የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ለኦዲት ግኝት እየሰጠው ያለው ትኩረት አነስተኛ መሆኑ ተገለጸ፡፡
በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ.ም በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የ2013 በጀት ዓመት የሂሳብ ኦዲት ሪፖርት ላይ ይፋዊ ህዝባዊ የውይይት መድረክ አካሂዷል፡፡
በመድረኩ ዩኒቨርስቲው በህግ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ የራሱን የክፍያ መመሪያ በማዘጋጀት የመንግስት ሀብትና ገንዘብ እንዲባክን እና አላስፈላጊ ክፍያዎች እንዲፈፀሙ ማድረጉ ተገልጿል፡፡
ከተመላሽ ሂሳብ ጋር ተያይዞም መሰብሰብ ካለበት ብር እስከአሁን አብዛኛው አለመመለሱን፤ ለረጅም ዓመታት የቆሙ ህንፃዎች የመሰነጣጠቅ እና ለከፋ ብልሽት እየተዳረጉ እንደሚገኙ እንዲሁም ለማስተማሪያነት የተገዙ የላብራቶሪ ቁሳቁሶች አገልግሎት ሳይሰጡ ለብዙ አመታት ተከማችተው እንደሚገኙ በኦዲት ግኝቱ ታይቷል ተብሏል፡፡
በአመራሩ በኩልም ህግና መመሪያ ተከትሎ ከመስራት አኳያ ሰፊ ክፍተቶች መኖራቸው ተገልጾ በአጠቃላይ ዩኒቨርሲቲው ከ2009 እስከ 2012 ድረስ ባሉት የኦዲት ግኝቶች ላይ ይህ ነው የሚባል የእርምት እርምጃ ያልወሰደ መሆኑም በውይይቱ ተነስቷል፡፡
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላት ዲያ በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው ተዘጋጅቶ የነበረው የክፍያ መመሪያ በአሁኑ ሰዓት አገልግሎት ላይ እንዳይውል መደረጉን እና ከተሰብሳቢ ሂሳብ ጋር ተያይዞም እስከአሁን ግማሽ ፐርሰንት ያህል መሰብሰብ እንደተቻለ እና ቀሪውን ደግሞ ለመሰብሰብ በሂደት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
አያይዘውም በበጀት እጥረት የተነሳ ግንባታቸው ተጀምሮ ለረጅም ዓመታት የቆሙ ህንፃዎች እስከአሁን ምንም የመፍትሄ እርምጃ እንዳልተወሰደባቸው አብራርተዋል፡፡
ም/ፕሬዚዳንቱ በውይይት መድረኩ ከባለድርሻ አካላት የተሰጡ አስተያየቶች ገንቢ መሆናቸውን ጠቅሰው ካለፈው ትምህርት በመውሰድ ዩኒቨርሲቲውን ከኦዲት ግኝት የፀዳ ለማድረግ አመራሩ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በዩኒቨርሲቲው በኩል የተሰጡ ምላሾችን ተከትሎ በሰጡት አስተያየት በአጠቃላይ የኦዲት ግኝቶቹን ከመቀበል አንፃር ሰፊ ክፍተት መኖሩን እና ለዚህ ማሳያ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በተከናወኑ በኦዲት ሪፖርቶች ከተገኙ ግኝቶች መካከል እስከአሁን የማስተካከያ እርምጃ የተወሰደው በጥቂቶቹ ላይ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር የኦዲት ስራዎቹን ሲያከናውን ተጨባጭ መረጃዎችን ይዞ እንደሆነ ያብራሩት ም/ዋና ኦዲተሩ ተቋማት የኦዲት ግኝት መነሻ በማድረግ አሰራራቸውን ሊያሻሽሉ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ይሁን እንጂ በየኒቨርሲቲው አሁን እየተሰራ ባለውና ባልተጠናቀቀው የኦዲት ሥራም ጭምር ተመሳሳይ ክፍተቶች እየተስተዋሉ መሆኑ አሁንም አመራሩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ አለመሆኑን የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመው አመራሩ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል፡፡
በመድረኩ የተገኙ የቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች የኦዲት ባለድርሻ አካላት በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው በህግ ሳይፈቀድለት እና ስልጣን ሳይሰጠው የራሱ የክፍያ መመሪያ በማዘጋጀት የህዝብና የመንግስት ሀብት እንዲባክን ባደረጉ አመራሮች ላይ ህጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃዎች ሊወስድ እንደሚገባውና ገንዘቡም ተመላሽ እንዲደረግ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው ውስብስብ ችግሮች እንዳሉበት እንደሚረዱ ገልጸው ለኦዲት ግኝቱ የተሰጠው ትኩረት አናሳ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የኦዲት ግኝቶቹ ላይ የሰጠው ማብራሪያ ለግኝቶቹ አስፈላጊ የእርምት እርምጃ አለመውሰዱን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡
አክለውም በዩኒቨርስቲው የአመራር ክፍተት እንዳለ እና ይህም ትምህርት ሚኒስቴር እና የዩኒቨርስቲው የቦርድ አመራሮች ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል እያደረጉ እንዳልሆነ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው የተሰጡትን አስተያየቶች መሰረት በማድረግ በግኝቶች ላይ የማሻሻያ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችል የተከለሰ የድርጊት መርሀ ግብር በማዘጋጀት ማስተካከያ እንዲያደረግ እና በየወቅቱ የሚወሰዱ የማስተካከያ እርምጃዎችንም በየሶስት ወሩ ለሚመለከታቸው አካላት ሪፖርት እንዲያቀርብ አሳስበዋል፡፡
ባለድርሻ አካላትም ተገቢውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ፤ በአግባቡ ኃላፊነታውን ያልተወጡ አመራርና ሠራተኞች በወንጀል እና በፍትሀብሔር እንዲጠየቁ እንዲያደርጉ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አሳስበው ዩኒቨርሲቲው በህግ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ በራሱ አዘጋጅቶ እየተጠቀመበት ያለውን የውስጥ ክፍያ መመሪያ እንዲያቆም እና ተመላሽ ሂሳቦችን ተከታትሎ እንዲያስመልስ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
ለተጨማሪ ማብራሪያ የሚከተለውን የቪዴዮ ሊንክ ይጫኑ!