ቋሚ ኮሚቴው የሦስት መ/ቤቶችን የክዋኔ ኦዲት ግኝት ላይ ይፋዊ ስብሰባ አካሄደ
በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሰብል እና የእንስሳት የምርምር ሥርዓት፣ የእርሻ እና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር በሰብል ልማት ኤክስቴሽን እንዲሁም የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር ልማት ኤጄንሲ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና የውጪ ንግድ አፈፃፀም ብቃትና ውጤታማነት የክዋኔ ኦዲት ግኝቶች ሪፖርት ላይ ይፋዊ ስብሰባ /Public Hearing/ ሚያዚያ 14፣ 2008 ዓ.ም አካሄደ፡፡
ቋሚ ኮሚቴውን የመሩት በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አምባሳድር መስፍን ቸርነት ሲሆኑ ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቱት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፋንታሁን መንግስቱ፣ ከእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ ወንድራድ ማንደፍሮና ከሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲ ዋና ዳሬክተር አቶ ኤሣዬ ደቻሳ እንዲሁም ሌሎች የየመ/ቤቶቹ ከፍተኛ አመራሮች፣ የቋሚ ኮሚቴው አባላት፣ የባለድርሻ አካላት ተወካዮች እና የዋና ኦዲተር መ/ቤት የሚመለከታቸው የስራ ክፍል ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትን በተመለከተ በቀረበው የኦዲት ሪፖርት ላይ እንደተመለከተው ተቋሙ ከአከባቢ ስነ-ምህዳር ጋር የሚጣጣሙ የቅባት እህሎችን፣ የሰብል ምርቶችንና የእንስሳት ዘርፍ በአግባቡ ተግባራዊ አለማድረጉን፤ ከተለያዩ የምርምር ሥራ ከሚሰሩ አካላት ጋር የቅንጅት አሰራር ዝቅተኛ መሆኑን፣ የእንስሳት ሃብት ቴክኖሎጂዎችን ማሰደግ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ የመስራት ክፍተት መኖሩን፤ በእንስሳት ዙሪያ የግብይት ሥርዓት ተግባራዊ አለመደረጋቸውን፤ የተለያዩ በኢንስቲትዩቱ የተዘጋጁ ማንዋሎች ለአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጥቅም ላይ ሊውል በሚችል ሁኔታ በተለያዩ ቋንቋዋች አለመተርጎማቸውን፤ ጥቅም ላይ የሚውሉ የተባይ መከላከያ ኬሚካሎች አያያዝና አወጋገድ ጋር በተያያዘ ችግሮች መኖራቸውን፤ ከግብርና ምርምር ጋር የተያያዙ ስልጠናዎች፣ የግብርና ቴክኖሎጂዎች እና የምርምር ውጤቶች መስጠት ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን እንዲሁም የተለያዩ ፕሮጀክቶች፣ ግንባታዎች፣ የምርምር ተግባራት በታቀደላቸው በጀት ዓመት አለመከናወንና የግዢና የንብረት አስተዳደር ላይ ክፍተቶች መታየታቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር በተመለከተ በቀረበው ሪፖርት ለመረዳት እንደተቻለው ከሥነ-ምህዳር ጋር ተስማሚ የሆነ ቴክኖሎጂ እና አሠራር መተግበር ላይ ችግሮች መታየታቸውን፤ ሴቶች ከወንዶች እኩል የኤክስቴንሽን ተጠቃሚ አለመሆናቸውን፤ በወረዳዎች የሚገቡ ግብዓቶችና ቴክኖሎጂዎች ከፍላጎትና አቅርቦት ጋር የተናበቡ አለመሆናቸውን፤ አርሶ አደሩን ለማሰልጠን የሚያስችሉ በቂ ባለሙያ፣ ቁሳቁስ እና ለሰርቶ ማሳያ የሚሆን በቂ መሬት የሌላቸው መሆኑን፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች፣ ግብዓቶችና አሠራሮች ውጤታማነታቸውን በማረጋግጥ ግብረ-መልስ አለመሰብሰቡን እና ሚኒስቴር መ/ቤቱ ቋሚ የመረጃ መሰብሰቢያና የሪፖርት ልውውጥ ማድረጊያ አሠራር ያልዘረጋ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የሆርቴካልቸር ልማት ኤጀንሲ በተመለከተ በቀረበው ሪፖረት አጀንሲው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በተመለከተ የኢንቨስትመንት ድጋፍ ማበረታቻ የዘረጋው አሰራር ቀልጣፋና ውጤታማ በሚያደርግ መልኩ አለመዘጋጀቱን፤ ኤጀንሲው በአንደኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን (2003-2007 ዓ.ም) በዘርፉ 23,040.4 ሄክታር መሬት በባለሃብቶች ይለማል ብሎ አቅዶ እስከ 2006 ዓ.ም መጨረሻ 16,756 ሄክታር ብቻ መልማቱን እና የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ምርት እና ምርታማነት ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ለማሳደግ የተዘረጋው የቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ሥርዓት ችግር ያለበት መሆኑ በኦዲት ሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡
በዝርዝር በሦስቱም ተቋማት ላይ የቀረበውን ሪፖርት ተከትሎ የየተቋማቱ የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ እና ከኦዲት ግኝቱ በኋላ የሰሯቸውን ሥራዎች ለቋሚ ኮሚቴው አስረድተዋል፡፡ በማብራሪያቸውም በኦዲት ግኝቱ መሠረት የሰሩዋቸውን ሥራዎች እና አሁንም እየሰሩ የሚገኙባቸውን ሥራዎች አስረድተዋል፡፡
የቋ ኮሚቴ አባል የተከበሩ ዶ/ር አድሃና ኃይለ ሲገልፁ የግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት የኦዲት ግኝቱ ያሳየውን ግኝት እውነት /Fact/ መሆኑን በመግለፅ ለቀጣይ የተሻለ አፈፃፀም እንደግብዓት መውሰድ እንደሚያስፈልግ፣ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር መ/ቤትም በኬሚካል አወጋገድ ያለውን ችግር ለመፍታት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሳይንስ ፋኩሊቲን ቢያማክሩ የተሻለ መፍትሔ ሊያገኙ እንደሚችሉ እና የሆርቲካልቸር ልማት ኤጀንሲም ያለበትን ችግር ለመፍታት እና በዘርፉ የሚጠበቀውን እምቅ አቅም ለመጠቀም ይቻል ዘንድ ቁርጠኛ አመራር እንደሚጠይቅ ገልፀው ተቋሙ ለዚህ ፍላጎት ተስማሚ የሆነ አሠራርና የስነልቦና ዝግጅት እንደሚጠበቅበት ገልፀዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በሰጡት ሃሳብ ተቋማቱ በኦዲት ግኝቱ የተገኘውን መረጃ መሠረት አድርገው የእርምት እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባ ገልጸው በተጨማሪም ከላይ እስከታች ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር በትኩረት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳድር መስፍን ቸርነት በመጨረሻ በሰጡት የማጠቃላያ ሃሳብ ተቋማቱ በኦዲት ግኝቶቹ መሠረት የእርምት እርምጃ መውሰድ መጀመራቸውን አድንቀው፣ በቀጣይ በተለይም አገሪቷ በ2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ልታሳካ ካሰበችው ግብ አኳያ ሥራቸውን በመፈተሽ በታዩት የኦዲት ግኝቶች ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባ፤ አዳዲስ ተክኖሎጂዎችና አሠራሮች ከመተግበር ባለፈ አፈፃፀማቸውም ምን ያህል ውጤታማ እንደሆነ በመገምገም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ መጣር እንደሚጠበቅባቸውና ሦስቱም ተቋማት ተመጋጋቢ ዘርፎች በመሆናቸው በቅንጅት ሊሠሩ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡