልጸዋል፡፡

ክብርት ወ/ሮ መሰረት የኦዲት ግኝቶቹ በየአመቱ ተደጋግመው የሚከሰቱት በመንግስትና ህዝብ ሀብት ላይ ጉዳት በሚያደርሱና የተጣለባቸውን ሀላፊነት በአግባቡ በማይወጡ የመንግስት ተቋማት አመራሮችና ሰራተኞች ላይ አስተማሪ የቅጣት እርምጃ ባለመወሰዱ ነው ብለዋል፡፡

በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ኦዲቱን በታቀደለት ጊዜ መጀመር አልተቻለም ያሉት ምክትል ዋና ኦዲተሯ በዚህም ምክንያት የእቅድ ክለሳ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም በ118 መ/ቤቶችና 36 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ላይ የፋይናንሻል ኦዲት ለማድረግ እንዲሁም 23 አዲስና 4 የክትትል የክዋኔ ኦዲቶችን ለማከናወን ታቅዶ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የእቅድ አፈጻጸሙን ሲገልጹም የ117 መ/ቤቶችና የ35 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የፋይናንሻል ኦዲት (99.1 %) ተጠናቋል ብለዋል፡፡ በክዋኔ ኦዲት ረገድም 17 አዳዲስ የክዋኔ ኦዲቶችና 3 የክትትል ኦዲቶች ሙሉ በሙሉ በመጠናቀቃቸው አፈፃፀሙ 74% እንደሆነና ፤1 መደበኛ ኦዲት  ባለመጠናቀቁ ወደ 2013/2014 ኦዲት አመት እንደተሻገረ ቀሪዎቹ 5 ኦዲቶችም ስራቸው ተጠናቆ የመውጫ ስብሰባና የኦዲት ተደራጊዎችን ምላሽ የሚጠባበቁ  በመሆኑ ሲጠናቀቁ አፈፃፀሙ 92.59% እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡

ክብርት ወ/ሮ መሰረት የፋይናንሻል ኦዲቱ የወጡ የፋይናንስና የንብረት አስተዳደር ህጎችን በአግባቡ ባለመተግበር ምክንያት የታዩ ግኝቶችን አሳይቷል ብለዋል፡፡ ከነዚህ ግኝቶች ውስጥ ከጥሬ ገንዘብና ከባንክ ሂሳብ አያያዝ፣ ከውዝፍ ተሰብሳቢና ተከፋይ ሂሳቦች፣ ከህግ ውጭ ከሚፈጸሙ ግዥዎችና የጥቅማጥቅምና ሌሎች ክፍያዎች፣ ከውል አስተዳደር ግድፈቶች፣ ከመንግስት ገቢ አተማመንና አሰባሰብ እንዲሁም ከውዝፍ ገቢ አሰባሰብ፣ ከበጀት አስተዳደርና አጠቃቀም እንዲሁም ከንብረት አጠቃቀምና አያያዝ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡

በዚህ መልኩ ሪፖርቱ ከጠቀሳቸው ግኝቶች ውስጥ ለአብነት ያህል በመቱ ዩኒቨርስቲና በማእከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በድምሩ ብር 77 ሺህ የጥሬ ገንዘብ ጉድለት መገኘቱና በሁለት መ/ቤቶች ወደ ገንዘብ ሚኒስቴር ፈሰስ መደረግ የነበረበት በባንክ ያለ ብር 39.1 ሚልየን መኖሩ ተጠቅሷል፡፡ በውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ በኩልም በ90 መ/ቤቶችና 12 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች  ብር 7.48 ቢልየን በወቅቱ ሳይወራረድ መገኘቱንና ለዚህም ትልቁን ድርሻ ከሚወስዱ ተቋማት መካከል የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እንደሚገኙበት ኦዲቱ አሳይቷል፡፡

በገቢ አሰባሰብ በኩልም በድምሩ ብር 390 ሚልየን በተለያዩ ገቢ ሰብሳቢ መ/ቤቶች ሳይሰበሰብ የቀረ ሲሆን  በገቢዎች ሚኒስቴር ስር ባሉ በ6 ቅርንጫፎች እና በጉምሩክ ኮሚሽን ስር ባሉ 6 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች በታክስ አዲት/ድህረ እቃ አወጣጥ ኦዲት ውሳኔ መሰረት ያልተሰበሰበ ብር 7.7 ቢልየን ውዝፍ የገቢ ሂሳብ መኖሩ ተገልጿል፡፡

በወጪ ረገድም በ30 መ/ቤቶች ብር 475 ሚልየን የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብለት ወጪ የሆነ ሲሆን፣  62 መ/ቤቶችና 11 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ደግሞ መመሪያን ሳይከተሉ የብር 96.8 ሚልየን ከደንብና መመሪያ ውጪ ክፍያ መፈጸማቸውን፣ ይህን ክፍያ ከፈጸሙት ውስጥም ዋቸሞ ዩኒቨርስቲ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ፣ ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ፣ ባህርዳር ዩኒቨርስቲ፣ እንጅባራ ዩኒቨርስቲ፣ ወልድያ ዩኒቨርስቲና ደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ  ዋና ዋናዎቹ መሆኑን አሳይቷል፡፡  በሌላ በኩል በተለያዩ ተቋማት አላግባብ በብልጫ የተከፈለ ብር 63.4 ሚልየን እንዳለ በኦዲት ሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

በግዥ በኩልም የግዥ መመሪያን በመጣስ የብር 1.2 ቢልየን ግዥዎች መፈጸማቸውና ይህንን ከፈጸሙ አካላት መካከል የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት፣ ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ፣ አሶሳ ዩኒቨርስቲ፣ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ፣ ወላይታ ሶዶ ዪኒቨርስቲ እና አርባ ምንጭ ዩኒቨርስቲ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በበጀት አጠቃቀም በኩልም 20 መ/ቤቶችና 2 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የሚመለከተውን አካል ሳያስፈቅዱና በጀት ሳያዘዋውሩ  ከመደበኛ በጀት፣ ከውስጥ ገቢና ከካፒታል በጀት በድምሩ ብር 846.4  ሚልየን  ከተደለደለው በጀት በላይ ወጪ አድርገዋል፡፡ ይህን ከፈጸሙት ውስጥም ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ፣ ዋቸሞ ዩኒቨርስቲ፣ የኢሚግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ፣ ጅግጅጋ ዩኒቨርስቲና ወልቂጤ ዩኒቨርስቲ በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

በመንግስት ንብረት አያያዝ ረገድም የተለያዩ የንብረት አስተዳደር ግድፈቶች በበርካታ ተቋማት ላይ እንደተስተዋለ በኦዲቱ ተጠቅሷል፡፡

ኦዲቱ በፋይናንሻል ኦዲት ከተገኙት ግኝቶች በተጨማሪ በመንግስት መ/ቤቶች የስራ አፈጻጸምና በፕሮጀክቶች አመራር ላይ ያተኮሩ የኦዲት ሪፖርቶች ውጤቶችን አቅርቧል፡፡

ክብርት ወ/ሮ መሰረት አብዛኞቹ ኦዲት ተደራጊ ተቋማት በኦዲት ግኝቶች ላይ እርምጃ ስለመወሰዳቸው በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለዋና ኦዲተር መ/ቤት እያሳወቁ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም በ2012 ኦዲት በተደረገው የ2011 በጀት አመት ሒሳብ  በ68 መ/ቤቶች እና በ7 ቅርንጫፍ መ/ቤቶች በተለያዩ የኦዲት ግኝቶች ላይ ተመላሽ እንዲደረግ ተብሎ አስተያየት ከተሰጠበት ብር 1.78 ቢልየን ውስጥ ተመላሽ የተደረገው 261.8 ሚልየን ብር ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ምክር ቤቱ በተሰጣቸው የኦዲት ማሻሻያ ሀሳብ መሰረት ማስተካከያ ባላደረጉ እና የመንግስት ገንዘብ እንዲመለስ ባላደረጉ መ/ቤቶች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ በትኩረት መከታተል እንዳለበት ምክትል ዋና ኦዲተሯ አሳስበዋል፡፡

ክብርት ወ/ሮ መሰረት በሪፖርቱ ውስጥ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን የድጋፍ ዘርፍ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አካተው ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ተቋሙን ካጋጠሙት ችግሮች ውስጥ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ኦዲቱን አስቀድሞ በወጣው የጊዜ ሰሌዳና መጠን እቅድ መሰረት ለመፈጸም አለመቻሉ፣ የተወሰኑ የመ/ቤት ሀላፊዎች በሰበብ አስባቡ ኦዲት ላለመደረግ የፈጸሙት ያልተገባ ሙከራ መኖሩ፣  አንዳንድ ክልሎች ለኦዲቱ እንቅፋት መፍጠራቸው፣ አንዳንድ ኦዲት ተደራጊዎች ለኦዲቱ መሳካት የሚጠበቅባቸውን ሀላፊነት በአግባቡ አለመወጣታቸውና በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የነበረው የጸጥታ መደፍረስ በኦዲት ስራው ላይ እክል መፍጠሩ የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡ በመ/ቤቱ በኩል ተጠንቶ የቀረበው መዋቅር በምክር ቤቱ ቢጸድቅም መዋቅሩን ተከትሎ የቀረበው የደመወዝ ጥያቄ በምክር ቤቱ አለመጽደቁ በመ/ቤቱ ስራ ላይ ችግር መፍጠሩን ክብርት ምክትል ኦዲተሯ ገልጸው ምክር ቤቱ ችግሩ እንዲፈታ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ክብርት ወ/ሮ መሰረት የኦዲት ሪፖርቱንና የመ/ቤቱን አፈጻጸም አስመልክቶ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በሰበሳቢው በተከበሩ አቶ መሀመድ ዩሱፍ ባቀረበው የማጠቃለያ አስተያየት በሚመለከታቸው አካላት ሊወሰዱ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ አመላክቷል፡፡ በዚህም  የፋይናንስ ህግን ባለማክበር የመንግስትና የህዝብ ሀብትን ያባከኑ የመንግስት ሀላፊዎችና ባለሙያዎች በኦዲት አስተያየት መሰረት ማሻሻል ያለባቸውን እንዲያሻሽሉ፣ መመለስ ያለበትን ገንዘብ እንዲያስመልሱ እንዲሁም በተለይ የግዥ ህግን ተላልፈው የተገኙ አካላት እንዲጠየቁ ማድረግ ይገባል ብሏል፡፡

ቋሚ ኮሚቴው በተጨማሪም የመንግስትና የህዝብን ጥቅም የማስጠበቅ ህጋዊ ስልጣን የተሰጠው ጠቅላይ አቃቤ ህግ በ2011 ዓ.ም በምክር ቤቱ በተላለፈው ውሳኔ መሰረት በኦዲት ግኝት መነሻነት የህግ ጥሰትና ወንጀል የፈጸሙ አካላትን በመለየት በህግ ማስጠየቅ ይገባዋል ብሏል፡፡

በተመሳሳይ መልኩም ገንዘብ ሚኒስቴር በኦዲቱ መነሻነት የኦዲት ግኝት ማስተካከያ እንዲደረግ መርሀ ግብር በማዘጋጀት ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅበት እንዲሁም በመንግስት ፕሮጀክቶች ላይ የታዩ ጎላ ያሉ ችግሮች እንዲፈቱና በሀገሪቱ ላይ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለበት የፋይናንስ አስተዳደር እንዲኖር ሚናውን መወጣት እንዳአለበት ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

በምክር ቤቱ በኩልም ቋሚ ኮሚቴዎች በሚከታተሏቸውና በሚቆጣጠሯቸው መ/ቤቶች የኦዲት ግኝት ላይ ማሻሻያና የእርምት እርምጃ ተግባራዊ እንዲደረግ በምክር ቤቱ የተላለፈውን ውሳኔ ማስተግበር አለባቸው ብሏል፡፡ እንደአጠቃላይም ምክር ቤቱ የኦዲት አስተያየት መስጠት ባልተቻለባቸውና በኦዲት የጎላ ችግር በታየባቸው ተቋማት ላይ ተገቢው ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ማድረግ እንዲሁም በኦዲት ግኝቶች ላይ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ከዚህ በፊት ያሳለፈው ውሳኔ ወደተግባር ተሸጋግሮ ውጤት እንዲታይ ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ አለበት ሲል ቋሚ ኮሚቴው አስገንዝቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *