የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለፉት ስድስት አመታት በኦዲት ዙርያ ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ገለጹ፡፡ ቋሚ ኮሚቴውና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የጋራ ስራዎቻቸውን አፈጻጸም ነሀሴ 20/2013 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ ገምግመዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ቋሚ ኮሚቴው ባለፉት ስድስት አመታት በኦዲት ግኝቶች ላይ ተመስርቶ የተጠያቂነት ስርዐት እንዲኖር፣ የተቋማት የመንግስት የሀብት አስተዳደርና የተግባር አፈጻጸም እንዲሻሻልና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እንዲጠናከር የሚያስችሉ ተጨባጭ ስራዎችን ማናወኑን ገልጸዋል፡፡
ከነዚህ ስራዎች መካከልም የኦዲት ግኝት ካለባቸው ተቋማት ጋር ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ በማድረግና በመስክ ጉብኝት በማሄድ በኦዲት ግኝቶች ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ፣ የኦዲት ግኝት መንስኤዎች እንዲስተካከሉ ጥረት እንዲደረግና በአጥፊዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ መስጠት እንደሚገኙበት ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ሌላም ኦዲቱ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና በምክር ቤቱ ባሉ ቋሚ ኮሚቴዎች ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ መቻሉና በተቋማት የሚታየው የሀብት አስተዳደርና የተልዕኮ አፈጻጸም ድክመት በህብረተሰቡና በሚድያው ታውቆ እነዚህ አካላት ግኝቶቹ እንዲታረሙ የበኩላቸውን ሚና ጥረት ማድረጉን ምክትል ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ለኦዲት ግኝት እንደሰበብ ይቀርቡ የነበሩ አሰራሮች እንዲስተካከሉና አስፈላጊ ህጎች እንዲወጡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ባደረገው ጥረት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡን ጠቅሰዋል፡፡ ቋሚ ኮሚቴው የኦዲት ባለድርሻ አካላት የጋራ የምክክር ፎረም እንዲመሰረት በማድረግም በኦዲት ግኝት፣ መፍትሄዎችና በእርምጃ አወሳሰድ ረገድ ባለድርሻ አካላት በጋራ የሚሰሩበትን ሁኔታ መፍጠሩን ጠቅሰዋል፡፡
ክብርት ወ/ሮ መሰረት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከአስፈጻሚ አካላት ነጻ በሆነ አግባብ አስፈላጊው የህግ ማዕቀፎችና አደረጃጀት እንዲኖሩትና ተገቢው መሰረተልማት እንዲሟላለት በማገዝ ብሎም የመ/ቤቱን እቅድና አፈጻጸም በቅርበት በመከታተል ግብረመልስና ድጋፍ በመስጠት ለመ/ቤቱ መጠናከር የማይተካ ሚና ተጫውቷል ብለዋል፡፡
እነዚህና በቋሚ ኮሚቴው በኩል የተሰሩ ሌሎች ስራዎች የተጠያቂነትን ስርአት ለመፍጠር በሀገሪቱ ለሚደረገው ጥረትና በቀጣይ በምክር ቤቱ ውስጥ ለሚቋቋመው የመንግስት ወጪ
አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ስራ አቅጣጫ አመላካችና መሰረት ናቸው ያሉት ክብርት ወ/ሮ መሰረት ቋሚ ኮሚቴውና ምክር ቤቱ በስራ ዘመናቸው ወቅት ላከናወኑት ውጤታማ ተግባር ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ከቋሚ ኮሚቴው ጋር በ2013 በጀት አመትና በቀደሙት አመታት በተሰሩት ስራዎች ዙርያ የውይይት መነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡ በውይይተቱ ላይም ቋሚ ኮሚቴው እስካሁን በአሰራር ያገኘውን ልምድና እውቀት በቀጣይ ለሚመጣው ቋሚ ኮሚቴ በማስተላለፍ በኦዲት ዙርያ ሲሰሩ የነበሩ ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩሊን ሚና እንዲጫወት ተጠይቋል፡፡
ከመድረኩ አስቀድሞ የምክር ቤቱ የቋሚ ኮሚቴ አባላቱና የመድረኩ ተሳታፊ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የስራ ኃላፊዎች በሲዳማ ክልላዊ መንግስት የዋና ኦዲተር መ/ቤት አስተባባሪነት በይርጋለም የተቀናጀ አግሮ-ኢንደስትሪ ፓርክ የችግኝ ተከላ ያካሄዱ ሲሆን በፓርኩ የሚገኙ ሁለት ኢንደስትሪዎችን ጎብኝተዋል፡፡