News

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የሚያደርገውን የአቅም ግንባታ ድጋፍ አጠናክሮ ቀጥሏል

የፌዴራል ዋና ኦዲተር /ፌዋኦ/ መ/ቤት ለሐረሪ ክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ኦዲተሮች እና የሥራ ኃላፊዎች በፋይናሺያል የኦዲት ማንዋል ላይ ሥልጠና ሰጠ፡፡

ስልጠናው በዋናነት የክልሉ ዋና ኦዲተር መ/ቤት እስከአሁን ይጠቀምበት የነበረውን የRAM (Regularity Audit Manual) ሥርዓት ወደ FAM (Financial audit Manual) የሚቀይረው መሆኑን በፌዋኦ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ቴዎድሮስ ሽመልስ ገልጸዋል፡፡

በስልጠናው የማጠናቀቂያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የሐረሪ ክልል ምክር ቤት የበጀትና ፍይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ኢክራም አብዱራህማን ባስተላለፉት መልዕክት “እንዲህ አይነት ከጊዜው ጋር የሚሄድ ስልጠና መሰጠቱ ለኦዲተሮች የተሻለ አቅም ከመፍጠሩም ባሻገር የህዝብና የመንግስት ገንዘብ እንዲሁም ንብረት አላግባብ እንዳይባክን የጎላ ሚና ይጫወታል” ብለዋል፡፡

አያይዘውም ኦዲተሮች ምንጊዜም ከጊዜው ጋር የሚሄድ አቅም ሊያዳብሩ እና የኦዲት ስነ-ምግባር ተላብሰው ሥራቸውን ሊያከናውኑ እንደሚገባ ያስተወሱት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በቀጣይ ኦዲተሮች ባገኙት እውቀት የበለጠ ውጤታማ ሥራ መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡

የሐረሪ ክልል ዋና ኦዲተር ዶ/ር አብዱላሂ አህመድ በበኩላቸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ለክልሉ ዋና ኦዲተር መ/ቤት ትኩረት በመስጠት የአቅም ግንባታ ድጋፍ በማደረጉ አመስግነው ድጋፍና ትብብሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አሁን ያገኙት ሥልጠናም ክልሉ ሲጠቀምበት የነበረውን ነባር የኦዲት ማንዋል በአዲሱ የኦዲት ማንዋል እንዲያሻሽሉ እንደሚያስችላቸው የገለጹት የክልሉ ዋና ኦዲተር ቀጣይ ሥራቸውንም ዘመናዊና ቀላል እንደሚያደርግላቸው ተናግረዋል፡፡

ሰልጣኝ ኦዲተሮች በበኩላቸው ሥልጠናው የተሰጠበት መንገድ ተግባር ተኮር በመሆኑ ማግኘት የሚገባቸውን እውቀት እንደጨበጡ እና ለመተግበርም እንደማይቸገሩ ገልጸዋል፡፡

አዲሱ የኦዲት ማንዋልም ስራዎቻቸውን በጊዜ፣ በጥራት እና በብቃት እንዲያከናውኑ ከማገዙም በላይ የኦዲት ሂደቱን የሚያቀልላቸውና የበለጠ ውጤታማ የሚያደርጋቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡

ስልጠናው በድሬዳዋ ከተማ ከነሐሴ 26 እስከ ጳጉሜን 02 ቀን 2014 ዓ.ም ለ7 ተከታታይ ቀናት የተሰጠ ሲሆን በስልጠናውም የሐረሪ ክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤት 72 ኦዲተሮች እና የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *