News

“መ/ቤቱ በሕገ መንግስቱ የተደነገገው የግልጽነትና የተጠያቂነት አሰራር እንዲሰፍን እየሰራ ነው”

“መ/ቤቱ በሕገ መንግስቱ የተደነገገው የግልጽነትና የተጠያቂነት አሰራር እንዲሰፍን እየሰራ ነው”

ክቡር ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ

* የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሰራተኞች የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን፣ የኤድስ ቀንንና የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀንን አከበሩ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሰራተኞች 11ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን “ህገ መንግስታችን ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችንና ለህዳሴችን” በሚል መሪ ቃል ህዳር 23 ቀን 2009 ዓ.ም በመ/ቤቱ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተለያዩ ዝግጅቶች አከበሩ፡፡

_dsc0028ስነስርዐቱ መክፈቻ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ባደረጉት ንግግር የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግስት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የተዛባ የበፊት ታሪካቸውን አርመው፣ በጎውን ታሪካቸውንና የአብሮነታቸውን ልምድ አበልፅገው በፍትህዊነት፣ በመከባበርና በመፈቃቀድ የጋራ የመልማትና የማደግ ፍላጎታቸውን በዴሞክራሲያዊ አግባብ ለማሣካት ቃል የገቡበት የጋራ የቃል ኪዳን ሰነድ መሆኑን እና ሕገ መንግስቱ የጸደቀበት ቀንም በግንቦት 1983 ዓ.ም ለተገኘው አዲስ ተስፋና ድል ዋስትና መስጠት የተቻለበት የስኬት ብስራት ቀን መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ክቡር ዋና ኦዲተሩ አያይዘውም የሕገ-መንግስቱን ዓላማዎች በአግባቡ በመገንዘብ፣ ሕገ መንግስታዊ መብትና ግዴታን በመረዳት እንዲሁም የሕገ-መንግስቱን መልካም ፍሬዎች በማወቅ የመንግስት አሰራር በግልጸኝነትና በተጠያቂነት አግባብ እንዲፈጸም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የበኩሉን ሚና መጫወት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በበአሉ አከባበር ወቅት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ “የተጠያቂነትና ግልፀኝነት አሰራርን በማጠናከር ህገ መንግስታዊ ስርዐቱን ለማጎልበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሚና” በሚል የተዘጋጀ የውይይት መነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡

ክብርት ዋና ኦዲተሯ ባደረጉት ገለጻ በ1987 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በፈቃዳቸው የሚተዳደሩበትን ህገመንግስት ማጽደቃቸውና ይህንን ተከትሎ ባለፉት 22 ዓመታት ሕገ መንግስቱ ያስገኛቸው በርካታ ውጤቶች በየዘርፉ መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

_dsc0029ክብርት ወ/ሮ መሰረት ሕገ መንግስቱ የግልጽነትና የተጠያቂነት አሰራርን የደነገገ መሆኑን ጠቅሰው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትም ይህን የማረጋገጥ ተልዕኮ ይዞ እየሰራ እንደሆነና ሁለተኛውን የአምስት አመት ስትራቴጂክ እቅድ አዘጋጅቶ ለሁሉም ፈጻሚ ግልጽ በማድረግ እየተተገበረ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ አንጻር በፌዴራል መንግስት መ/ቤቶች ውስጥ ተጠያቂነትና ግልጽነትን በማስፈን መልካም አስተዳደርን ለማረጋገጥ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ዋነኛ አጋዥ ኃይል መሆኑን በመገንዘብ ሰራተኛው ለዚህ ተልዕኮ በይበልጥ ሊዘጋጅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተለይም ስትራቴጂክ እቅዱን መነሻ በማድረግ እስካሁን የተገኙ ውጤቶችን በማስጠበቅ፣ የክዋኔ ኦዲት ሽፋንን በማሳደግ፣ የኦዲት ጥራትን በማሻሻል፣ የሰራተኛውን አቅም በመገንባት፣ የኦዲት ማሻሻያ አስተያየቶች መተግበራቸውን በማረጋገጥ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና አስተዳደርን በማሻሻል ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡      

በዕለቱ የመ/ቤቱ ሰራተኞች ከኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ጎን ለጎን ዓለም አቀፍ የኤድስ ቀንና የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀንን ጨምረው አክብረዋል፡፡

_dsc0068በየአመቱ ህዳር 22 ቀን የሚከበረው ዓለም አቀፍ የኤድስ ቀን በሀገራችን ለ29ኛ ጊዜ “አሁንም ትኩረት ለኤች.ኤ.ቪ መከላከል” በሚል መሪቃል የተከበረ ሲሆን የስራ አካባቢ ደህንነትና ጤንነት ባለሙያ የሆኑት አቶ ታመነ ጌታሁን ቫይረሱ በሀገራችን ስላለው ስርጭት፣ በይበልጥ ለቫይረሱ ተጠቂ ስለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ስለኤድስ በሽታ ምንነት፣ ስለቫይረሱ መተላለፊያና መከላከያ መንገዶች፣ በሽታው ስለሚያደርሰው ተጽዕኖ፣ ስለምርመራና ህክምና እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ገለጻ አድርገዋል፡፡

 

_dsc0072በተመሳሳይ ሁኔታም ከህዳር 16 – ታህሳስ 1 ቀን ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የጸረ-ጾታዊ ጥቃት ቀን (የነጭ ሪባን ቀን) በሀገራችን ለ11ኛ ጊዜ “በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የኃይል ጥቃቶችን በመከላከልና በማስቆም የህዳሴ ለውጥን ዘላቂነት እናረጋግጥ!” በሚል ሀገራዊ መሪ ቃል ተከብሯል፡፡ በወቅቱ የስርአተ ጾታ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ገዛኸኝ ሙሊሳ በበዓሉ ታሪካዊ አመጣጥ፣ በጾታዊ ጥቃት መገለጫዎች፣ በጥቃቱ ሰለባዎች ማንነት፣ ጥቃቱ በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች፣በሚፈጸምበት ምክንያትና በሚያስከትለው ጉዳት፣ጥቃቱን ለማስወገድ መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎችና ከጾታዊ ጥቃት ጋር በሚገናኙ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በኤች.አይ.ቪ ኤድስና በጾታዊ ጥቃት ላይ በቀረቡት ገለጻዎች ላይ ክቡር ዋና ኦዲተሩ በሰጡት ማጠቃለያ የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ የለም የሚል የተሳሳተ አመለካከት እየተፈጠረና ስርጭቱም ዳግም እያንሰራራ እንደሚገኝ በመግለጽ በተለይ ከስራ ባህሪያቸው ጋር ተያይዞ ለበሽታው ሊጋለጡ የሚችሉ የመ/ቤቱ ሰራተኞች ይበልጥ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸው  አሳስበዋል፡፡ ጾታን መሰረት አድርጎ ከሚፈጸም ሀይል ጥቃት ጋር በተያያዘም ወንዶች በሴቶች ላይ የሚፈጽሙትን የሀይል ጥቃት ለማቆምና ጥቃቱ ሲፈጸም ዝም ላለማለት ቃል መግባት እንዳለባቸው ከዚህ ባለፈም ስለጾታዊ ጥቃት ምንነት ላካባቢያቸው ማህበረሰብ ማስተማር እዳለባቸው ዋና ኦዲተሩ አስገንዝበዋል፡፡

_dsc0047

 

 

 

 

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *