የቀድሞው የማዕከላዊ ስታትሰቲክስ ኤጀንሲ የአሁኑ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የዘላቂ ልማት ግቦች መረጃዎች አሰባሰብና አደረጃጀትን በሚመለከት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ባካሄደው የ2012/2013 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት መሰረት የታዩ ግኝቶች ላይ ያተኮረ ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ጥር 23 ቀን 2014 ዓ.ም ተካሄደ፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ቋሚ ኮሚቴው በስብሰባው ላይ ከተገኙት የተቋሙ የስራ ኃላፊዎች ምላሽ የሚፈልጉ የኦዲት ግኝቶችን በዝርዝር አቅርቧል፡፡
በዚህም የዘላቂ ልማት ግቦችን መረጃ በተሟላ መልኩ ለመሰብሰብና ለማደራጀት እንዲሁም ኢላማዎችና አመላካቾችን ለመለየት የሚረዱ መረጃዎችን ለመሰብሰብ የሚያስችል ሥርዓት አለመዘርጋቱና መረጃ መሰብሰቢያ ቅጾችም ተዘጋጅተው በአግባቡ አለመሰራጨታቸውን፣ በሀገሪቱ ካሉ 50 ያህል የብሔራዊ ስታትስቲክስ ስርዓት አባል ተቋማት መካከል ከ5 ተቋማት ብቻ መረጃ መሰብሰቡን፣ ለዘላቂ ልማት ግቦች መረጃ ግብአት ሊሆኑ የሚችሉ የግል ሴክተሮችና ሲቪክ ማህበራት ያልተለዩና መረጃቸውን ለመሰብሰብ የሚረዳ እቅድ ወይም ፕሮግራም አለመዘጋጀቱን ኦዲቱ ማሳየቱ ተገልጿል፡፡
እንደዚሁም በአገልግሎቱም ሆነ በፈጻሚ ተቋማት የሚሰበሰቡ መረጃዎችን በማዕከላዊም ሆነ በአንዳንድ ሴክተር መ/ቤቶች የመረጃ ቋት በአግባቡ አለመደራጀቱንና የመረጃ ትስስርና ቅብብሎሽ ሥርዓትም ያልተዘረጋ መሆኑን ብሎም የስታትስቲክስ መረጃ ማጠቃለያ ሁሉንም ሴክተር መ/ቤቶች ያላከተተና የዘላቂ ልማት ግቦችንና የግብ አመላካቾችን ያልያዘ መሆኑን ኦዲቱ አሳይቷል፡፡
በተጨማሪም ከመንግስት፣ ከግልና ከሲቪክ ማህበራት ሴክተሮች የሚሰበሰቡ ኦፊሺያል የስታትስቲክስ መረጃዎችን ጥራት ለመቆጣጠር የሚያስችል ወቅታዊ የቁጥጥር ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ የጥራት ቁጥጥር ስራው በአግባቡ አለመከናወኑ፣ የዘላቂ ልማት ግቦች አመላካች መረጃዎችን እንዲልኩ በተቋሙ ከተጠየቁ ዘርፍ መ/ቤቶች ውስጥ ከተወሰኑት በስተቀር ሌሎቹ መረጃዎቹን ስለመላካቸው ማስረጃ አለመገኘቱ፣ የዘላቂ ልማት ግቦች መረጃዎችን ለመሰብሰብ፣ ለማደራጀት፣ ለመተንተንና ለማጠቃለል የሚያስችል አደረጃጀት አለመዘርጋቱ ተጠቅሷል፡፡
ከዚህም ሌላ በመንግስት፣ በግልና በሲቪክ ማህበራት ሴክተሮች መረጃዎችን ለሚሰበስቡ ሠራተኞች የእውቀት ክፍተትን መሰረት ያደረገ የአቅም ግንባታ ስልጠና በሚገባው ልክ አለመሰጠቱ እና የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸምን የተመለከቱ አሠራሮችን የማስተዋወቅ ስራ አለመሰራቱ እንዲሁም በኦዲት ናሙናነት በታዩ ሴክተር መ/ቤቶች የሚሰበሰቡ መረጃዎችን ለማደራጀት በባለቤትነት የሚከታተል አደረጃጀት አለመኖሩና ለዚህም አገልግሎቱ ለሴክተሮቹ ድጋፍ አለማድረጉ፣ የመረጃ አሰባሰብ፣ አደረጃጀት፣ አተናተንና አጠቃቀምን በሚመለከት ለመንግስት ሴክተር መ/ቤቶች የተዘጋጀው መመሪያ ለሴክተሮቹ ደርሶ ተግባራዊ መሆኑን ማረጋገጥ አለመቻሉና ለሌሎች የግል ሴክተሮችና የሲቪክ ማህበራት መተግበሪያ መመሪያ ያልተዘጋጀላቸው መሆኑ እንዲሁም የዘላቂ የልማት ግቦች አመላካቾችን በሚመለከት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት መረጃዎች ሳይቆራረጡና ወቅታቸውን ጠብቀው ሊደርሱ የሚችሉበት የክትትልና የግምገማ ሥርዓት ዘርግቶ ተግባራዊ አለማድረግ ችግሮች በኦዲቱ ተመልክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢራቱ ይገዙ እና በውይይቱ ላይ የተገኙ የተቋሙ የስራ ኃላፊዎች ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡ ሲሆን የዘላቂ ልማት ግቦች መረጃዎች አቅርቦቶችን ለማሻሻል አገልግሎቱ በየጊዜው የፕላንና ልማት ሚኒስቴርን ጨምሮ ከተለያዩ አካላት ጋር እየሰራ መሆኑንና የተለያዩ እርምጃዎችንም እየወሰደ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ከብሔራዊ ስታትስቲክስ ሥርዓት አባል ተቋማት መካከል የዘላቂ ልማት ግቦች መረጃን የሚያቀርቡት የተወሰኑት መሆናቸውን የጠቆሙት ኃላፊዎቹ የዘላቂ ልማት ግቦች መረጃ መሰብሰቢያ ቅጽ የሚላከውም ለእነዚህ ቀጥታ መረጃ አቅራቢ ተቋማት ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የተለያዩ የሶሺዮ-ኢኮኖሚ መረጃዎች የሚገኙባቸው የዘላቂ ልማት ግቦች ጠቋሚ መረጃዎችን የሚያስገኙ ጥናቶች መኖራቸውን ጠቅሰው በኤጀንሲው የሚካሄዱ የቆጠራ ጥናቶች የአጠቃላይ ልማት ግቦች መለኪያ መረጃዎችን የሚያመነጩ እንጂ የዘላቂ ልማት ግቦች መለኪያ መረጃዎችን ብቻ የሚያስገኙ አለመሆናቸውን አብራርተዋል፡፡
የዘላቂ ልማት ግቦች እንደ ሀገር የሚተገበሩ በመሆናቸው የግልና የሲቪክ ማህበራት ሴክተሮችን ለብቻ በመለየት የሚተገበሩ አለመሆናቸውንና ሌሎች ማሻሻያ ተግባራት ካሉ ወደፊት ከሚመለከታቸው ጋር በመወያየት የሚከናወን መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊዎቹ መረጃዎች በተደራጀ የመረጃ ቋት መቀመጥ የሚገባቸው በመሆኑ የመረጃ ቋት በማደራጀት በተሟላና ተደራሽ በሆነ መልኩም ባይሆን መረጃዎች በመረጃ ቋት እንዲቀመጡ መደረጉንና የግብ አመላካቾችን በመረጃ ቋት የማስቀመጥ ተግባር የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ተግባር መሆኑን አመላክተዋል፡፡ አክለውም በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመነጩ መረጃዎችን ጭምር በመረጃ ቋቱ የማስቀመጥ ስራ መሰራቱን አንስተው ከኦዲቱ በኋላ የተለያዩ መረጃዎች መካተታቸውንና የመረጃ ቋት የማሻሻያ ስራዎች ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር ጋር በመሆን የተጀመሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እስከአሁን ያለው የተቋሙ ስራ መረጃን መሰብሰብ፣ መተንተንና ለተጠቃሚ ማቅረብ መሆኑንና የመረጃ ሬጉላቶሪ ስልጣንና ኃላፊነት የፕላንና ልማት ሚኒስቴርን የሚመለከት መሆኑን በማብራሪያው ያመላከቱት የተቋሙ ኃላፊዎች በመረጃ አቀራረብ፣ አደረጃጀትና አጠቃቀም ሂደት ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚረዳ አዋጅ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው አዋጁ የተቋሙን የማስፈጸም አቅም የበለጠ እንደሚያጠናክርና በተለይም አሁን ያሉትንና ለአሠራር ያልተመቹ የህግ ማዕቀፍ ችግሮችን እንደሚፈታ ገልጸዋል፡፡
በሚፈለገው ደረጃ ባይሆንም በመረጃ ሥርዓቱ ላይ የስልጠናና የአቅም ግንባታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊዎቹ ወደፊትም ስልጠናውን ለማጠናከር እቅድ መያዙን፣ በመመሪያ አተገባበር ላይ ያሉት ችግሮች እንዳሉና የመረጃ ሥርዓቱን የሚመለከቱ መመሪያዎች መዘጋጀታቸውን፣ መረጃ ሳይቆራረጥ ለተጠቃሚ ለማቅረብ እንዲያስችልም የስታትስቲክስ የስነ-ምግባር ደንብ፣ የስታትስቲክስ ካሌንደር እና የስታትስቲክስ ጥራት ቁጥጥር መስፈርት የማዘጋጀት ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው የእነዚህ አሠራሮች መተግበርና የአገልግሎቱ የማሻሻያ አዋጅ መጽደቅ በመረጃ አቅርቦት መቆራረጥ ላይ ያለውን ችግር ይፈታል ብለዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ተሳታፊ የሆኑ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች እንዲሁም የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለጥያቄዎቹ በተሰጡ ምላሾች ላይ አስተያየቶቻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ተቋሙ የሀገሪቱን ዘላቂ የልማት ግቦች ሊያሳኩ የሚችሉ ጠቃሚ መረጃዎችን በማመንጨትና ለህዝብ በማቅረብ ረገድ ያለው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የጠቀሱት ተሳታፊዎቹ ቁመናውንና አሠራሩን በዚህ ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ልክ ማድረግ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ ቀደም ሲል የኦዲት ግኝቶቹን መሰረት ያደረገ የድርጊት መርሀ ግብር በወቅቱ ተዘጋጅቶ መቅረብና ችግሮችን ለመፍታት ተግባራዊ ተጨባጭ እንቅስቃሴ መደረግ የነበረበት መሆኑን ጠቅሰው የኦዲት ግኝቶቹንና የተሰጡ አስተያየቶችን እንደ ጠቃሚ ግብአት በመውሰድና የእቅድ አካል በማድረግ በመረጃ አሰባሰብ፣ አደረጃጀትና አተናተን እንዲሁም አቀራረብና ቅብብሎሽ፣ በመረጃ ቋት አደረጃጀት፣ በአቅም ግንባታና ሁለገብ ቴክኒካዊ ድጋፍ ትግበራ፣ በመረጃ አቀራረብ ዘዴ፣ በመረጃ ጥራት ቁጥጥር ስራ እና የመረጃ ሥርዓት አተገባበር መመሪያን በማዘጋጀትና በመተግበር ሂደት ያሉትን ክፍተቶች በመቅረፍ ሀገሪቱ ላስቀመጠቻቸው የዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት ተቋሙ የድርሻውን ሚና በቁርጠኝነት ማበርከትና የተጣለበትን ኃላፊነት መወጣት ይገባዋል ብለዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የልማትና ማህበራዊ አገልግሎት ክዋኔ ኦዲት ዳይሬክተር አቶ ጳውሎስ ዘሪሁን በበኩላቸው ኦዲቱ ሀገሪቱ ያስቀመጠቻቸውን የዘላቂ ልማት ግቦች በመተግበር ረገድ የመረጃ አሰባሰብ፣ አደረጃጀት፣ አቅርቦትና ጥራት በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ሥርዓቱም በአግባቡ መዘርጋቱን በመፈተሽ ላይ ያተኮረ መሆኑን ጠቅሰው የመረጃ ሥርዓቱ የግቦቹን ዒላማዎችና አመላካቾች በሚለይ ደረጃ መቀመጡን ማረጋገጥ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በሰጡት አስተያየት ተቋሙ ሀገሪቱ ያስቀመጠቻቸውን ዘላቂ የልማት ግቦች ለማሳካት መሰረት የሆኑ ዘርፈ ብዙ መረጃዎችን አቅራቢ እንደመሆኑ ያለበትን ትልቅ ኃላፊነት በመወጣት ሀገሪቱ የ2030 ዓለም አቀፍ የልማት ግቦችን ለማሳካት በምታደርገው ጥረት ውስጥ የሚጠበቅበትን ተቋማዊ ተግባር በትኩረት ሊያከናውን ይገባዋል ብለዋል፡፡ አክለውም በኦዲቱ የታዩት የመረጃ ስርዓቱ ከሀገር አቀፍ የልማት እቅድና ስትራቴጂ ጋር ያለውን ተዛምዶ ያለማሳየት፣ የብሔራዊ ስታትስቲክስ አባል መ/ቤቶች አስተዳደራዊ መረጃዎች አያያዝ በሚገባው ልክና ወጥነት ባለው መልኩ አለመሆኑ፣ በግሉ ዘርፍ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚውሉ መረጃዎች በአግባቡ የማይተገበሩና የመረጃ መሰብሰቢያ ቅጾችም ሁሉንም አመላካቾች ያልያዙ መሆናቸው እና በተቋማት መካከል ያለው የመረጃ ትስስርና ቅብብሎሽ ሥርዓት በአግባቡ ያልተገነባ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ እና ሌሎች ክፍተቶችን በማረም በህግ የተሰጠ ስልጣንና ኃላፊነትን በአግባቡ መወጣት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ የመረጃ ስራ ለአገልግሎቱ መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ዋና ኦዲተሯ በኦዲት ግኝቶቹ መሰረት የተሰጡ የማሻሻያ ሀሳቦችን ሊለካ በሚችል የድርጊት መርሀ ግብር በማዘጋጀትና በእቅድ በማካተት የተሻለ የመረጃ ሥርዓት መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ የዘላቂ ልማት ግቦችን መሰረት ያደረገና ወጥ የሆነ የመረጃ ሥርዓት መፍጠር ከአገልግሎቱ የሚጠበቅ መሆኑን ጠቅሰው ጠንካራና ያልተቆራረጠ የመረጃ ሥርዓት አተገባበር ክትትልና ግምገማ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ በበኩላቸው የኦዲት ግኝቶቹን እንደመልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ አሠራርን ማዘመንና ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመው ከመረጃ ውጪ ስራን መስራት ስለማይቻል አገልግሎቱ የሚያመርታቸው መረጃዎች የሀገሪቱን የልማት እቅዶች የሚያሳኩና ቁመናዋንም ለመለካት የሚያስችል በመሆኑ በመረጃ አደረጃጀትና ጥራት ረገድ ትኩረት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ለተቋሙ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው የገለጹት ሰብሳቢው ሚኒሰቴር መ/ቤቱና አገልግሎቱ በኦዲት አስተያቶቹ ላይ በጋራ በመምከር በአጭር ጊዜ ውስጥ የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅተው ለቋሚ ኮሚቴውና ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እንዲልኩ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላትም በሚመለከታቸው ጉዳዮች ዙሪያ የተቋሙን የኦዲት ግኝቶች የሚመለከቱ እርምጃዎችን በመውሰድ ሪፖርት እንዲያቀርቡ አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡