በሴቶችና ወጣቶች ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት የተዘጋጀና በተሻሻለው የፌዴራል የቤተሰብ ህግ ላይ ያተኮረ ስልጠና ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሰራተኞች ከታህሳስ 26-27፣ 2009 ዓ.ም ተሰጠ፡፡
በስልጠናው መክፈቻ ላይ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሙሉ ጥሩነህ ስልጠናው የመ/ቤቱ ሰራተኞች በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ ላይ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቤተሰብ ህጉ ላይ ስልጠና የሰጡት የመ/ቤቱ የህግ ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አወቀ አግዘው እንደገለጹት የቤተሰብ ህጉ በ1992 ዓ.ም ከመሻሻሉ አስቀድሞ በ1952 ዓ.ም በጸደቀው የፍትሀ ብሄር ህግ ውስጥ ተካቶ ይሰራበት እንደነበረና የሴቶች መብት የማያስከብሩ በርካታ የህግ ድንጋጌዎችን የያዘ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም አሁን ካለው የህብረተሰብ የእድገት ደረጃ በዋነኝነትም ከህገ-መንግስቱ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማድረግ፣ በጋብቻም ሆነ በፍች ወቅት የተጋቢዎችን እኩልነትና መብት ለማስጠበቅ አንዲሁም የህጻናትን መብት ለማስከበርና ለቤተሰብ አስፈላጊውን ጥበቃ ለማድረግ የቤተሰብ ህጉ እንዲሻሻል መደረጉን አቶ አወቀ አስረድተዋል፡፡
የቤተሰብ ህጉ መሻሻል የህገመንግስቱ ትሩፋት መሆኑን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ በህገመንግስቱ የሴቶችንና የዜጎችን መብቶች አስመልክተው የተደነገጉ ድንጋጌዎችን አካቶ እንደተዘጋጀ አስረድተዋል፡፡
አቶ አወቀ በቤተሰብ ህጉ የተካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን ከጋብቻ፣ ከፍች፣ ከትዳርና ቤተሰባዊ አኗኗር ጋር የተያያዙ ህጋዊና ስርዓተ ጾታዊ ሁኔታዎችን እንዲሁም ከፌዴራልና ከክልል የቤተሰብ ህጎች ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን ቀድሞ ከነበረው ህግና አሰራር፣ ከነባራዊ ሁኔታዎች፣ በስራና በህይወት ከተገኙ ተሞክሮዎች ብሎም ከዓለም አቀፍ ህግጋት ጋር አስተሳስረው አቅርበዋል፡፡
ስልጠናውን ተከትሎ የመ/ቤቱ ሰራተኞች ባነሷቸው ጥያቄዎች ላይ ምላሽ የተሰጠ ሲሆን ውይይትም ተካሂዷል፡፡ ሰራተኞቹ ስልጠናው ስለ ቤተሰብ ህጉ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸው የገለጹ ሲሆን በቀጣይም መሰል ስልጠናዎች እንዲዘጋጁ ጠይቀዋል፡፡
በሁለት ዙር ለግማሽ ቀን በተሰጠው ስልጠና ላይ 74 ሴትና 37 ወንድ በድምሩ 111 ሰልጣኞች የተካፈሉ ሲሆን በሁለተኛው ቀን የተሰጠውን ስልጠና አቶ ሳሙኤል ግርማ የህግ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያ ሰጥተዋል፡፡