News

የተጠያቂነት ስርዐትን ማስፈን ከቋሚ ኮሚቴው የሚጠበቅ ቀዳሚው ተግባር እንደሆነ ተገለጸ

ኦዲትን መሰረት በማድረግ የተጠያቂነትን ስርዐት ማስፈን ከኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚጠበቅ ቀዳሚው ተግባር እንደሆነ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ገለጹ፡፡ ክብርት ወ/ሮ መሰረት ይህን የገለጹት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከታህሳስ 1-2/2014 ዓ.ም ድረስ በባህርዳር ከተማ ለቋሚ ኮሚቴው አባላት ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ላይ ነው፡፡

በስልጠናው ወቅት “ተጠያቂነት እንዲሰፍን እንፈልጋለን” ያሉት ክብርት ምክትል ዋና ኦዲተሯ በየደረጃው ያለው አመራር ኃላፊነቱን እንዲወጣ ለማድረግ እንዲሁም ተጠያቂ መሆን የሚገባውን አካል ተጠያቂ ለማድረግ የኦዲት ግኝትን መሰረት ያደረገ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ ከተቻለ እየታዩ ያሉ የኦዲት ግኝቶች እንደሚቀንሱ በመጥቀስ ቋሚ ኮሚቴው ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ቀዳሚ ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ መንግስት ለህዝብ አስተዳደር፣ ለልማት ስራዎችና ለልዩ ልዩ ጉዳዮች የሚመድበው ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉንና የሚፈለገውን ውጤት ማምጣቱን እንዲሁም ያቋቋማቸው አስፈጻሚ የመንግስት አካላት ተልዕኳቸውን ማሳካታቸውን የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሀገሪቱን በጀት የሚያጸድቅ፣ ህጎችን የሚያወጣና የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን በበላይነት የሚቆጣጠር ከፍተኛው የመንግስት የስልጣን አካል በመሆኑ የቁጥጥርና የክትትል ሚናውና ኃላፊነቱ እጅግ ከፍተኛ ነው ያሉት የተከበሩ አቶ ክርስትያን በምክር ቤቱ ውስጥ ከተቋቋሙ አካላት ውስጥ ደግሞ በተለይ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዚህ ረገድ ልዩ የሆነ ኃላፊነት ተጥሎበታል ብለዋል፡፡

በዚህም ቋሚ ኮሚቴው በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ኦዲቶች ላይ በመመስረት የኦዲት ግኝት ያለባቸው ተቋማት ከኦዲት ግኝት እንዲወጡና በኦዲት ግኝቶች ላይ ፈጣን እርምጃ እንዲወስዱ የመደገፍ፣ የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት ያሉ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም በኦዲት ግኝት ላይ እርምጃ የማይወስዱ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ የበኩሉን ሚና መጫወት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ምክር ቤቱ ለኦዲት ግኝት የተለየ ትኩረት ሰጥቶ በአስፈጻሚ አካላት ላይ የሚካሄደው የድጋፍ፣ የቁጥጥር፣ የክትትል ስራ እንዲሁም ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የማስፈን ተግባር ዘላቂና ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲተገበር አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል በማለት ተናግረዋል፡፡

በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ በአዲስ መልክ የተቋቋመው የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ይህንን ታሪካዊና ሀገራዊ ከባድ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት እንዲችል በኦዲት ስራ፣ በመንግስት ሀብት አስተዳደርና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ በቂና ወደ ስራ ሊያስገባ የሚያስችል ግንዛቤ አስቀድሞ ሊጨብጥ የሚገባው በመሆኑ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተዘጋጀው ስልጠና ወቅቱን የጠበቀና በጣም አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

በሁለቱ ቀናት መድረክ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትና የገንዘብ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች ለቋሚ ኮሚቴው በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ በስልጠናው የተዳሰሱት ርዕሰ ጉዳዮች የቋሚ ኮሚቴው አሰራርና አለም አቀፍ ተሞክሮዎች፣ የኦዲት ግኝቶች ምንነት፣ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው በመንግስት ኦዲት ዙርያ የወጡ አለም አቀፍ ህግጋት፣ የፋይናንስ አስተዳደር የህግ ማዕቀፍ እንዲሁም የኦዲት ምንነትና የፓርላማ ሚና ናቸው፡፡

በመድረኩ ከግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው በተጨማሪ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የ2013/2014 በጀት አመት እቅድ ለቋሚ ኮሚቴው አካላት ቀርቦ ግብረ መልስ ተሰጥቶበታል፡፡

እቅዱን ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረቡት ምክትል ዋና ኦዲተሯ ክብርት ወ/ሮ መሰረት በኦዲት እና በድጋፍ ዘርፍ በተያዙት እቅዶች የትኩረት አቅጣጫዎች እና በሌሎች የእቅዱ ይዘቶች ላይ ገለጻ አድርገዋል፡፡

ክብርት ምክትል ዋና ኦዲተሯ በእቅዱ መሰረት በ2013 በጀት ዓመት የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች የሆኑ 187 መ/ቤቶች እና 54 ቅርንጫፎች ላይ የፋይናንሻል ኦዲት በማድረግ 100 ፐርሰንት የፋይናንሻል ኦዲት ሽፋን ለማስቀጠል፤ በክዋኔ ኦዲት ረገድም 24 አዳዲስ እና 4 የክትትል ኦዲቶችን በማድረግ በድምሩ 28 የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቶችን ለማውጣት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *