የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤና ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰን ጨምሮ ሌሎች የመ/ቤቱ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች “የጤና እመርታ” በሚል መሪ ቃል በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ጤና ሚኒስቴር አስተባባሪነት ከሰኔ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በሳይንስ ሙዚየም እየታየ ያለውን አውደ ርዕይ ሐምሌ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ጎበኙ፡፡
አውደ ርዕዩ በርካታ ተቋማትና አካላት እየጎበኙት ሲሆን በዝግጅቱ ላይ የተለያዩ ፎቶግራፎችና ሀገሪቱ አስከአሁን በጤናው ዘርፍ የደረሰችበትንና ወደፊትም ሊሰሩ የታሰቡ ጉዳዮችን የሚያሳዩ የተለያዩ የህክምና መርጃ ቁሳቁስ የቀረቡበት ነው፡፡
አውደ ርዕይው በርካታ ሀገር በቀል እውቀቶች፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የህክምና ቴክኖሎጂ የዕድገት ሂደት እና የወደፊቱን የጤና አቅጣጫ የሚያመላክቱ የተለያዩ ዝግጅቶችን ያካተተ ሲሆን ከጉብኝቱ በኋላ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ስለ አውደ ርዕይው ያላቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በሚኒስቴር መ/ቤቱ ተዘጋጅቶ በቀረበው አውደ ርዕይና ባዩት ሁኔታ የተደሰቱ መሆናቸውን የገለጹት ከብርት ዋና ኦዲተሯ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ከታዳጊ ህጻናት ጀምሮ መልካምና ጤንነቱ የተጠበቀ ዜጋን ለማፍራት በባህላዊውም ሆነ በዘመናዊው የጤና ዘርፍ በርካታ ይበል የሚያሰኙ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በጉብኝታቸው ለመረዳት መቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተለይም ለህብረተሰቡ መሠረታዊ ጉዳዮች በሆኑት በቅድመ መከላከል እና በጤና ኬላ ግንባታና መስፋፋት ዙሪያ ስኬታማ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ከአውደ ርዕዩ መገንዘባቸውን ጨምረው የገለጹት ክብርት ወ/ሮ መሠረት በመላው ሀገሪቱ ካለው የጤና ሽፋን ፍላጎትና ተደራሽነት አንጻር ሚኒስቴር መ/ቤቱ ቀጣይ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡