ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የገቢዎችና ጉምሩክ ኦዲት ዳይሬክተሬት ኦዲተሮች የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የሀገር ውስጥ ታክስን እና የጉምሩክ አሰራርን ለማስተዳደር እየተጠቀመበት ስላለው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ የመረጃ አያያዝ ስርዓት ስልጠና ተሰጠ፡፡
በባለስልጣኑ የመረጃ ስራ አመራር ቴክኖሎጂ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ጌትነት አበባው ስለ ስልጠናው ተጠይቀው በሰጡት አስተያየት መ/ቤቱ የሀገር ውስጥ ታክስን በሲግታክስ (SIGTAX) እንዲሁም የጉምሩክ አሰራርን በአሲኩዳ ፐላስ ፕላስ (ASYCUDA++) የመረጃ አስተዳደር ስርዓትን እየመራ እንደሚገኝ ገልጸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ኦዲተሮች የባለስልጣኑን በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር በአግባቡተረድተው ስራቸውን እንዲያከናውኑ ስልጠናው ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በስልጠናው ወቅት ሠልጣኞቹ ስለሁለቱ የመረጃ አስተዳደር ስርአቶች ምንነት፣ ከምዝገባ እስከ ሪፖርት ዝግጅት ድረስ መረጃዎች በስርዓቶቹ ተደራጅተው ጥቅም ላይ ስለሚውሉበት ሂደት እንዲሁም ከሀገር ውስጥ ገቢ አስተዳደርና ከጉምሩክ ስርዓት ጋር በተያያዘ ኦዲተሮች ሊያውቋቸው ስለሚገቡ ጉዳዮች የንድፈ-ሀሳብና የተግባር ትምህርት ተሰጥቷል፡፡
የስልጠናው መሰጠት ኦዲተሮች በቀጥታ የባለስልጣኑን መረጃ በማግኘት የኦዲት ስራቸውን እንዲያከናውኑ በማገዝ በመረጃ ተደራሽነት ላይ የነበረውን ችግር እንደሚፈታ ይታመናል፡፡
በስልጠናው ተካፋይ የሆኑት ወ/ት ብስኩት ለገሰና አቶ አድነው አማዶ ስልጠናው በመረጃ አስተዳደር ስርአቶቹ ላይ ግንዛቤ እንዲጨብጡ እንዳደረጋቸውና በቀጣይ ለሚኖራቸው ስራ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው አስረድተዋል፡፡
ስልጠናው በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አዘጋጅነት ለ35 ኦዲተሮች በሁለት ዙር በገቢዎችና ጉምሩክ መ/ቤት ባለሙያዎች በመሠጠት ላይ ሲሆን መስከረም 26/ 2009 ዓ.ም ይጠናቀቃል፡፡
በሀገር ውስጥ ገቢ እና በጉምሩክ ስርአት አስተዳደር ዙረያ ለኦዲተሮች ስልጠና ተሰጠ
