በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የመንግሰት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር መ/ቤትን የ2007 በጀት ዓመት የሒሳብ ኦዲት ይፋዊ ስብሰባ ሚያዚያ 25 ቀን፣ 2009 ዓ.ም ባካሄደበት ወቅት የሚኒስቴር መ/ቤቱ የስራ ኃፊዎችና የሚመለከታው ባለሙያዎች የፋይናንስ ህግና ደንብ ሳይጠብቁ ለፈፀሟቸው ክፍያዎች ሊጠየቁ እንደሚገባ ገለፀ፡፡
የሚኒስቴር መ/ቤቱን የሒሳብ ኦዲት ሪፖርት ያደመጠው ቋሚ ኮሚቴው ተቋሙ ይህን የጎላና ከፋይናንስ ህግና መመሪያ ውጪ ሥራዎችን እንዲሠሩ ያደረጋቸውን ጉዳይ እንዲያብራሩ በርካታ ጥያቄዎችን አንስቷል፡፡
በቋሚ ኮሚቴው ለሚኒስቴር መ/ቤቱ ከቀረቡት ጥያቄዎች ውስጥ በብር 464,893.89 የተለያዩ 5 ግዥዎችን የዋጋ ማወዳደሪያ ሳይሰበሰብ ግዥ የተፈፀመ መሆኑን፤ ከነዚህም ያለዋጋ ማወዳደሪያ ከተፈፀሙት ግዥዎች ውስጥ ለፅሕፈት መሣሪያ ወጪ ሆኖ ከተከፈለው ብር 36,400.00 የተገዛው ደብተር /በቁጥር 700/ እና እስክሪብቶ /በቁጥር 700/ በመመሪያው መሠረት በሞዴል 19 ገቢ አለመደረጋቸውን፤ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር መ/ቤትን ሳያስፈቅዱ ከመመሪያ ውጪ የተለያዩ 6 የውሎ አበል ክፍያዎችን በድምሩ ብር 199,174.75 መፈፀሙን፤ የውሎ አበል ሂሳብ በመንግስት የሠራተኛ የቀን ውሎ አበል መመሪያ መሠረት የደመወዝ መጠን፣ መነሻና መድረሻ ቦታና ሰዓት ሳይገለፅ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለጎበኙ ሠራተኞች፣ በነገሌ ቦረና ከተማ ላይ የተካሔደውን የመቻቻል ቀን ሲከበር ለተሳተፉ ተሳታፊዎች እንዲሁም በአፋር ክልል የዓለም ቱሪዝም ሲከበር ለተሳተፉ ሰዎች እና በቢሮ ውስጥ ለተሠሩ ሥራዎች በድምሩ ብር 1,223,655.00 ውሎ አበል ከመመሪያ ውጪ መክፈሉ በኦዲት ግኝቱ ተገልጿል፡፡
የወጪ ሒሳቦችን በተመለከተ ትክክለኛ የወጪ አርዕስታቸውን ጠብቀው የተመዘገቡና ሪፖርት የተደረጉ መሆናቸው ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ በ14 የተለያዩ ወጪዎች በድምሩ ብር 2,278,477.75 በትክክለኛው የሒሳብ መደብ ላይ አለመመዝገቡን እና ለሞባይል ካርድ በሁለት ክፍያዎች በጥሬ ገንዘብ 7,000.00 ያለ ወጪ ማስረጃ መጪ መደረጉን፣ ተሰብሳቢ ሒሳብን በተመለከተ በልዩ ልዩ ተሰብሳቢ ሒሳቦች በድምሩ ብር 420,429.15 ያልተወራረደ መሆኑን እና በተለያዩ ተከፋይ የሒሳብ መደቦች በድምሩ ብር 314,479.19 ሳይከፈሉ በተከፋይ ሒሳብ ተይዘው የሚገኙ መሆናቸውን የኦዲት ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም በሚኒስቴር መ/ቤቱ የእቃ ግምጃ ቤት ውስጥ አገልግሎት የማይሰጡ ፕሪንተሮች፣ ፒሲ ኮምፒዩተሮች፣ ፎቶ ኮፒ ማሽኖች፣ ወንበሮች አገልግሎት ከሚሠጡ ንብረቶች ጋር ተቀላቅለው መቀመጣቸውን እንዲሁም በግቢ ውስጥ 1 ተሸከርካሪ ያለባለቤትነት መታወቂያ ደብተር /ሊብሬ/ ሳይኖረው ከ2 ወር በላይ ቆሞ የሚገኝ መሆኑን፤ በብልሽት ከ4 ወር እና ከ6 ወር በላይ የቆሙ መኪናዎች መኖራቸውንና እያንዳንዱ ተሸከርካሪ የፈጀው የነዳጅ መጠን ከሸፈነው ኪሎ ሜትር መጠን ጋር እየተመዘገበ የነዳጅ ፍጆታ ሪፖርት በየወሩ የማይሰራ መሆኑ በኦዲቱ ተጠቅሶ እነዚህ የፋይናንስ ህግና መመሪያ ጥሰቶችን ተቋሙ ለምን እንደጣሰ ማብራሪያ እንዲሰጡ ለተቋሙ የበላይ አመራሮች ቋሚ ኮሚቴው ጥያቄዎቹን አቅርቧል፡፡
በይፋዊ ስብሳባው የሚኒስቴር መ/ቤቱ እና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በአግባቡ ተሟልተው ባልተገኙበት መድረክ ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በስብሰባው የተገኙት ሚኒስቴር ደኤታ ክቡር አቶ ረመዳን አሸናፊ ለተቋሙ አዲስ እንደሆኑና በኦዲት ሪፖርቱ የተመላከቱት ግኝቶች አውነተኛና ተቀባይነት እንዳላቸው እንዲሁም በኦዲት ግኝቱ መሠረት ተገቢውን የመከታተያ መርሃ ግብር በማዘጋጀት ማብራሪያ ለቋሚ ኮሚቴው አለመስጠታቸውንና በተቋማቸው የቅንነት፣ የሃላፊነት እና የአቅም ችግር መኖሩን ገልፀው ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ያላአግባብ የተከፈለ የትርፍ ሰዓት ክፍያን በተመለከተ በህጉ መሠረት ሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር መ/ቤትን አስፈቅደው መስራት ይጠበቅባቸው እንደነበረ ነገር ግን አሠራሩን ተግባራዊ ሳያደርጉ ክፍያው መፈፀሙንና ይህ የማሻሻያ ሃሳብ ከተሰጣቸው በኋላ አስፈቅደው ክፍያ እየፈፀሙ እንደሚገኙ፤ የለአግባብ የተከፈሉ የውሎ አበሎችንም በተመለከተ ክፍያ የተፈፀመላቸውን ሰዎች ተመላሽ እንዲያደርጉ ለማድረግ እንዳስቸገራቸው ገልፀው አስተያየት ከተሰጣቸው ጊዜ ጀምሮ በመመሪያው መሠረት ክፍያዎች እየፈፀሙ እንደሚገኙ፤ የነዳጅ አጠቃቀም ላይ የነበረውን የአሠራር ክፍተት በማረም በመመሪያው መሠረት ተፈፃሚ እንዲሆን ማድረጋቸውን፤ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን በተመለከተ ሊሰበሰቡ የሚችሉና ለመሰብሰብ አስቸጋሪ የሆኑትን በመለየት መሰብሰብ ያለባቸውን እያሰባሰቡ እንደሆነ እንደዚሁም ለረጅም ጊዜ ሲንከባለሉ የመጡና ለመሰብሰብ አስቸጋሪ የሆኑትን ሂሳቦች ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መ/ቤት ጋር በመነጋገር እልባት እንዲያገኙ እየሰሩ እንደሚገኙ፤ የንብረት አያያዝን በተመለከተ የነበሩ ችግሮችን ለማስቀረት ሊወገዱ የሚገቡትን ንብረቶች እንዲወገዱ ማድረጋቸውን፤ ያለአግባብ ከአዳዲስ እቃዎች ጋር ተቀምጠው የነበሩትን ያገለገሉ እቃዎች በመለየት በተገቢው ሁኔታ እንዲቀመጡ ማድረጋቸውን እና ሊብሬ ሳይወጣለት ተቀምጦ የነበረውንም ተሸከርካሪ ሊብሬ እንዲወጣለት በማድረግ ወደሥራ እንዲገባ ማድረጋቸውን፤ በአጠቃላይ የታዩትን ችግሮች ለመቅረፍ የተለያዩ የአሠራር ለውጦችን እንዲሁም የሰራተኛ ቅጥርና የሐላፊዎች ሽግሽግ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
ሌሎች የሚመለከታቸው የሚኒስቴር መ/ቤቱ ኃላፊዎች በተነሱት ጥያቄዎች ተጨማሪ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ተቋሙ ብዙ ጊዜ ድንገተኛና አሰቸኳይ ሥራዎች እንደሚያጋጥሙትና ይህም ከዕቅድ ውጪ ግዢዎችንና ክፍያዎችን እንዲፈፅም እንደሚያስገድደው እንዲሁም ብዙ ሁነቶች ከከተማ ውጪ በሩቅ ቦታዎች ላይ እንደሚካሄዱና ለዛም ተመጣጠኝ ክፍያ መክፈል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ለመክፈል እንደሚገደዱ እና የተቋሙ የሥራ ባህሪ አስቸጋሪና ውስብስብ በመሆኑ በወጣው ህግና ደንብ መሠረት ለመስራት አስቸጋሪ በሚሆንባቸው ጊዜ ከመመሪያው ውጪ ለመፈፀም መገደዳቸውን ገልፀዋል፡፡
የተቋሙ አመራሮች ምላሽ ከሰጡ በኋላ የቋሚ ኮሚቴ አባላት አስተያየትና ሃሳብ የሰጡ ሲሆን ሚኒስቴር መ/ቤቱ ያለጨረታ ግዥ መፈፀሙ አግባብ አለመሆኑን፤ በተሰብሳቢ ሒሳብና በሌሎች ከመመሪያ ውጪ በተፈፀሙ የውሎ አበል ክፍያዎች ተቋሙ ለማስተካከልና ለማስመለስ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ እንጂ ምን ያህሉን እንዳስተካከሉ ወይም እንዳስመለሱ ዝርዝር መረጃ ማቅረብ አለመቻላቸውን፣ ከኦዲት ግኝቱ በኋላ የተቋሙ አመራር ቁጭ ብሎ በመነጋገርና እቅድ በማዘጋጀት በአግባቡ የእርምትና የማሻሻያ እርምጃ ለመውሰድ አለመሞከሩን፤ የተቋሙ የፋይናንስና የኦዲት ክፍል በአግባቡ ተጠናክሮ እየሰራ እንደማይገኝ ገልፀው ሠራተኞች የሥራ ኃላፊነት ሲሰጣቸው ከተጠያቂነት ጋር ሊሆን እንደሚገባ እና የሁነት መብዛት ህግና መመሪያ ለመጣስ ምክንያት ሊሆኑ እንደማይችሉ አውቆ በእቅድ በመመራት ሊሰራ እንደሚገባ አባላቱ አሳስበዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት ሃሳብ የተቋሙ አመራሮች በኦዲት ግኝቱ መሠረት የእርምት እርምጃ መውሰዳቸውን ይግለፁ እንጂ የተሻሻለ ነገር አለመኖሩን እንዲያውም መባባሱን ገልፀዋል፡፡ ዋና አዲተሩ እንደገለፁት በ2008 ዓ.ም የኦዲት ግኝት ላይም ማየት እንደቻሉት አሁንም ያለጨረታ ግዥዎች እንደሚፈፅሙ፣ የትርፍ ሰዓት ክፍያም ከመመሪያ እና ደንብ ውጪ እየተፈፀሙ እንደሚገኙ፣ የአመዘጋገብ ስህተት አሁንም መኖሩን እና የለአግባብ የሚከፈሉ ውሎ አበል ክፍያዎች አለመታረማቸውን አስረድተው በተቋሙ ያለው አንዱ ቁልፉ ችግር ከሁነት ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ አግባብነት የሌላቸው ክፍያዎች መሆናቸውንና ይህንንም የፈፀሙ አመራሮችም ሆኑ ሠራተኞች ሊጠየቁና የህዝብ ገንዘብ በተጠያቂነት ሊረጋገጥ እንደሚገባው ገልፀዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በመጨረሻ በሰጡት የማጠቃለያ ሃሳብ ተቋሙ የኦዲት ግኝቱ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ፣ በኦዲት ግኝቱ መሠረት የወሳዳቸውን እርምጃዎች በድርጊት መርሃ ግብር ለዋና ኦዲተር ሊያሳውቅ እንደሚገባ፣ ተቋሙ በድፍረት የፋይናንስ ህግና ደንብ በመጣስ የሚሰራቸውን አሰራሮች በአስቸኳይ ሊስተካክል እንደሚገባ፣ የቋሚ ኮሚቴው አባላትና ዋና ኦዲተሩ የሰጡትን አስተያየቶችና ምክረ ሃሳቦች በመተግበር ሊስተካከሉ የሚገባቸው አሠራሮች በሙሉ መስተካከል እንዳለባቸው እና በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤት ማምጣትና ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡