መ/ቤቱ የፌዴራል መንግስት መ/ቤቶችን የ2009 በጀት ዓመት የሂሳብና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል፡፡
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የ2009 በጀት ዓመት የሂሳብና የክዋኔ ኦዲት የተጠቃለለ ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 16፣ 2010 ዓ.ም አቀረቡ፡፡ ምክር ቤቱ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በየዓመቱ የሚያወጣውን የኦዲት ሪፖርት መሠረት አድርጎ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነቱን አለመወጣቱን ገልጿል፡፡
ክቡር ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ በምክር ቤቱ 5ኛ ዘመን 3ኛ ዓመት 26ኛ መደበኛ የምክር ቤት ስብሰባ ሪፖርታቸውን ባቀረቡበት ወቅት በ2009 በጀት ዓመት በመ/ቤቱ ኦዲት ለማድረግ ከታቀዱት 174 መ/ቤቶች ሁለቱ ከዕቅድ በኋላ በመታጠፋቸው አንድ ተቀንሶ የ173 መ/ቤቶችና 48 ቅ/ጽቤቶችና የፌዴራል መንግስት የ2009 በጀት ዓመት አጠቃላይ ገቢና ወጪ ሂሳብ ኦዲትንም በማጠናቀቅ የፋይናንስና ህጋዊነት ኦዲት ዕቅድ አፈፃፀም 100% ማሳካታቸውን እንዲሁም በክዋኔ ኦዲት 20 አዳዲስ የክዋኔ ኦዲቶች ሥራ ለመስራት ታስቦ በታቀደው መሠረት ማጠናቀቅ ሲቻል በክትትል ኦዲት 8 ለማድረግ ታስቦ 6ቱ ብቻ መጠናቀቃቸውንና የዓመቱ የክዋኔ ኦዲት ዕቅድ ክንውን 92.86% መሆኑን ገልፀዋል፡፡ እንደዚሁም በመሠረታዊ አገልግሎት ከለላ ኦዲት በዕቅዱ መሠረት የ251 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ጽ/ቤቶችና የፕሮግራሙ ፈፃሚ በሆኑ የሴክተር ቢሮዎች እንዲሁም አንድ ፕሮግራም አቀፍ የሆነውን የማጠቃለያ ኦዲት በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ደረጃ ለመፈፀም መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በፋይናንስ፣ በግዥና ንብረት አስተዳደር እንዲሁም በተልዕኮ አፈጻጸም ረገድ በፌዴራል የመንግስት ተቋማት ላይ የታዩና በኦዲት ግኝት የታዩ ጉዳዮችን በዝርዝር ክቡር ዋና ኦዲተሩ ያቀረቡ ሲሆን ችግሮቹን ለመፍታት በተከበረው ምክር ቤት በቀጣይ ሊወስድ በሚገቡ ጉዳዮች ላይ የመፍትሔ አስተያየቶችን አቅርበዋል፡፡ በተጨማሪም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን ዋና ዋና የድጋፍ ዘርፍ አፈጻጸምን፣ የ2009 በጀት ዓመትና የ2010 በጀት ዓመት የ9 ወር የበጀት አጠቃቀም እና የ2010/2011 ኦዲት ዓመት ዕቅድን ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
የዋና ኦዲተሩን ዓመታዊ የኦዲት ሪፖርት ተከትሎ የምክር ቤቱ አባላት በቁጭት አስተያየታቸውን የገለፁ ሲሆን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተጣለበትን ኃላፊነት በተገቢው ሁኔታ ቢወጣም ምክር ቤቱ ግን በሚፈለገው ደረጃ ተጠያቂነት የማረጋገጥ ኃላፊነቱን አለመወጣቱን፤ ጠቅላይ አቃቤ ህግም የዋና ኦዲተር መ/ቤትን የኦዲት ሪፖርት መሠረት አድርጎ ተጠያቂነትን ሊያረጋግጥ አለመቻሉንና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ሁሉም አስፈጻሚ አካላት በሚገኙበት የኦዲት ሪፖርት ላይ ግልፅ የሆነ አቅጣጫ ሊሰጥ እንደሚገባ ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ት ወይንሸት ገለሶ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየት የዋና ኦዲተር መ/ቤት ያስመዘገባቸውን ውጤታማ ስኬቶችና ይበልጥ ተቋሙ አጠናክሮ ሊቀጥልባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን በተለይም የኦዲት ግኝት ችግሮች ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሱ የሄዱ በመሆኑ በልዩ መድረክ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በተገኙበት የኦዲት ጉዳይ ሊታይ እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴውም አስተያየት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከዓመታዊ የኦዲት ሪፖርቱ በተጨማሪ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሠራተኞች አስተዳደር ረቂቅ ደንብ ለምክር ቤቱ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በሙሉ ድምፅ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አስተዳደር ደንብ ቁጥር 8/2010 ሆኖ ፀድቋል፡፡
ለፓርላማ የቀረበውን ሪፖርት በድረገፃችን http://www.ofag.gov.et/ofag/audit-report/ይመልከቱ፡፡
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለሚሰራው ሥራ ውጤት አልባ መሆን ምክር ቤቱ ራሱን ወቀሰ
