News

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከመንግስት የልማት ድርጅቶች የስራ ኃላፊዎች ጋር በኦዲት ዙርያ ውይይት አካሄደ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከ22 የመንግስት የልማት ድርጅቶች የስራ ኃላፊዎች ጋር ድርጅቶቹ ሒሳባቸውን በወቅቱ ዘግተው ለማስመርመር ባጋጠሟቸው ችግሮችና የመፍትሔ ሃሳቦች ዙሪያ ህዳር 09/2012 ዓ.ም በመ/ቤቱ አዳራሽ የግማሽ ቀን ውይይት አካሄደ፡፡

ውይይቱን የመሩት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ሒሳብ የመመርመር ስልጣንና ኃላፊነት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት መሆኑን አስታውሰው ትኩረቱ በባለበጀት መ/ቤቶች ኦዲት ላይ የነበረ በመሆኑ እስካሁን ድረስ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን በቀጥታ ኦዲት ሲያደርግ እንዳልበረ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ግን የግል የኦዲት ድርጅቶችና የሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን በመንግስት የልማት ድርጅቶች ላይ የሚያከናውኑትን ኦዲት በመውሰድ ዋና ዋና ግኝቶችን ከባለበጀት መ/ቤቶች የኦዲት ግኝቶች ጋር በሪፖርት አካቶ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እያቀረበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በየአመቱ ለምክር ቤት የኦዲት ሪፖርት ሲቀርብ ኦዲት ሳይደረጉ የቀሩ የመንግስት ልማት ድርጅቶችን ዝርዝር ጨምሮ መ/ቤቱ እንደሚያቀርብ ክቡር ዋና ኦዲተሩ ጠቅሰው ኦዲታቸው ወደኋላ የቀረ መ/ቤቶችን በመጥራት ሒሳባችውን በወቅቱ ዘግተው ማቅረብ ባላስቻሏቸው ምክንያቶችና መወሰድ ባለባቸው መፍትሄዎች ዙርያ ለመነጋገር መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በውይይቱ ላይ የተጋበዙ ተቋማት ሒሳባችውን በወቅቱ  ዘግተው ላለማቅረብ የገጠሟቸውን ችግሮች እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል፡፡

የየመ/ቤቶቹ የስራ ኃላፊዎችም ሒሳባቸውን በወቅቱ ዘግተው ለማስመርመር የገጠሟቸውን ችግሮች አቅርበዋል፡፡

የስራ ኃላፊዎቹ ካነሷቸው ዋና ዋና ችግሮች መካከል አስቀድሞ ሲሰሩበት ከነበረው የሒሳብ አሰራር ወደ IFRS (International Financial Reporting Standards) በተደረገው ሽግግር ወቅት የተቋማቸውን ሀብት በገንዘብ የመተመን ስራው (Asset Valuation) ችግር መፍጠሩ፣ የሃብት ትመና ለመስራትም የይዞታ ማረጋገጫ የሌላቸው ንብረቶች መኖራቸው፣ ስራውን የሚሰራው የሰው ሃይል ከስራ መልቀቁና ያለውም የአቅም ውስንነት ያለበት መሆኑ፣ በመላው ሀገሪቱ ያሉ በርካታ ቅርንጫፍ መ/ቤቶችንና ወኪሎችን ሂሳብ በፍጥነት ለማሰባሰብ አለመቻሉ፣ የኦዲት ድርጅቶች ውል ማፍረስና ስራዎችን በወቅቱ ያለመጨረስ ችግር መኖሩ፣ የረጅም አመታት ውዝፍ ሂሳቦች መኖራቸው፣ ከመ/ቤቶች መፍረስና መዋሀድ ጋር ተያይዞ ሂሳብ ለማጠቃለል ችግሮች ማጋጠሙ፣ የኦዲት ስራና የሌሎች ተያያዥ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቅጥር የጨረታ ሂደት መጓተቱ፣ ተጠሪ ተቋማት የየራሳቸውን ሂሳብ ለየብቻ በመዝጋታቸው ሲሳቡን በፍጥነት ለማጠቃለል አለመቻሉ፣ በአንዳንድ መ/ቤቶች ውስጥ ሁለት ዓይነት ሒሳብ የሚያዝበት አሰራር ያለ መሆኑ እንዲሁም ከተቆጣጣሪ መ/ቤቶችና ከሌሎች አካላት በቂ ድጋፍ አለመደረጉ ይገኙበታል፡፡

የስራ ሀላፊዎቹ አያይዘውም ያለፉት አመታት ሂሳቦች ኦዲት በአሁኑ ወቅት በምን ደረጃ ላይ እንዳለ አስረድተዋል፡፡

የሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን የስራ ሀላፊዎችም በተነሱ አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከየተቋማቱ ለተገለጹት ችግሮች ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ መፍትሔዎችን በማስቀመጥ ማጠቃለያ ሰጥተዋል፡፡

በዚህም ክቡር ዋና ኦዲተሩ ለመ/ቤቶች ሒሳብ አለመዘጋትና ለምርመራ ዝግጁ አለመደረግ IFRSን እንደ ምክንያት ማቅረብ ተገቢ ባለመሆኑ ለስራው ትኩረት በመስጠት በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ በአንድ  መ/ቤት ሁለት ሒሳብ የሚይዙትን  በተመለከተም እነዚህ መ/ቤቶች በአብዛኛው የሚጠቀሙት የመንግስት በጀትን በመሆኑ ሒሳባቸውን በመንግስት ሒሳብ አያያዝ መሰረት ወደ አንድ አምጥተው መያዝ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ በውላቸው መሰረት የኦዲት ስራውን የማይጨርሱ የኦዲት ተቋማትም ውላቸውን እንዲያከብሩ ግፊት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ በስብሰባው ከተነሱ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ከተቆጣጣሪ መ/ቤቶች፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከሂሳብ አያያዝና ኦዲት ቦርድና ከሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽን ጋር በመነጋገር የሚፈቱ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቅሰው ከእነዚህ መ/ቤቶች ጋር በመመካከር ችግሮች እንዲፈቱ እገዛ እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም ክቡር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶቹ ማግኘት የሚፈልጓቸውን ድጋፎች በዝርዝር ለዋና ኦዲተር መ/ቤት በአስቸኳይ ለይተው እንዲያሳውቁ፣ እስካሁን ያልተጠናቀቁ ሒሳቦችን ዘግቶ ለምርመራ ለማዘጋጀት የድርጊት መርሃ ግብር ማዘጋጀት በፍጥነት እንዲተገብሩ፣ የየተቋማቱ የውስጥ ኦዲተሮችም የኦዲት ግኝቶች ላይ የተጠናከረ ክትትል በማድረግ ሪፖርት እንዲያቀርቡ እንዲሁም ተቋማቱ በቀጣይ ከፋይናንሺያል ኦዲቱ በተጨማሪ የህጋዊነት ኦዲት እንዲያስደርጉ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *