በኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በማዕድን ሚኒስቴር በከበሩ እና በከፊል የከበሩ ማዕድናት ፈቃድ አስተዳደር ግብይትና ቁጥጥርን በተመለከተ በ2005 በጀት ዓመት የኦዲት ግኝቶች ሪፖርት ላይ ይፋዊ ስብሰባ /Public Hearing/ ጥር 18፣ 2008 ዓ.ም አካሄዷል፡፡
በኦዲት ግኝት ሪፖርቱ ላይ እንደተመለከተው ሚኒስቴር መ/ቤቱ ለወጡ አዋጆች ደንብና መመሪያዎችን በወቅቱ ባለማዘጋጀቱ በሚኒስቴር መ/ቤቱና በክልል ማዕድን ቢሮዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት መካከል ከፍተኛ ክፍተት እንደፈጠረ እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 678/2002 ሚኒስቴር መ/ቤቱ የሚያማክር የማዕድን ሥራዎች መ/ቤት መቋቋም ሲገባው ሳይቋቋም እንደቀረ ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል የከበሩና በከፊል የከበሩ ማዕድናት ባለፈቃዶች የሚያካሂዳቸው የማዕድን ሥራዎች የአከባቢ ጥበቃን ያላገናዘቡና ለማህበረሰብ አከባቢ ልማት አሉታዊ አስተዋፅኦ የሚያደርጉ እንደሆኑ እና የከበሩ ማዕድናት የአዘዋዋሪነት የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት የተሰጣቸው ግለሰቦች የሚያዘዋውሩት ጥሬ የከበሩ ማዕድናት የተገኙበትን ህጋዊ ምንጭ የማይገልፁ መሆናቸው አስረድተዋል፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ የከበሩ ማዕድናት አዘዋዋሪ ባለፈቃዶች በእያንዳንዱ በጀት ዓመት በስምምነት የሚወሰነውን ወርቅና ብር ማዕድናት መጠን ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቅረብ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም ይህ እንደማይሆንና ከ2004 -2006 ዓ.ም በመደበኛነት ክትትልና ቁጥጥር አለመደረጉን፤ በክልሎች ወጥ የሆነ የሮያልት ቁጥጥር እንደሌለና ይህንንም ተከትሎ የህገወጥ ወርቅ ግብይትና ዝውውር መጨመሩን፣ ወደባንክ የሚገባው ወርቅ በከፍተኛ ሁኔታ መጠኑ መቀነሱ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
የሮያልት ክፍያን በተመለከተ በ2005 ዓ.ም የኦሮሚያ ክልል፣ የጉጂ ዞን፣ የአማራ ክልል ማግኘት ይገባቸው የነበረ ከፍተኛ የሮያልት ክፍያ የገንዘብ መጠን ባለመከፈሉ ማጣታቸውን ተነግሯል፡፡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከአምራቾችና አዘዋዋሪዎች ጋር በቂ የውይይት መድረኮች እንዳልተፈጠሩና በኦዲት ሪፖርቱ ከታዩት 10 ባለድርሻ አካላት ውስጥ ከ8ቱ ጋር በቅንጅት እንደማይሰራ ታይቷል፡፡
እንደዚሁም ከክልሎችና ባንኮች ጋር የከበረና በከፊል የከበሩ ማዕድናት ሽያጭ ዙሪያ የሪፖርት አቀራረብ ሥርዓትን በተመለከተ የመግቢያ ሰነድ፣ የባለ ፍቃዶች ወቅታዊ የሪፖርት ማቅረቢያ ጊዜ፣ የፍቃድ ዕድሳት ጊዜ፣ የክፍያ መፈፀሚያ ጊዜ፣ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ አያያዝና ልውውጥ ሥርዓት የሌለ መሆኑ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡
በቋሚ ኮሚቴው የቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ ከሚኒስቴር መ/ቤቱ የተገኙ የተቋሙ አመራሮች ተቀናጅተው ምላሽ መስጠት እንዳልቻሉ ተስተውሏል፡፡
ሌሎች የሚኒስቴር መ/ቤቱ አመራሮች በሰጡት ምላሽ ከፍቃድ አሰጣጥና አዘዋዋሪነት ጋር በተያያዘ የተፈጠሩ ችግሮች ክልሎች በራሳቸው መመሪያ የሚተዳደሩ በመሆኑ የተፈጠሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በሚኒስቴር መ/ቤቱ በታዩ ችግሮች ላይ ጠንከር ያሉ ሃሳቦችን ሰንዝሯል፡፡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከክልል ቢሮዎች ጋር ተቀናጅቶ መስራት ላይ ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዳለ፤ አዋጅ ከፀደቀ 6 ዓመት ቢያልፍም አሁንም ደንብና መመሪያዎችን ተግባራዊ አለመደረጋቸውን፤ የአከባቢ ደህንነትን ከመጠበቅ አኳያም ይህ ነው የሚባል ሥራ እንዳልተሰራና ተጠያቂነትን በሙሉ ወደ ክልሎች ላይ ማዞሩ ተቀባይነት እንደማይኖረው ገልጿል፡፡
በተለይም ቋሚ ኮሚቴው የፌዋኦ ተግባርና ኃላፊነት ጠንቅቆ ሊረዳና ተቋሙ በሚያዘጋጀው የክዋኔ ኦዲት መርሃ ግብር መሠረት አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ ይጠበቅበት እንደነበረ ተግልጿል፡፡ በተጨማሪም ሚኒስቴር መ/ቤቱ በተሠጠው የኦዲት ሪፖርት አስተያየት መሠረት እራሱን በመፈተሽ የድርጊት መርሃ ግብር በማዘጋጀት እንደሚኖርበትና የሚወስዱንትም የእርምት ማስተካካያዎች በአስቸኳይ ለዋና ኦዲተር መ/ቤት ማሳወቅ እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ ሚኒስቴር ዲኤታ ዶ/ር ዋቅጋሪ ፉሪ እንደተናገሩት የኦዲት ሪፖርቱን ያለምንም ማቅማማት እንደሚቀበሉ ለቋሚ ኮሚቴው ገልፀዋል፡፡ ሪፖርቱንም እንደገና ቁጭ ብለው በማየት ትክክለኛ ግኝት የሆኑትን በመለየት አፋጣኝ የእርምት እርምጃ እንደሚወስዱ አስረድተዋል፡፡
ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶም ሲገልፁ ዋናው ችግር ለሪፖርቱ ትኩረት አለመሠጠቱና ከዋና ኦዲተር መ/ቤት በኩል በተደጋጋሚ ለተደረገ ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ካለመስጠት የመጣ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኦዲት መ/ቤትን በተለየ ሥጋት ከመመልከት ወጥተው የኦዲት ሪፖርቱ ያመላከታቸው ችግሮች ላይ ትኩረት በመስጠት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አምባሳድር መስፍን ቸርነት እንደገለፁት በዋና ኦዲትር መ/ቤት የተሰጡትን አስተያያቶች እንዳለ ተቀብለው ተቋሙ ለኪራይ ሰብሳቢነትና ለመልካም አስተዳደር ችግር ተጋለጭ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶ በወጡ ሕጎችና መመሪያዎች ላይ መሠረት ተደርጎ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
ማዕድን ሚኒስቴር በ2ኛው የዕድገና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመንም ሊጫወት የሚጠበቅበትን ሚና እውን ማድረግ ይቻል ዘንድ በቅንጅት ከሚመለከተው አካል ጋር ሁሉ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡