News

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ እንዳልሆነ ተገለጸ

የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የትምህርት ጥራትንና አግባብነትን ለማረጋገጥ የሚያደርገው ክትትልና ድጋፍ ዝቅተኛና የሀገሪቱ የእድገት ግብና ፍላጎት የሚያሟላ የተማረ ትውልድ ለመፍጠር የማያስችል በመሆኑ ሀላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ እንደሚገባ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ኤጀንሲው በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመጀመሪያ ዲግሪ የትምህርት ጥራት ላይ የሚያደርገውን ክትትልና ግምገማ በተመለከተ ከ2004-2006 ዓ.ም  በተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ላይ ይፋዊ ስብሰባ ጥር 22 ቀን 2009 ዓ.ም አድርጓል፡፡

በስብሰባው ወቅት ቋሚ ኮሚቴው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በኤጀንሲው ላይ ያከናወነውን የክዋኔ ኦዲት ግኝት መሰረት በማድረግ የትምህርት ጥራትንና አግባብነትን ከማረጋገጥ አኳያ ኤጀንሲው ድክመት ያሳየባቸውን ተግባራት በመዘርዘር የተቋሙ የስራ ኃላፊዎች ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቋል፡፡improved_DSC0019

ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው ከተፈለጉት ጉዳዮች ውስጥ ኤጀንሲው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ያከናወነውን ኦዲት ተከትሎ የማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ አለመላኩ፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጧቸው ትምህርቶችና ስልጠናዎች ከሀገሪቱ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ፍላጎት እንዲሁም ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ጋር የተገናዘቡ ስለመሆናቸውና ለሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት የሚፈለጉ ብቁ ተመራቂ ተማሪዎችን ማፍራት ስለመቻላቸው ማረጋገጥ ሲገባው ተቋማቱ እነዚህን ሀላፊነቶች እንዲወጡ የሚያስገድድበት ህጋዊ መነሻ የለውም በሚል ሰበብ ሀላፊነቱን አለመወጣቱ፣ በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቀረጹት የትምህርት ፕሮግራሞች ተግባራዊ መደረጋቸውን አለማረጋገጡ፣ ካሪኩለሙ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የተግባርና የንድፈ ሀሳብ ትምህርቶች መጠናቀቃቸውን የሚያረጋግጥበት ስርዓት የሌለው መሆኑ እንዲሁም ተመራቂዎች ተፈላጊውን ዕውቀትና ክህሎት ይዘው መመረቃቸውን የማያረጋግጥበት የሙያ ብቃት ምዘና ስርዐት ያልዘረጋ መሆኑ ይገኙባቸዋል፡፡

በተጨማሪም ኤጀንሲው በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ለተማሪዎች ጥቅም የሚውሉ የትምህርት፣ የጤና፣ የማደሪያ፣ የመመገቢያ ቁሳቁሶች፣ ግብአቶችና አገልግሎቶች እንዲሁም ለመምህራን የሚውሉ አገልግሎቶች በሚፈለገው ሁኔታ የተሟሉ፣ የተመጣጠኑ፣ ጥራታቸውን የጠበቁና ለደህንነት ስጋት የማይፈጥሩ ሆነው መገኘታቸውንና አገልግሎት መስጠታቸውን መከታተል አለመቻሉ፣ አዳዲስ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሲገነቡም ሆነ ነባሮቹ ሲስፋፉ ግንባታዎች አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ታሳቢ ስለማድረጋቸው የማይከታተል መሆኑ፣ ተማሪዎች መምህራኖቻቸውን በመሚመዝኑበት አሰራር ውስጥ መምህራኑ የሚያቀርቡት ቅሬታ በአፋጣኝና በጥንቃቄ መፍትሄ የሚያገኝበት ስርአት መፈጠሩን የሚያረጋግጥበት የአሰራር ስርዐት የሌለው መሆኑ እንዲሁም የግልም ሆነ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የተመለከተ መረጃ ያልያዘና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ወቅቱን የጠበቀና ቀልጣፋ የመረጃ ልውውጥ ስርአት ያልዘረጋ መሆኑ ተጠቅሰው ማብራሪያ ተጠይቆባቸዋል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተስፋዬ ሙልዬ ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡ ሲሆን በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተደረገው የክዋኔ ኦዲት በኤጀንሲው እይታ ውስጥ ያልነበሩ ጉዳዮችንና ሊተገበሩ የሚችሉ ጉዳዮችን ያመላከት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ኤጀንሲው የማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር ቢያዘጋጅም አለመላኩ ስህተት መሆኑን፣ ኦዲቱን መሰረት አድርጎ ዋና ዋና ግኝቶችን ከፋፍሎ እርምጃ እንዲወሰድ ለሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች ስራዎችን መሰጠቱን ነገር ግን ስራዎቹ አሁን ኤጀንሲው ባለው አደረጃጀት ሊፈጸሙ የማይችሉ በመሆኑ የአሰራር ስርአት በመዘርጋት ላይ ማተኮሩን፣ ከአደረጃጀት ጥበትና ከመዋቅር ጋር በተያያዘ ያለውን ችግር ለመፍታት ጥናትና ምርምር በማካሄድ ግኝትን መሰረት አድርጎ ስትራቴጂ የሚቀርጽና ስርአት የሚነድፍ አደረጃጀት ባለመኖሩ የተፈጠረውን ትልቅ ክፍተት ለመሙላት በመሰረታዊ የስራ ሂደት ለውጥ የጥናትና ምርምር ስታንዳርዳይዜሽንና አለም አቀፍ ተሞክሮ ዳይሬክቶሬት እንዲቋቋም እንዲሁም የትምህርት ተቋማቱን እንቅስቃሴዎችን ለመከታተልና ለመደገፍም የተቋማት ኢንስፔክሽን የክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እንዲቋቋሙ መደረጉን፣ ከዚህ ውጪ ግን በኦዲቱ የተገኙትን እያንዳንዱን ችግሮች በየዩኒቨርስቲዎቹ እየተከታተሉ እንዲፈቱ ለማድረግ ቀርቶ በፕሮግራም የተያዙ ኦዲቶችን እንኳ በአግባቡ ለማከናወን ኤጀንሲው አቅም እንደሌለው አስረድተዋል፡፡improved_DSC0012

ሌሎች የኤጀንሲው ኃላፊዎችም ኦጀንሲው እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ባደረገው የትምህርት ጥራት ኦዲት መሰረት ማስተካከያ እንዲደረግ ከመንገር ባለፈ ተፈጻሚ እንዲያደርጉ የሚያስገድድበት አሰራር እንዳልነበረ ገልጸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን የኦዲት ግኝት መሰረት አድርገው ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የኦዲት ሪፖርታቸውን ለትምህርት ሚኒስቴር እና ለከፍተኛ ትምህርት ቋሚ ኮሚቴ በመላክ ተጠያቂነት እንዲኖር ጥረት መጀመሩን እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ የማስተካከያ መርሀ ግብር አዘጋጅተው ከላኩ በሁዋላ ተግባራቱ በተጨባጭ መተግበራቸውን መከታተል እንደተጀመረ አስረድተዋል፡፡

በተጨማሪም ኤጀንሲው የመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የጥራት ማረጋገጥ ስራቸውን በራሳቸው እንዲያካሂዱና እንዲገመግሙ የሚያደርግ የውስጥ ቁጥጥር ስርአት እንዲዘረጉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን፣ የትምህርት ተቋማቱ የጥራት ማሻሻያ መርሀ ግብር እንዲያዘጋጁ እየተደረገና ባንዳንዶቹ ተቋማትም ላይ መሻሻሎች እየታዩ መሆኑን እንዲሁም በአንዳንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በኦዲቱ ከታየው ችግርም በላይ ሰፊ ችግሮች እንዳሉና ለዚህም በየተቋማቱ የአቅም ችግር አንደኛው መንስኤ እንደሆነ፣ በመንግስት ዩኒቨርቲዎች የሚታየው የጥራት ችግርም ባንድ በኩል ተቋማቱ ለትምህርት ጥራት የተቀመጡ አስፈላጊ ሁኔታዎችን ሳያሟሉና ከኤጀንሲው አስተያየትና ማረጋገጫ ሳያገኙ በሚኒስቴሮች ምክር ቤት ደንብ እንዲቋቋሙ በመደረጉ ምክንያት የተፈጠረ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ የትምህርት ተቋማት ሲገነቡና ወደ ስራ ሲገቡ በኤጀንሲውና በትምህርት ሚኒስቴር መሀከል ቅንጅት አለመኖሩን፣ ኤጀንሲው የትምህርት ጥራትና አግባብነትን የማረጋገጥ ስራውንም ሆነ የእውቅና አሰጣጡን በአግባቡ እንዲወጣ የሚያስችል በቂ ሰው ሀይል የሌለው መሆኑን፣ የርቀት ትምህርት መርሀ ግብር የሚሰጡትን የመንግስት የትምህርት ተቋማትን በሙሉ ባለው አቅም በልዩ ሁኔታ ኤጀንሲው እየገመገመና ፈቃድ እየሰጠ እንደሆነ ሆኖም ግን መደበኛ መርሀ ግብር ላይ ያሉትን በመገምገም እውቅና በመስጠት ላይ ግን በአቅም ውስንነት ምክንያት እንዳልሄደበት እንዲሁም ኤጀንሲው ራሱን ለሚመለከታቸው አካላት በቅርበት እንዳላስተዋወቀና መግባባት ላይ እንዳልደረሰ የስራ ኃላፊዎቹ አስረድተዋል፡፡  

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በመስሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በሰጡት አስተያየት ኤጀንሲው የኦዲት ግኝቱን እንደጠቃሚ ግብአት ወስዶ ለመታረም ያሳየው ዝግጁነትና ከችግሮቹ ለመውጣት ስርዐት ለመፍጠር እያደረገ ያለው ጥረትን በመልካም ጎን ጠቅሰው ነገር ግን የትምህረት ጥራት ማረጋገጥ ስራ መብቃት (empowerment) የሚጠይቅ በመሆኑ ኤጀንሲው በዚህ አግባብ መንቀሳቀስ እንዳለበት፣ የጥራት መለኪያ መነሻ (benchmark) በማዘጋጀት ላይ መስራት እንደሚጠበቅበት፣ ጥራትን በወቅቱ ማረጋገጥ እንደሚያሻው፣ ከሀገሪቱና ከገበያው ፍላጎት ጋር የተጣጣመ የተማረ የሰው ሀይል ለማፍራት በግልም ሆነ በመንግስት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚቀረጹ የትምህርት ፕሮግራሞች አግባብነት ላይ አትኩሮ መስራት እንደሚገባው፣ የጥራት ቁጥጥሩን ለግልም ሆነ ለመንግስት ተቋማት ወጥና ፍትሀዊ ማድረግ እንደሚኖርበት፣ የማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ አለመላክ ተጠያቂነትን የሚያስከትል በመሆኑ መርሀ ግብሩን አዘጋጅቶ ለመላክና ለመተግበር ትኩረት መስጠት እንደሚያሻው እንዲሁም የትምህርት ጥራትና አግባብነትን የማረጋገጥ ሀላፊነት የትምህርት ፖሊሲውን የማሳካት ጉዳይ በመሆኑ ለዚህ ትልቅ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አያይዘውም የመንግስት የትምህርት ተቋማት ችግራቸውን እየፈተሹ የትምህርት ጥራታቸውን በራሳቸው እንዲያረጋግጡ የማብቃት ስራው እንዳለ ሆኖ የኤጀንሲው ክትትልና ድጋፍ መጠናከር እንደሚገባው፣ በግል የትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለውን የትምህርት ጥራት ችግርና ብልሹ አሰራር ለመፍታት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚኖርበት፣ ለትምህርት ጥራት የግብአት መሟላት ወሳኝ በመሆኑ ቢያንስ መሰረታዊ ግብአቶችንና አገልግሎቶችን በፍጥነት ለሟሟላት ትኩረት መስጠት እንደሚገባው፤ አሁን የተጀመሩት ስርዐት የመገንባት፣ የህግ ማዕቀፎችን የመፈተሽ፣ አደረጃጀትና መዋቅርን የማስተካከልና ከባለድርሻ አካላት ጋር ጥብቅ ቅንጅታዊ አሰራር የመፍጠር ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚኖርበት፣ ኤጀንሲው ኃላፊነቱ በቁጥጥር ሚና ላይ የተገደበ ብቻ ሳይሆን በትምህርት ቁጥጥር ዘርፉ ላይ የአመራርነት ሚና መጫወት ጭምር እንዲሆን መስራት እንዳለበት አስተያየት ሰጥተው ኤጀንሲው አሁን ባለበት ቁመና የትምህርት ጥራትንና አግባብነትን በማረጋገጥ ሀገሪቱ ለኢኮኖሚያዊና ለማህበራዊ እድገቷ የምትፈልገውን ብቁ የሰው ሀይል ለማምረት የትምህርት ጥራትና አግባብነትን የማረጋገጥ ሚናውን በአግባቡ እየተወጣ ባለመሆኑ ችግሮቹን አርሞ ጠንክሮ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው ከአምስት አመት በፊት በግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት ላይ ኦዲት ተደርጎ በርካታ ችግሮች እንደተገኙ በማስታወስ ይህንን ሪፖርት በመመልከት ለቀጣይ ስራ ኤጀንሲው በግብአትነት እንዲጠቀምበት ጠቁመው የኦዲት ግኝቱን መሰረት አድርጎ ኤጀንሲው ስለሰራው የክትትል ስራ ሪፖርት እንዲልክ ለቀረበለት ጥያቄ ግን ምላሽ እንዳልሰጠ ገልጸዋል፡፡

improved_DSC0025ክቡር አቶ ገመቹ የከፍተኛ ትምህርት አዋጁ በመንግስት የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ኤጀንሲው እርምጃ እንዲወስድ የማያስችለው እንደሆነ ኤጀንሲው ካመነ ባለፉት ስምንት አመታት እንዲስተካከል ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ሆኖ መስራት እንደነበረበት፣ አሁንም ኤጀንሲው ከኦዲት ሪፖርቱ በኋላ የድርጊት መርሀ ግብር አዘጋጅቶ እየሰራ ባለመሆኑ ጉዳዩ በትኩረት ሊታይ እንደሚገባው፣ ባለፉት ሰባት አመታት ኤጀንሲው በግልና በመንግስት የትምህርት ተቋማት ላይ 54 የጥራት ኦዲቶችን ብቻ ማድረጉ የኦዲት ሽፋኑ በጣም ትንሽ መሆኑን እንደሚያሳይ፣ እርምጃ አወሳሰዱም በናሙና በታዩት ዩኒቨርስቲዎች ሲታይ የኤጀንሲው ኃላፊዎች በገለጹት ልክ እንዳልሆነ፣ ኤጀንሲው የሚያካሂደውን የጥራት ኦዲት መሰረት አድርጎ እርምጃ በመውሰድ ረገድ የራሱን ሚና በሚገባ አለመወጣቱን፣ ዩኒቨርስቲዎች የሚከፍቷቸው ፕሮግራሞችና ትምህርት ክፍሎች እንዲሁም የሚያስመርቋቸው ተማሪዎች ገበያውንና የሀገሪቱን ፖሊሲ በሚመጥን አግባብ መሆኑን የማገናዘብ ስራ በሚገባ እየተሰራ ባለመሆኑ በድጋሚ ሊጤን እንደሚገባው ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በማጠቃለያ ሀሳባቸው ተቋሙ ከችግሮቹ ለመውጣት የጀመረውን ጥረት በጥሩ ጎኑ ገልጸው ነገር ግን ኦዲቱን ተከትሎ የድርጊት መርሀ ግብር መላክ እንደነበረበትና ይህም ኤጀንሲው ለጀመረው የእርምት ስራ አጋዥ ግብአቶችን ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት እንዳያገኝ እንዳደረገውና መርሀ ግብሩን ለሚመለከታቸው አካላት መላክ የመልካም አስተዳደር ማረጋገጥ ጉዳይ ተደርጎ መወሰድ እንደነበረበት ገልጸዋል፡፡

improved_DSC0031

የተከበሩ አምባሳደር መስፍን ኤጀንሲው አዲስ በሚገነቡ ዩኒቨርስቲዎችም ሆነ በነባር የትምህርት ተቋማት የሚከናወን የማስፋፊያ ግንባታ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ፍላጎትና መብት ትኩረት መሰጠቱን ማረጋገጥ እንደሚገባው፣ ለዩኒቨርስቲዎች የትምህርት ጥራት መሟላት አስፈላጊ ግብአቶች በጎንዮሽ ዘዴዎችም ሆነ በተራዘመ አግባብ መሟላታቸውን የመቆጣጠር ስልጣን አለኝ ብሎ ስልጣኑን በቅንጅትም ሆነ በተናጥል መጠቀም እንደሚጠበቅበት፣ ተቋሙ ስለተልእኮና ስለሀላፊነቱ ራሱን ለህብረተሰቡም ሆነ ለሌሎች ባለድርሻ አካላት ማስተዋወቅና በዚህም የሚገኙ ግብዐቶችን መጠቀም እንደሚያሻው፣ የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ረገድ የሚያጋጥሙ ከኤጀንሲው አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮችን ለመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ሆነ ለከፍተኛ ትምህርት ቋሚ ኮሚቴ በማሳወቅ ተጠያቂነት እንዲመጣ መስራት እንደሚገባው፣ በተቋሙ ውስጥ ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር የተቋሙን አቅም የሚጎዳና ተልዕኮውን እንዳይወጣ የሚያደርግ ዋነኛ ችግር በመሆኑ በአመለካከትና በአቅም የተሟላ ፈጻሚ ለመፍጠር በመ/ቤቱ የሰው ሀይል ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባው እንዲሁም ከባለድርሻ አካላትና ከህዝብ ክንፉ ጋር ያለውን ትስስርና ተሳትፎን ማሳደግ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

One thought on “የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ እንዳልሆነ ተገለጸ

  1. Ewukna yelelachew yetmrt zerflay yalen yekeftegna tmrt temariwoch eyetegodan engegnale lemsala physics laboratory technology yalu ytmrt endat ytayalu?

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *