የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እንዲሁም የክልልና የከተማ አስተዳደሮች ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች በ2013 በጀት አመት የነበራቸውን የስራ አፈጻጸም ከነሀሴ 22-23/2013 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ ገመገሙ፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ባዘጋጀው የምክክር መድረክ መክፈቻ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ባደረጉት ንግግር በፌዴራልና በክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች መካከል ወቅታዊና ተከታታይ የሆነ የግንኙነት መስመር በመዘርጋት የጋራ ተልዕኳቸውን በማሳካት የሀገር ሀብት በወጡት ህጎች በአግባቡ በስራ ላይ መዋሉንና የተቋማት የተልዕኮ አፈጻጸም ውጤታማ በሆነ መልኩ መፈጸሙን በማረጋገጥ በድምር ውጤቱም መልካም አስተዳደር በሀገሪቱ እንዲሰፍን የበኩላችንን ሚና ልንወጣ ይገባል በማለት አስገንዝበዋል፡፡ ምክትል ዋና ኦዲተሯ አክለውም በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትና በክልልና በከተማ አስተዳደሮች የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች መካከል ያለው ግነኙነት በሀገር አቀፍ ደረጃ ጠንካራ የኦዲት ስራን የሚፈጥርና ተመጣጣኝ የሆነ ኦዲት የማድረግ አቅም ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እና የስምንት ክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በውይይቱ በኦዲት ሽፋንና ጥራት፣ በባለድርሻ አካላት ተሳትፎ፣ በአቅም ግንባታ ስራዎች እና በሌሎችም አፈፃፀሞች ዙሪያ ልምድ ሊወሰድባቸው ይገባል የተባሉ መልካም ተሞክሮዎች ቀርበዋል፡፡ በስራ አፈፃፀም ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችም ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ነጻነታቸውን አረጋግጠው መስራት በሚችሉበት፣ የኦዲት ሽፋንና ጥራትን በሚያሳድጉበት፣ እርስ በርስ በሚደጋገፉበት፣ እንዲሁም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በሀገር አቀፍ ደረጃ የኦዲት ስራው እንዲጠናከር ለክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ድጋፍ በሚሰጥበት አግባብ ላይ ሀሳቦች ቀርበው ውይይት ተደርጓል፡፡
ከዚህም ሌላ ስድስተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ ተከትሎ በቀጣይ በፌዴራልና በክልል ደረጃ በሚቋቋሙ ምክር ቤቶች ውስጥ የኦዲትን ጉዳይ የሚከታተል አካል በሌለባቸው ክልሎች እንዲቋቋም የዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ውይይት ተደርጓል፡፡
በፌዴራል መንግስት ለክልል መንግስታት የሚሰጠውን የድጋፍና ድጎማ በጀት ኦዲት ከማድረግ አኳያ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትና በክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች መካከል የሚኖረውን የኦዲት ስራ ድግግሞሽ ለማስቀረት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጸደቀው የነጠላ ኦዲት አዋጅ ዙርያ በቀጣይ ለመወያየት ተወስኗል፡፡
ከመድረኩ መጀመር አስቀድሞ በሲዳማ ክልላዊ ብሔራዊ መንግስት ዋና ኦዲተር መ/ቤት አስተባባሪነት የስብሰባው ተሳታፊዎች በታቦር ተራራ ላይ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል፡፡