News

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ህግን በማያከብሩ የመንግሥት ተቋማት ላይ ምክር ቤቱ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ጠየቀ

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ የ2008 በጀት ዓመት የመንግሥት መ/ቤቶች የሂሳብና የክዋኔ ኦዲት የተጠቃለለ ሪፖርትን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 22፣ 2009 ዓ.ም  አቀረቡ፡፡ ክቡር ዋና ኦዲተሩ የመንግሥት መመሪያና አሠራርን ተከትለው በማይሰሩ ተቋማት ላይ ምክር ቤቱ ጠንካራ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡

ክቡር አቶ ገመቹ የኦዲት ሪፖርቱን በ35ኛው የምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ ላይ ባቀረቡበት ወቅት በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተከናወኑ የ158 መ/ቤቶች እና በኦዲት ሰርቪስ ኮርፖሬሽን የተከናወኑ 7 መ/ቤቶች የሂሳብ ኦዲት እንዲደረጉ የታቀዱ ሁሉም የፌዴራል ባለበጀት መ/ቤቶች ኦዲት እንደተደረጉና የክዋኔ ኦዲት እቅድ አፈፃፀሙም 100% እንደሆነም ገልፀዋል፡፡ እንደዚሁም የመሰረታዊ አገልግሎት ከለላ ኦዲትን በ238 ወረዳዎች፣ ከተማ መስተዳድሮች፣ በክልልና ዞን ደረጃ በሚገኙ ፈፃሚ ሴክተር ቢሮዎች እንዲሁም ፕሮግራም አቀፍ የሆነውን የማጠቃለያ ኦዲት በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ደረጃ መፈፀም መቻሉን ገልፀዋል፡፡

ክቡር ዋና ኦዲተሩ በፋይናንስ፣ ግዥና ንብረት አስተዳደር እንዲሁም በተልዕኮ አፈጻጸም ረገድ በፌዴራል የመንግስት ተቋማት ላይ የታዩና በኦዲት ግኝትነት የተያዙ ጉዳዮችን በዝርዝር ያቀረቡ ሲሆን  ችግሮቹን ለመፍታት በቀጣይ መውሰድ አለባቸው በሚል የሰጧቸውን  አስተያየቶች ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡ ክቡር ዋና ኦዲተሩ ምክር ቤቱ የመንግሥትን መመሪያ በመጣስ የመንግሥትና የህዝብ ሀብትን በሚያባክኑ አካላት ላይ ምክር ቤቱ ጠንካራ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት በሰጡት አስተያየት ምንም እንኳ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በየዓመቱ የመንግሥት መመሪያን ተከትለው ያልሰሩ እንዲሁም በተደጋጋሚ ተመሳሳይ የኦዲት ግኝት የሚገኝባቸው ተቋማትን የተመለከተ የኦዲት ሪፖርት ለምክር ቤቱ የሚያቀርብና የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎችም በክትትል እና ድጋፍ ስራቸው ችግሮቹን በተጠሪ ተቋማት ላይ የሚያዩበት ሁኔታ ቢኖርም ምክር ቤቱ በነዚህ አካላት ላይ እርምጃ እንዳልወሰደ በመግለጽ ሪፖርቱን መሰረት ያደረገ እርምጃ መውሰድ ከምክር ቤቱ ይጠበቃል ብለዋል፡፡ በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚታየውን ሰፊ ችግር ምክር ቤቱ በልዩ ሁኔታ ሊያየው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በአንጻሩም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተሰጠውን ተልዕኮ በሚገባ እየተወጣ ያለ ተቋም ነው ብለዋል፡፡

ክቡር ዋና ኦዲተሩ ባቀረቡት የፌዴራል መንግሥት ተቋማት የ2008 በጀት አመት የሂሳብና የክዋኔ ኦዲት ሪፖርትና በሪፖርታቸው ውስጥ የተካተተውን የመ/ቤታቸውን አፈፃፀም አስመልክቶ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ የምክር ቤቱ አባላት ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ለፓርላማ የቀረበውን ሪፖርት በድረ ገፃችን http://www.ofag.gov.et/ofag/audit-report/ይመልከቱ፡፡

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *