News

የ ACCA የትምህርት ሂደት በተመለከተ ውይይት ተካሄደ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የ ACCA- Association of Chartered Certified Accountants- (በዓለም አቀፍ ደረጃ በቻርተር የተመሰከረላቸው የሂሳብ ባለሙያዎች ማህበር) ለመ/ቤቱ ኦዲተሮች የሚሰጠውን የትምህርት ሂደት በተመለከተ ከማህበሩ የኢትዮጵያ ተወካይ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አደረገ፡፡

ጥቅምት 22 ቀን 215 ዓ.ም በመ/ቤቱ በተካሄደው ውይይት ላይ የመ/ቤቱ የዋና ኦዲተር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አወቀ ጤናው፣ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ሽመልስ እና ትምህርቱን እየወሰዱ የሚገኙ የመ/ቤቱ ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡

ውይይቱ የትምህርቱን ሂደት በሚመለከቱ መሠረታዊ ነጥቦች ላይ ያተኮረ ሲሆን የተማሪዎችን ተጨማሪ የድጋፍ ክፍለ ጊዜ (Tutorial) እና ትውውቅ (Induction) አሰጣጥ፣ የትምህርት መጻህፍት ማግኛ ዘዴዎች፣ መ/ቤቱ ተማሪዎች ያሉበትን የትምህርት ሁኔታና ደረጃ ሊከታተልበት ስለሚችልበት መንገድ እና በተለይም ወኪል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት እና የክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ተማሪዎች ከአዲስ አበባ ውጪ ፈተና ሊፈተኑ ስለሚችሉበት ሁኔታ የሀሳብ ልውውጥ ተደርጓል፡፡

የማህበሩ የኢትዮጵያ ተወካይ ኃላፊዎች በተነሱት ነጥቦች ዙሪያ ባደረጉት ገለጻ መ/ቤቱ `ACCA Exchange` በተባለ የተማሪዎችን የትምህርት ሁኔታና ደረጃ ለመከታተል የሚያስችል መተግበሪያ መጠቀም የሚችልበት ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚመቻች፣ በአሁን ሰዓት ትምህርቱን ለመጀመር ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ የመ/ቤቱ አባላት የትውውቅ (Induction) ስልጠና እንደሚሰጥ እና ለተማሪዎቹ የሚያገለግሉ የ “ኦን ላይን” የትምህርት መጻህፍትን መጠቀም እንደሚቻል አብራርተዋል፡፡

በቀጣይ መ/ቤቱ ከ ACCA ኢትዮጵያ ጋር የመግባቢያ ሰነድ እንደሚፈራረም በውይይቱ ላይ የተጠቀሰ ሲሆን የማህበሩ የኢትዮጵያ ተወካይ ኃላፊ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ሠራተኞቹን በ ACCA ትምህርት በመስጠት ትልቁ ደንበኛ መሆኑን በመጠቆም ወደፊትም በትምህርቱ በርካታ ዕድሎችን ማግኘት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

የዋና ኦዲተር ጽ/ቤት ኃላፊው አቶ አወቀ ጤናው በበኩላቸው የማህበሩ የACCA የኢትዮጵያ ተወካይ ኃላፊዎች በትምህርቱ ሂደት ላይ ለመወያየት በመምጣታቸው ምስጋናቸውን አቅርበው ወደፊትም አብሮ የመስራት ከፍተኛ ፍላጎትና ቁርጠኝነት መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ቀደም ካሉት ጊዜያት ጀምሮ ለበርካታ ኦዲተሮቹ የ ACCA ትምህርት ዕድል እያመቻቸ ሲሆን በአሁን ሰዓት 18 የመ/ቤቱ ኦዲተሮች እና 11 የክልል መስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ኦዲተሮች መ/ቤቱ ያመቻቸውን የትምህርት ዕድል በመከታተል ላይ የሚገኙ መሆኑንና 10 የሚሆኑ አዳዲስ ተማሪዎችም ለትምህርቱ ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ከመ/ቤቱ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *