የስራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እና የመ/ቤቱ የድጋፍ ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ ባዩሽ ተስፋዬ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም የመ/ቤቱ አመራሮችና ሠራተኞች በተገኙበት መጋቢት 17 ቀን 2013 ዓ.ም የክብር አሸኛኘትና ምስጋና ተደርጎላቸዋል፡፡
በዕለቱ በተካሄተደው የሽኝትና የምስጋና መርሀ ግብር ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የመ/ቤቱ የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እና ክብረት ወ/ሮ ባዩሽ ተስፋዬ በመ/ቤቱ ቆይታቸው ሀገራቸውን እና ህዝባቸውን በላቀ የኃላፊነት ስሜት ከማገልገል ባለፈ መ/ቤቱን አሁን ለደረሰበት የስኬት ደረጃ እንዲበቃ ያደረጉ በመሆኑ በተቋሙ ታሪክ ጭምር ይታወሳሉ ብለዋል፡፡
ሁለቱ አመራሮች በነበራቸው የሥራ ዘመን ህግና ሥርዓት እንዲከበር፣ የባከነና የጠፋ የመንግስትና የህዝብ ሀብት እንዲመለስ እንዲሁም በአጥፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ወጥ፣ ቁርጠኛና ጠንካራ አቋም በማሳየት የግልፅነትና የተጠያቂነት ሥርዓት እንዲሰፍን መታገላቸውን ክብርት ወ/ሮ መሠረት ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ አቶ ገመቹ ወደ ተቋሙ ሲመጡ በዓመት 32 በመቶ የነበረው የፋይናሺያል ኦዲት ሽፋን በተሰራው ጥረት የታከለበት ጠንካራ አሠራር 100% መድረሱን እና የክዋኔ ኦዲትም በዓመት በአማካይ ከነበረበት 2 የኦዲት አፈጻጸም ሽፋኑን በፍጥነት በማሳደግ ወደ 24 እንዲሁም የክትትል ኦዲት አፈጻጸምን ወደ 6 ማድረስ መቻሉን ያብራሩት ክብርት ወ/ሮ መሠረት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኦዲት ለማድረግ የሚያስችል የሙከራ ስራ መጀመሩንም በንግግራቸው ጠቅሰዋል፡፡
መ/ቤቱም በአፍሪካ ካሉ ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች አንዱ እንዲሆንና ሀገሪቱ የምስራቅ አፍሪካ አቻ የኦዲት ተቋማት አባል እንድትሆን በርካታ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ጨምረው የገለጹት ክብርት ወ/ሮ መሠረት በተቋሙ ዓለም አቀፍ የኦዲት ስታንዳርድን መሠረት ያደረገ የአሠራር ሥርዓትና ማኑዋል እንዲተገበር፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መሠረተ ልማት ግንባታን በማጠናከር የወረቀት አልባ የመረጃ መለዋወጫ ቴክኖሎጂ ተፈጻሚ እንዲሆንና ምቹ የሥራ አከባቢ እንዲፈጠር ከማስቻል ባለፈም ተቋሙ ከውጫዊ ተጽዕኖዎች ነጻ ሆኖ ሙያዊ ሥራ እንዲሠራ አመራሮቹ ያላሰለሰ ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሐመድ የሱፍ በበኩላቸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በሥራው በምክር ቤቱ ከየትኛውም ተቋም የተለየና የተሻለ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን አውስተዋል፡፡
ምክር ቤቱ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን ለማስፈን በሚያደርገው ጥረት ውስጥ መ/ቤቱ የሚያከናውነው ጠንካራ የኦዲት አሠራር ለፓርላማውም ሆነ ለቋሚ ኮሚቴው ትልቅ አቅም የፈጠረ መሆኑን አክለው የጠቀሱት የተከበሩ አቶ መሐመድ ለዚህ ደረጃ መድረስ የክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እና የክብርት ወ/ሮ ባዩሽ ተስፋዬ ሚና የጎላ ነበር ብለዋል፡፡
በሽኝት መርሃ-ግብሩ የተገኙ የተቋሙ ሠራተኞች በሰጡት አስተያየትም ከሁለቱ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የመስራት ዕድሉን በማግኘታቸው ደስተኞች እንደነበሩ እና በቆይታቸውም መልካምና ጠንካራ የሥራ ባህልን እንዲያዳብሩ፣ተቋማቸውን እና ሀገራቸውን ወደው እንዲሠሩ እንዳደረጓቸው ምስክርነታቸውን ሰጥተው አመራሮቹ ሁሉንም የተቋሙ ሠራተኞች በእኩል በማየትና በማስተባበር መ/ቤቱን አሁን ለደረሰበት ደረጃ ያደረሱ በመሆናቸው ወደ ፊት መልካም ዕድል እንዲገጥማቸው ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
የአፍሪካ እንግሊዝኛ ተናጋሪ ዋና አዲተር መ/ቤቶች ማህበር (AFROSAI-E) የክቡር ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶን የዋና ኦዲተርነት የአገልግሎት ዘመን ማብቃትና ስንብት አስመልክቶ በስነ ስርዓቱ ላይ በንባብ የቀረበ መልዕክት የላከ ሲሆን ዋና ኦዲተሩ ለማህበሩ የስትራቴጂክ ዕቅድ ግብ መምታትና ለአጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴው መጎልበት ያበረከቱት አስተዋጽኦና ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን በመልዕክቱ ላይ በመጥቀስ ወደፊትም መልካም ዕድል እንዲገጥማቸው ምኞቱን ገልጿል፡፡
ክብርት ወ/ሮ ባዩሽ ተስፋዬ በተደረገላቸው ደማቅ የሽኝት ስነ-ስርዓት ምስጋናቸውን አቅርበው በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በነበራቸው ቆይታ ስራዎችን ከመላው የተቋሙ ሰራተኞች ጋር በትብብር ሲሰሩ በመቆየታቸው ደስተኛ እንደነበሩና በቀጣይም በማንኛውም ሁኔታ ከተቋሙ ጎን ተሳትፏቸው እንደማይለይ አረጋግጠዋል፡፡
ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶም ለተደረገላቸው ሽኝት ምስጋናቸውን አቅርበው ዕድሉን አግኝተው ሀገርን እና ህዝብን በዚህ ደረጃ በማገልገላቸው ደስተኛ እንደነበሩ እና የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለሀገር ዕድገት እንዲሁም ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንዲያበረክት በነበራቸው የስራ ዘመን የበኩላቸውን ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸው ከመ/ቤቱ አመራርና መላው ሰራተኞች እንዲሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ስለተደረገላቸው የትብብር ድጋፍ አመስግነዋል፡፡ አያይዘውም ተቋሙ አሁን ካለበት ደረጃ ሳይወርድ በሀገር ዕድገት ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወት ተቋም ሆና እንዲቀጥል ሁሉም የተቋሙ ሠራተኞች በርትተው ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች ለክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶና እና ለክብረት ወ/ሮ ባዩሽ ተስፋዬ የዋንጫና የወርቅ የአንገት ሀብል ሽልማት ያበረከቱላቸው ሲሆን አቶ ገመቹ ከ12 ዓመታት በላይ በዋና ኦዲተርነት እንዲሁም ወ/ሮ ባዩሽ ተስፋዬ ከ7 ዓመታት በላይ በድጋፍ ዘረፍ ምክትል ዋና ኦዲተርነት መ/ቤቱን ማገልገላቸው በስነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡