የኦዲት ባለድርሻ አካላት የትብብር ፎረም የ2014 በጀት አመት የስራ እቅዱን ታህሳስ 18/2014 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው የጋራ የውውይት መድረክ ላይ አጸደቀ፡፡
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስተባባሪነት በሚካሄደው በዚህ የኦዲት ባለድርሻ አካላት የትብብር ፎረም እቅድ የውይይት መድረክ ላይ የፎረሙ ባለድርሻ አካል የሆኑ የተለያዩ የፌዴራል ተቋማት በበጀት አመቱ በኦዲት ግኝት ዙርያ ለማከናወን ያቀዷቸው ተግባራት ቀርበዋል፡፡
የፎረሙ እቅድ ዋና ግብ የፌዴራል መ/ቤቶች በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ምክረ ሀሳብና አስተያየት መሰረት በኦዲት ግኝት ላይ ተገቢውን የማስተካከያ የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ የሚያስችል ስራ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት የማስተካከያ እርምጃ ባልተወሰደባቸው ሁሉም ተቋማት ላይ ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል፡፡
የባለድርሻ አካላቱ እቅድ በቀረበበት ወቅት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበጀት አመቱ በተመረጡ 10 የፌዴራል መንግስት መ/ቤቶች የሂሳብና ህጋዊነት ኦዲት ሪፖርቶችና በ16 የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቶች ላይ ይፋ የህዝብ ውይይት ለማካሄድ እንዲሁም በከተማና በገጠር በሚገኙ 12 የፌዴራል መንግስት መ/ቤቶች ላይ የመስክ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ማቀዱ ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይ በመድረኩ ላይ የፎረሙ ባለድርሻ አካል የሆኑት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የፍትህ ሚኒስቴር፣ የትምህርት ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ስነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን፣ የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን፣ የመንግስት ግዥ አገልግሎት እና የጉምሩክ ኮሚሽን ከኦዲት ግኝት ጋር በተያያዘ በበጀት አመቱ ሊያከናውኗቸው ያቀዷቸው ተግባራት ቀርበዋል፡፡
በቀረቡት እቅዶች ላይ በመድረኩ ተሳታፊዎች የተለያዩ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን አስተያየቶቹን በማካተት የመጨረሻ ዕቅድ እንደሚዘጋጅ ታሳቢ በማድረግ እቅዱ ጸድቋል፡፡
በመድረኩ ላይ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስቲያን ታደለ ህዳር 29/2014 ዓ.ም በፎረሙ እቅድ ላይ ውይይት በማድረግ ለማጽደቅ ታቅዶ እንደነበረና በወቅቱ በተካሄደው መድረክ ላይ የፎረሙ አባል የሆኑ የመንግስት ተቋማት የበላይ የስራ ኃላፊዎች በሚፈለገው መጠን ባለመገኘታቸው ምክንያት ለሌላ ጊዜ እንዲዛወር መደረጉን አስታውሰዋል፡፡
ከዚሁ ጋር አያይዘውም ለሁለተኛ ጊዜ በተጠራው በዚህ መድረክ ላይም እንዲሳተፉ ጥሪ ከተደረገላቸው የፎረሙ አባል ተቋማት የበላይ የስራ ኃላፊዎች መካከል ቋሚ ኮሚቴውን ሳያሳውቁ ያልተገኙ እንዳሉ ጠቅሰው ጥሪ ሲደረግላቸው የማይገኙ የመንግስት መ/ቤቶች የበላይ ኃላፊዎች ላይ በምክር ቤቱ የአሰራርና የአባላት ስነምግባር ደንብ መሰረት እርምጃ እንዲወሰድ ለማድረግ ቋሚ ኮሚቴው የሚገደድ መሆኑን በአጽንኦት አስገንዝበዋል፡፡