News

የወሎ ተርሸሪ ኬር የህክምናና የማስተማሪያ ሆስፒታል ፕሮጀክት ያሉበትን የአፈጻጸም ችግሮች አስወግዶ የተነሳበትን ዓላማ እንዲያሳካ ተጠየቀ

ለወሎ ተርሸሪ ኬር የህክምናና የማስተማሪያ ሆስፒታል ግንባታ ፕሮጀክት ከህብረተሰቡ የተሰበሰበው ገንዘብ ለታለመለት አላማ መዋሉን ማረጋገጥን እና የአሰራር ችግሮችን ለይቶ በማውጣት ችግሮቹ የሚወገዱበትን መፍትሔ መጠቆም አላማው ባደረገው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የ2015/2016 ኦዲት አመት የክዋኔ ኦዲት የታዩ ግኝቶች ላይ ህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ የውይይት መድረክ በፕሮጀክቱ የአፈጻጸም ሂደት የታዩ ጉልህ ክፍተቶች ታርመው በጅማሮ የተቀመጡ አላማዎች እንዲሳኩ ማድረግ ይገባል ተባለ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና ሌሎች የኦዲት ባለድርሻ አካላት በጋራ ባካሄዱት መድረክ የሆስፒታሉ የሥራ አመራር ቦርድ የስራ ግምገማ አናሳ መሆኑና የቦርዱ የአገልግሎት ጊዜ ያልተወሰነ መሆኑ፣ ለሆስፒታሉ ግንባታ የሚሆን ገቢ ለማሰባሰብ ለመሸጥ የተዘጋጀ ከብር 9.3 ሚሊዮን በላይ የሚያወጣ ኩፖን ጠፋ በሚልና በሀገር ውስጥ ባንክ ያልገባ እንዲሁም ያልተመለሰ የቶምቦላ ገንዘብን ጨምሮ በጥቅሉ ከብር 17.1 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ ጠፍቷል በሚል ከህግ ውጭ ከእዳ እንዲሰረዝ መደረጉ ተገልጿል፡፡

በተያያዘም የግንባታ ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ህጉ በሚያዘያው መሠረት በሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የበጎ አድራጎት ፈቃድ ሳያሳድስ ለረጅም ጊዜ ሲሰራ መቆየቱና የተለያዩ የንብረትና የህትመት ግዥዎች መፈጸሙ፣ በፕሮጀክቱ ቦርድ የበላይ ጠባቂ አካል አቅጣጫ የተሰጠ ቢሆንም ገንዘብና ንብረቱን ኦዲት በማስደረግ ለወሎ ዩኒቨርሲቲ በወቅቱ ያለማስረከቡ እና ከዩኒቨርሲቲው ጋር የጋራ አማካሪ ቦርድ ያለማቋቋሙ እንዲሁም በመረጃ ስርጭት፣ በቅንጅታዊ አሠራር፣ በንብረት አያያዝና አጠባበቅ እና በሌሎች የፕሮጀክቱ ግንባታ አፈጻጸም ሂደቶች ላይ ጉልህ ክፍተቶች መታየታቸው በመድረኩ ተገልጿል፡፡

በመድረኩ የተነሱ የኦዲት ግኝቶችን ተከትሎ የፕሮጀክቱ እና የወሎ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች የየበኩላቸውን ሰፊ ምላሽና ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የመድረኩ ተሳታፊ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ከህዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ ለመገንባት ትልቅ አላማ ይዞ የተነሳው ፕሮጀክቱ የታቀደለትን አላማ ሳያሳካ እስከአሁን መቆየቱ የህዝብ ጥያቄን ያስነሳ መሆኑን ጠቁመው ለገንዘብም ሆነ ለአሠራር ጥፋቶች ተጠያቂ የሆኑ አካላት ላይ ተጠያቂነት እንዲሰፍንና ገንዘብንና ንብረትን ጨምሮ ፕሮጀክቱን በቦርዱ የበላይ ጠባቂ አካል በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በኩል ለወሎ ዩኒቨርሲቲ በማስተላፍና ፕሮጀክቱን በማጠናቀቅ የህዝብ ጥያቄን መመለስ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠ ከፕሮጀክቱ አመራሮች ከተሰጡ ምላሾች በኋላ በሰጡት አስተያየትም ኦዲቱ ከተደረገና የማሻሻያ አስተያየት ከተሰጠ በኋላ የተሰሩ ስራዎች በግልጽ እንዲብራሩ በመጠየቅ የገንዘብም ሆነ የአሠራር ጥፋት በማድረስ ለፕሮጀክቱ መጓተት ምክንያት የሆኑ አካላት መጠየቅ እንደሚኖርባቸው ገልጸው ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ በነበሩበት ችግሮች ሳቢያ ህልውናውን ካጣና እንቅስቃሴውን እንዲያቆም በቦርዱ የበላይ ጠባቂ አካል አቅጣጫ ከተሰጠ በኋላ ፈቃዱን ሳያሳድስ ገንዘብ ማንቀሳቀሱና ግዥ መፈጸሙ ህጋዊ አይደለም ብለዋል፡፡

የኦዲቱን ሂደት ከመነሻው ጀምሮ በመጥቀስ እንዲሁም የግኝቶቹን ሁኔታ በማብራራትና የኦዲቱን የትኩረት አቅጣጫ በመጥቀስ አስተያየታቸውን የሰጡት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ኦዲቱ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ጥያቄ መሠረት የተካሄደ መሆኑን ገልጸው ግኝቶቹ በኩፖንም ሆነ በቶምቦላ ተሰብስቦ ወደ ባንክ ያልገባ ገንዘብ መኖሩን ጨምሮ ሌሎች ጉልህ ክፍተቶችን ያሳዩ ናቸው ብለዋል፡፡

አክለውም የህዝብ ገንዘብ ህጋዊ ባልሆነ አሠራርና አግባብ ጠፋ በሚል ከእዳ እንዲሰረዝ መደረጉ ትክክለኛ አሠራር ባለመሆኑ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲወሰድ አሳስበው ወደ ባንክ ያልገባው የህዝብ ገንዘብ ወደ ባንክ እንዲመለስ ጠይቀዋል፡፡

ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የፕሮጀክቱ ጽ/ቤት ስራውን እንዲያቆም ከተደረገ በኋላ ለግዥና ለህትመት የተንቀሳቀሱ ሂሳቦች ህጋዊ ያለመሆናቸውን ጨምረው የገለጹት ክብርት ዋና ኦዲተሯ አሁንም የተበላሹ አሠራሮች ተስተካክለው ፕሮጀክቱ በሚቀጥልበት ሁኔታ ላይ የሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሚመለከተውን ሀላፊነት በመወጣት የፕሮጀክቱን ገንዘብና ንብረት ኦዲት በማስደረግ አቅጣጫ ወደተቀመጠለት ወደ ወሎ ዩኒቨርሲቲ የሚተላለፍበትን ሁነታ እንዲያመቻች አሳስበው ዩኒቨርሲቲውም ከሚመለከተው የመንግስት አካል ጋር በመነጋገርና በጀት በማስፈቀድ ፕሮጀክቱን ማስቀጠል ይገባዋል ብለዋል፡፡

የኦዲቱን ሂደትና የግኝቶቹን ሁኔታ በማጠቃለያ አስተያየታቸው ያነሱት የቋሚ ኮሚቴው ም/ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው የፕሮጀክት ጽ/ ቤቱ ስራ እንዲያቆም ከቦርዱ የበላይ ጠባቂ አቅጣጫ ከተቀመጠለት በኋላ የፈቃድ እድሳት ሳያደርግ ለግዥ ገንዘብ ማንቀሳቀስን ጨምሮ ያለስልጣኑ የእዳ ስረዛ ማድረጉና ሌሎች በኦዲቱ የተጠቀሱ ግኝቶችን መፈጸሙ ከህግ ውጪ መሆናቸውን ጠቁመው ወደፊት ፕሮጀክቱ ወደ ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሚተላለፍበትና ሌሎች ቀጣይ ስራዎችን ለመስራት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ቋሚ ኮሚቴው ከዩኒቨርሲቲው እና ከፕሮጀክቱ አመራሮች እንዲሁም ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የጋራ ምክክር ያደርጋል ብለዋል፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *