ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ

የዋና ኦዲተር መልዕክት

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 101 እና በማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 982/2008 እንዲሁም በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1146/2011 መሰረት የተሰጡትን ተግባርና ኃላፊነቶች  ለመወጣት ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

የመ/ቤቱ ተጠሪነት ለኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሲሆን የህዝብና የመንግሥት ሀብትና  ንብረት በአግባቡ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል እና ይህንን ተግባር የመፈጸምና የማስፈጸም ተልዕኮ የተሰጣቸው የመንግሥት ተቋማትም ለተግባራዊነቱ በመትጋት ግልፅነትና ተጠያቂነትን እንዲሁም  መልካም አስተዳደርን ሊያሰፍን የሚችል አሠራር እንዲከተሉ ለማድረግ ተልዕኮውን በመወጣት ላይ ይገኛል::

በፌዴራል መንግስት ተቋማት እና ድርጅቶች ላይ የፋይናንሽያል፣ የክዋኔ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ የቁጥጥር፣ ልዩ ኦዲቶችንና ሌሎች ኦዲቶችን በማድረግ የተቋማቱ  አሠራሮች በህግ አግባብ እንዲከናወኑና እንዲመሩ እንዲሁም በየዘርፉ የሚታዩ የኦዲት ግኝቶች በወቅቱ እንዲታረሙ የማድረግ ተልዕኮውን እየተወጣ ይገኛል፡፡

ለተልዕኮው ስኬታማነትም የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትን ጨምሮ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመስራት በርካታ የኦዲት ግኝቶች በየደረጃቸው እንዲታረሙና አጥፊዎችም በሚመለከታቸው የፍትህ አካላት አማካይነት በህግ አግባብ እንዲጠየቁ ማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ተጨባጭ እና ተአማኒ መረጃዎችንና ማስረጃዎችን በማመንጨት ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው አስተዋጽኦዎችን እያበረከተ ነው፡፡

መ/ቤቱ ስራውን በብቃት ለመወጣት የሚያስችለውን የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት፣ ዘመኑ የሚጠይቀውን የዘመናዊ ቴክኖሎጂ ግብአት በየወቅቱ በሟሟላትና የመ/ቤቱን አመራርና ሠራተኞች ሙያዊ ዕውቀት ለማዳበር የሚያስችሉ ተቋማዊ እንዲሁም የሀገር ውስጥና የውጭ ስልጠናዎችን በማመቻቸት ስራውን ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

የተቋሙ የኦዲት ስራ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና የተለያዩ የዓለም አቀፍ የኦዲት ስራ ሰታንዳርዶችን ያሳለጠ እንዲሆን ከተለያዩ የአለም አቀፍ የኦዲት ተቋማት ጋር ያለውን የትብብር አሠራር እያጠናከረ ይገኛል፡፡ ለዚህም ከእንግሊዝኛ ተናጋሪ የአፍሪካ ሀገሮች ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ማህበር (Afrisai-E) ጋር እያከናወነ ያለው ተግባር በዋቤነት የሚጠቀስ ነው፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በየዓመቱ የሚያካሂዳቸው የኦዲት ሪፖርቶች ብቻቸውን ውጤት ስለማያመጡ ከዚህ በፊት ሲያደርግ እንደነበረው ከኦዲት ተደራጊ መ/ቤቶች ጋር ያለውን ግኝኙነት እና የሥራ ትብብር አጠናክሮ በመቀጠል በተለይም በኦዲት ሥራ ላይ ቀጥተኛ ግንኙነት ካላቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ግንኙነትም አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የመገናኛ ብዙሃንም በህብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ከመፍጠርና ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ ከማድረግ አኳያ ጉልህ ሚና የሚጫወቱ በመሆኑ በጋራ ተቀናጅቶ መስራቱ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

በየአምስት ዓመቱ የሚከልሳቸውን ወቅታዊውን የተቋሙን እንቅስቃሴ ታሳቢ ያደረጉ ስትራቴጂያዊ ዕቅዶችን መሰረት ያደረጉ ዓመታዊ ዕቅዶቹን መላውን ሠራተኛ ባሳተፈ መልኩ በማዘጋጀትና አፈጻጸማቸውንም በመገምገም ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወንም ጥረት ያደርጋል፡፡ በዚህም መሠረት ባለፉት ተከታታይ 8 ዓመታት ባደረግናቸው ጠንካራ ጥረቶች የፋይናንስና ህጋዊነት ኦዲቱን ሽፋን ወደ 100% እንዲሁም የክዋኔ ኦዲት ሽፋኑን በአማካኝ ወደ 30% ማሳደግ ተችሏል፡፡

በአሁን ሰዓትም ከ2013 እስከ 2018 በጀት ዓመት ተግባራዊ የሚሆን ተቋማዊ ስትራቴጂያዊ ዕቅድ በመንደፍና ይህንኑ ወደ ዓመታዊ ዕቅዶች በማውረድ አመርቂ አፈጻጸም እያስመዘገበ ይገኛል፡፡

ለዚህም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አማካይነት የኦዲት ተደራጊ ተቋማት የኦዲት ግኝቶችን በተመለከተ በየጊዜው የሚካሄዱ ይፋዊ የህዝብ መድረክ ውይይቶችና ከውይይቶቹም እየተገኙ ያሉ ግብረ መልሶች ለውጤታማ አፈጻጻሙ ማሳያ ተደርገው የሚወሰዱ ናቸው፡፡

ባለፉት ዓመታት በኦዲት ስራው ላይ ውጤታማ ስኬቶች እያስመዘገበ ያለው መ/ቤቱ በዕቅድ አፈጻጸሙ ላይ የሚገጥሙትን የተለያዩ ተግዳሮቶች በመቅረፍ እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመመካከር የመፍትሔ እርምጃዎችን በመውሰድ ለውጤት መብቃቱ በመላው የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች ያላሰለሰ ጥረትና ቁርጠኝነት የተሞላበት አፈጻጸም በመሆኑ መላው የተቋሙ ማህበረሰብ ሊኮራበት የሚገባ ነው፡፡

ወደፊትም በዕቅድ አፈጻጸማችን ላይ ሊገጥሙ በሚችሉ የአሠራር ተግዳሮቶች ላይ ቀድሞ በመዘጋጀትና የመፍትሔው አካል በመሆን የበለጠ ስኬት እንደምናስመዘግብ እመነቴ የፀና ነው፡፡

መ/ቤቱ ከተጣለበት የህዝብንና የሀገርን ሀብት ከብልሹ አሠራርና ከብክነት የመጠበቅ ታላቅ ሀገራዊ አደራና ተልዕኮ እንዲሁም ለሌሎች የጥሩ አፈጻጸም ምሳሌ ከመሆን አንጻር የእያንዳንዱ የተቋሙ አመራርና ሠራተኛ እንቅስቃሴም ከብልሹ አሠራር እና ከዳተኝነት የጸዳ እና የበለጠ ፍጹም በሆነ ሙያዊና ሞራላዊ ስነ-ምግባር የታነጸ እንዲሆን አደራዬን አስተላልፋለሁ፡፡

 

አመሰግናለሁ፡፡

መሠረት ዳምጤ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር