በመ/ቤቱ የሴቶች ፎረም ተቋቋመ
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ጥቅምት 03 ቀን 2009ዓ.ም ባዘጋጀው የግማሽ ቀን ስብሰባ ሰባት ዓባላት ያሉት የሴቶች ፎረም ኮሚቴ ተቋቋመ፡፡
በዕለቱ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሙሉ ጥሩነህ የፎረሙ መቋቋም ሴቶች በመ/ቤቱ ውስጥ ያላቸውን ተጠቃሚነትና የሚኖራቸውን ሚና የጎላ እንደሚያደርገው ገልፀዋል፡፡ ተሰብሳቢ የመ/ቤቱ ሴት ሠራተኞች የተገኙ ሲሆን ሰባት ዓባላት የመረጡ ሲሆን በቀጣይ ከዳይሬክቶሬቱ ጋር በሚያደርጉት ውይይት የተለያየ ኃላፊነት እንደሚሰጣቸውና ወደሥራ እንዲገቡ እንደሚደረግ በመድረኩ ተገልጿል፡፡
ፎረሙን ከማቋቋም ጎን ለጎን በጀንደር ሜኒስትሪሚንግ ፅንሰ ሃሳብ ምንነት እና አስፈላጊነት ዙሪያ በሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ገዛኸኝ ሙሊሳ ገለፃ ተደርጓል፡፡ በስብሰባው የተገኙ ሠራተኞችም ከፎረሙ መቋቋም፣ ሴቶችን ይበልጥ ተጠቃሚ ከማድረግና በተሻለ የሥራ አካባቢ እንዲሠሩ ከማስቻል ጋር በተገናኙ ጉዳዮች ሃሳብና ጥያቄዎች አንስተው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
ወ/ሮ ሙሉ ጥሩነህ በተነሱት ሃሳቦችና ጥያቄዎች ዙሪያ ምላሽ ሲሰጡ የሜኒስትሪሚንግ ስራ በጅምር ላይ እንደሚገኝና ይበልጥ አጠናክረው በመቀጠል በተነሱት ጉዳዮች ላይ ከሁሉም የመ/ቤቱ ሠራተኞች ጋር እንደሚሠሩ ገልፀው በተለይም የሴቶች የነቃ ተሳትፎ ለታሰበው ግብ ስኬት የጎላ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡ በስብሰባው ላይ በርካታ የመ/ቤቱ ሴት ሰራተኞች ተካፍለዋል፡፡