News

ህግን አክብረው በማይሰሩ አካላት ላይ የራሱን እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አሳወቀ

በቀጣዩ በጀት አመት ሁሉም ተቋማት የወጡ ህጎችንና የተዘረጉ አሰራሮችን በአግባቡ በመተግበር ከኦዲት ግኝት ነጻ ለመሆን መስራት እንደሚገባቸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ አሳሰቡ፡፡ ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ይህንን ያሳሰቡት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከሰኔ 11-13/2010 ዓ.ም ድረስ ከፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች የፋይናንስ አስተዳደር ኃላፊዎች፣ የግዥና የንብረት አስተዳደር የስራ ኃላፊዎችና የውስጥ ኦዲት ኃላፊዎች ጋር በኦዲት ግኝቶች ዙሪያ ለመወያየት ባዘጋጀው መድረክ ላይ ነው፡፡

በመድረኩ መክፈቻ ላይ ክቡር አቶ ገመቹ መ/ቤቱ በሚያከናውናቸው የፋይናንሻል ኦዲቶች በኦዲት ተደራጊ ተቋማት ውስጥ በፋይናንስ አስተዳደር፣ በግዥ አፈፃፀምና በንብረት አስተዳደር በኩል በርካታ ግኝቶች እየተገኙ እንዳሉና መጠናቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደሆነ ገልፀው የሚደረጉ ኦዲቶች እሴት የሚጨምሩና ፋይዳ ያላቸው እንዲሆኑ ስህተቶችን በማረም ወደትክክለኛው ስርአት መምጣት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የኦዲቱ ውጤት የፋይናንስ ስርአቱ እንዲጠናከርና ህግና ስርዓት ተጠብቆ እንዲሰራ ማስቻል እንደሆነም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በ2011 በጀት ዓመት ኦዲት ተደራጊ ተቋማት ተገቢውን ማስተካከያ በማድረግ የፋይናንስና የግዥ አዋጆችና መመሪያዎችን እንዲሁም ሌሎች ተጓዳኝ የአሰራር ስርዓቶችን ተከትሎ በመስራት ከኦዲት ግኝት ነፃ ሆነው መስራት በሚችሉበት መንገድ ላይ ከተቋማቱ የፋይናንስ፣ የግዥና የንብረት አስተዳደር እንዲሁም የውስጥ ኦዲት ክፍሎች ኃላፊዎች ጋር ለመወያየት መድረኩ በዋናት እንደተዘጋጀ ክቡር አቶ ገመቹ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የኦዲት ግኝቶች የሚመነጩበትን ብሎም ተገቢውን የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ያልተቻለበትን ምክንያት ለማወቅና በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኩል ሊሰጡ የሚችሉ ድጋፎችን ለመለየት መድረኩ እንደተዘጋጀ አክለው ገልጸዋል፡፡
ክቡር ዋና ኦዲተሩ በተቋማት ውስጥ ግኝቶች እንዲከሰቱ እንዲሁም ግኝቶቹን አስቀድሞ መከላከል እንዳይቻል እያደረጉ ያሉ ጉዳዮችን የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዲገልጹ በጠየቁት መሰረት ተሳታፊዎች ምክንያት ናቸው ያሏቸውን ጉዳዮች ያቀረቡ ሲሆን በፋይናንስ፣ በንብረት አስተዳደርና በግዥ እንዲሁም በውስጥ ኦዲት በኩል ያሉ ተያያዥ ጉዳዮች ላይም ጥያቄዎችና አስተያየቶችን አንስተዋል፡፡
በተሰጠው አስተያየትም በፋይናንስ፣ በግዥና በንብረት አስተዳደር በኩል ሥራውን በዕውቀት የሚመራና የሚሰራ በቂ እውቀትና አቅም ያለው ሠራተኛ አለመኖሩ እንዲሁም የተቋማቱን ስፋት በሚመጥን ልክም የስራ ክፍሎቹ በመዋቅርና በሰው ሀይል የተደራጁ አለመሆኑ ለግኝቶች እንደ መንስኤ ተገልጿል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም ለፋይናንስ፣ ለግዥና ለንብረት አስተዳደርና ለውስጥ ኦዲተሮች ያለው የደመወዝና የጥቅማ ጥቅም ክፍያ አነስተኛና የማይስብ በመሆኑ ሠራተኞች በየወቅቱ የሚለቁ በመሆኑ ለችግሩ አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተጠቅሷል፡፡ የሰው ሀይሉ ችግር እስካልተፈታ ድረስም ግኝቶች ሊቀጥሉ ይችላሉ የሚል ስጋት በተሳታፊዎች በኩል ተንጸባርቋል፡፡

በተጨማሪም ተቋማት በዕቅድ አለመመራታቸው ለኦዲት ግኝቶች መንስኤ ነው በሚል በተሳታፊዎች የተገለጸ ሲሆን ይህም በፋይናንስና ግዥ ላይ ግኝቶች እንዲፈጠሩ እንዳደረገ ተጠቁሟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፋይናንስ ክፍል ኃላፊዎች ከአንዳንድ የበላይ አመራሮች የሚቀርቡ ተገቢ ያልሆኑ ጥያቄዎችን ላለመቀበል ፍርሀት የሚያድርባቸው በመሆኑ ጥያቄውን ተቀብለው በሚፈጽሙት ድርጊት የተነሳ ግኝቶች እንደሚፈጠሩ ተጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የክፍያ ስርዓት ያልወጣላቸው ጉዳዮች መኖራቸውና የውሎ አበል ክፍያ አነስተኛ በመሆኑ ከፋይናንስ ህግ ውጪ እየተከፈለ መሆኑ የኦዲት ግኝቶች እንዲገኙ እያደረጉ ምክንያት ሆኗል፡፡
በንብረት አያያዝ በኩል ንብረቶችን ለማስወገድ የሚቋቋሙ ኮሚቴዎች ዝቅተኛ የጨረታ መነሻ ዋጋ አሳንሰው እንዳይገምቱ በመፍራት ከፍተኛ ግምት በማቅረባቸው ገዥዎች ንብረቱን መግዛት ባለመቻላቸው ንብረቶች አለመወገዳቸው፤ ሊብሬና የሞተር ቁጥራቸው የማይናበብና የኋላ ታሪካቸው የማይታወቅ ተሽከርካሪዎችን ማስወገድ አለመቻሉ እንዲሁም ኬሚካሎች የሚወገዱበት አሠራር አለመኖሩና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ እቃዎችንም ለማስወገድ በሚመለከተው አካል ፈጣን ምላሽ አለመሰጠቱ በንብረት አወጋገድ በኩል ላሉ የኦዲት ግኝቶች መንስኤ ናቸው በሚል ቀርበዋል፡፡
በግዥ ረገድ ግዥ በዕቅድ አለመከናወኑ፣ ከገንዘብ ምንዛሪ መስተካከል በኋላ አቅራቢዎች የዋጋ ማስተካከያ ካልተደረገ አናቀርብም በማለታቸው ወደ አፋጣኝ ግዥ እየተገባ መሆኑ፤ የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ኃላፊነቱን እየተወጣ ባለመሆኑና አቅራቢዎች በዓመቱ መጨረሻ ላይ ወይም አዘግይተው ዕቃ በማቅረባቸው እንዲሁም በማዕቀፍ ግዥ የማይካተቱ ዕቃዎች፣ ገበያ ላይ ደረሰኝ የማይገኝላቸው እቃዎች፣ ካለ ዕቅድ የሚመጡ ግዥዎች መመሪያ የሌላቸው መሆኑ ለግኝቶች መንስኤ ናቸው ብለዋል፡፡
በውስጥ ኦዲት በኩል የውስጥ ኦዲት ባለሙያዎች ግኝቶችን ቀድሞ በማሳየት እርምጃ እንዲወሰድ የመከታተልና የመደገፍ ስራ ቢሰሩም በተቋማቱ የፋይናንስና ሌሎች ባለሙያዎች እጥረት በመኖሩ መፍታት አለመቻሉና በኢፍሚስ ስርአት ችግር የተነሳ የፋይናንስ ሪፖርቶች በአግባቡ ተጠቃለው ባለመድረሳቸው ችግሮች እየተፈጠሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡

በነዚህና በተነሱ በሌሎች በርካታ ጉዳዮች ላይ ክቡር ዋና ኦዲተሩ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ክቡር አቶ ገመቹ ከተሳታፊው የቀረቡ ምክንያቶች ባብዛኛው ችግሮቹን ወደውጭ የመግፋት ሁኔታ እንደታየባቸው ገልጸው በፋይናንስ፣ በግዥና በንብረት አስተዳደር በኩል ያለው ሰው ሀይል ችግርና የአበል ማነስ ጉዳይ የሚታወቅ እንደሆነ ነገር ግን እነዚህ ምክንያቶች ያለው ሰራተኛ ስራውን በአግባቡ እንዳይሰራ ምክንያት ሆነው መቅረብ የለባቸውም ብለዋል፡፡
ሰራተኞችን በማብቃት የአቅም ክፍተቶችን መሙላት እንደሚያስፈልግ፣ ችግሮቹን ወደራስ ወስዶ ባለው የውስጥ አቅም ለማረም መስራት እንደሚያሻ፣ ከዚህ በተጨማሪም በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በሚሰጡ የማሻሻያ ሀሳቦች መሰረት እርምጃ መውሰድ ግዴታ እንደሆነ፣ የበላይ ሀላፊዎች ለሚያቀርቡት ያልተገባ ጥያቄ አሉታዊ ምላሽ መስጠትና ራስንም ሆነ ኃላፊዎችን ከስህተት መጠበቅ እንደሚገባ፣ ሁሉም ሰራተኛ በየደረጃው ያለበትን ሀላፊነት መወጣት እንዳለበትና ሀላፊነትን አለመወጣትም ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ክቡር ዋና ኦዲተሩ ገልጸዋል፡፡
ክቡር ዋና ኦዲተሩ በተቋማት ውስጥ የኦዲት ግኝት መንስኤ የሆኑ ጉዳዮች ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የመፍትሄ ሀሳብ ለመንግስት ማቅረቡን የገለጹ ሲሆን በአሰራር ችግር እያስከተሉ ያሉ ጉዳዮችን ኦዲት ተደራጊ አካላት እንዲፈቱ የራሳቸውን ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል፡፡
ያለበቂ ምክንያት በኦዲት ግኝቶች ላይ የድርጊት መርሀግብር በማይልኩና እርምጃ ወስደው በማያሳውቁ ተቋማት ላይ በማቋቋሚያ አዋጁ በተሰጠው ስልጣን መሠረት ከ2011 በጀት አመት ጀምሮ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር በመግለጽ ሁሉም ኃላፊና ሰራተኛ ህግን አክብሮና አሰራሩን ጠብቆ መንቀሳቀስ እንዳለበት፤ ተቋማትም የተጠያቂነት አሰራርን ማስፈን እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡
ክቡር አቶ ገመቹ በቀጣይ ከየተቋማቱ የበላይ አመራሮችና ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጋር በመድረኩ በተነሱ ጉዳዮች ላይና በኦዲት ግኝቶች ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግ አሳውቀዋል፡፡ በመድረኩ ላይ ከተለያዩ የፌዴራል መንግስት መ/ቤቶችና ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተገኙ የፋይናንስ፣ የግዥ፣ የንብረት አስተዳደርና የውስጥ ኦዲት ኃላፊዎች ተካፍለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *