የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ በፋይናንስ አሠራር፣ በንብረት አስተዳደርና አያያዝ ሥርዓት ላይ ያሉበትን ጉድለቶች በአስቸኳይ ማረም እንዳለበት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ፡፡ ታህሳስ 5 ቀን 2013 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ያካሄደው ይፋዊ ህዝባዊ ስብሰባ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በ2011 በጀት ዓመት በኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ ያከናወነውን የፋይናንሻል ኦዲት መሠረት ያደረገ ነው፡፡
በኦዲት ግኝት ሪፖርቱ መሠረት በዩኒቨርስቲው የታዩ የፋይናንስ አሠራር እንዲሁም የንብረት አስተዳደርና አያያዝ ጉድለቶች ስፋት ያላቸው መሆኑን በጥልቀት የገመገመው ቋሚ ኮሚቴው በዩኒቨርስቲው አመራሮች ምላሽ እንዲሰጥባቸው ቁልፍና መሠረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡
በኦዲቱ ወቅት በመዝገብ ላይ የተገኘ ብር 323,248.32 በካዝና ባለመቆጠሩ ምክንያት ትክክለኛ መሆኑን ማረጋገጥ ያለመቻሉ፣ የሂሳብ መዝገብና የባንክ ስቴትመንትን የማስታረቅ ስራ ባለመሰራቱ ባንክ ላይ የሌለ ገንዘብ አለ ተብሎ ሪፖርት መደረጉ፣ የገቢ ሂሳብ በትክክል መዝግቦ ለገንዘብ ሚኒስቴር የተጠቃለለ ሪፖርት ባለመደረጉ ምክንያት የሒሳቡን ትክክለኛነት ማረጋገጥ አለመቻሉ፣ የተፈቀደ በጀት ሳይኖር ከተለያየ ገቢ የተሰበሰበ ብር 3,351,676.16 በበጀት ሳይደገፍ ወጪ መደረጉ፣ የተለያዩ ግብይቶች ሲፈፀሙ ከግለሰቦችና ድርጅቶች ተቀንሶ ገቢ መደረግ የነበረበት ብር 46,927.64 ተጨማሪ እሴት ታክስ ሳይቀነስ መቅረቱና በውሉ መሰረት ላልተፈፀሙ ስራዎች ከአቅራቢዎች መሰብሰብ የነበረበት ብር 205,639.67 የጉዳት ካሳ ሳይሰበሰብ መቅረቱ፣ ብር 698,490.86 ባልተስተካከለ የሂሳብ መደብ ተመዝግቦ መገኘቱ፣ ደንብና መመሪያን ያልተከተሉ የብር 490,383.00 የትርፍ ሰዓት እና የብር 1,552,258.39 የውሎ አበል ክፍያዎች መፈፀማቸው እና በዋጋ ማወዳደሪያ (ፕሪፎርማ) በመጠቀም ተመሳሳይ ማህበራትን ብቻ በተደጋጋሚ በመጋበዝ የብር 1,383,161.97 የመኪና ኪራይ አገልግሎት ግዥ መፈፀሙ እንዲሁም የብር 1,207,801.46 የተለያዩ ግዥዎች ያለምንም ውድድር መፈፀማቸው ቋሚ ኮሚቴው ባነሳቸው ጥያቄዎች ውስጥ የተካተቱ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው በተሰብሳቢ ሂሳቦች አተገባበር ላይ ያሳያቸውን ጉድለቶች በሚመለከት ተጨማሪ ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን በ2011 በጀት ዓመት መጨረሻ ከሚታይ ተሰብሳቢ ሂሳብ ውስጥ ብር 1,427,191.80 ያልተወራረደ ሂሳብ መገኘቱና ከዚሁ ተሰብሳቢ ሂሳብ ውስጥ ከማን እንደሚሰበሰብ የማይታወቅ ብር 692,760.51 መገኘቱ፣ በ2011 በጀት ዓመት መጨረሻ በድምሩ ብር 5,492,214.24 ያልተወራረደ ተከፋይ ሂሳብ መገኘቱና የዚህንም የቆይታ ጊዜ ማወቅ ያለመቻሉ እንዲሁም ብር 484,394.58 ለማን እንደሚከፈል የማይታወቅ ተከፋይ ሂሳብ መገኘቱን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው በቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ ቀርቧል፡፡
የዩኒቨርስቲውን የንብረት አስተዳደርና አያያዝ ሥርዓት በተመለከተም በኦዲት ግኝቱ የታዩ ክፍተቶችን መሠረት ያደረጉ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ ንብረቶች በአይነታቸው ተለይተው ያልተቀመጡ መሆኑና የቢን ካርድ አሠራር ሙሉ ለሙሉ ያለመተግበሩ እንዲሁም ሁሉም ንብረቶች መለያ ቁጥር ያልተሰጣቸው መሆኑ፣ የ2011 በጀት ዓመት የንብረት ቆጠራ ያልተካሄደ መሆኑ፣ ከተገዙ በኋላ ከ3 ዓመታት በላይ አገልግሎት ሳይሰጡ የተቀመጡ ንብረቶች መኖራቸው፣ ቢጠገኑ መልሰው አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ንብረቶች አገልግሎት መስጠት ከማይችሉት ጋር ሳይለዩ ተቀላቅለው መቀመጣቸው እና ንብረቶች ከመጋዘን ውጪ ለስርቆት በተጋለጠ መልኩ ተቀምጠው መገኘታው ለምን እንደሆነ የዩኒቨርስቲው አመራሮች ማብራሪያ እንዲሰጡ ተጠይቋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ሙክታር መሀመድ በሰጡት ምላሽ የቀረቡት ጥያቄዎች ተገቢና የተጠቆሙት ጉድለቶችም በኦዲቱ ወቅት የታዩና ከኦዲቱ ወዲህ ጉድለቶቹን ለማስተካከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመላክተው የክፍተቶቹ መንስኤዎች ያሏቸውን አብራርተዋል፡፡ በተለይም በፋይናንስ አሠራር ላይ የታዩት ክፍተቶች በዋናነት ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲል በቴክኒክና ሙያ ተቋም በኋላም በኮሌጅ ደረጃ በተለያዩ ተቋማት ስር ሲተዳደር ቆይቶ ከነበሩት የቀድሞ አሠራሮቹና የሰው ሀይል ጋር ወደ ዩኒቨርሲቲ ያደገ በመሆኑ የተፈጠሩ ከመሆናቸውም ባሻገር የነበሩት የፋይናንስ ባለሙያዎች ወቅቱ ከሚጠይቀው ዘመናዊ የፋይናንስ አሠራርና ቴክኖሎጂ ጋር ለማዋሀድ ክፍተት መኖሩና በቂና አቅም ያለው የሰው ሀይልም ያልነበረ መሆኑ ለጉድለቶቹ መሰረታዊ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቁመው ይህንን በሰው ሀይል በኩል የተፈጠረ መሠረታዊ ችግር በስልጠናና የመዋቅር ክለሳ በማድረግ ለመቅረፍ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ በንብረት አስተዳደርና አያያዝ በኩል የተፈጠሩ ክፍተቶች በተለይ የንብረት አስተዳደር ሥራው ከሌላ የስራ ክፍል ጋር ተደርቦ የነበረ በመሆኑ በበቂ የሰው ሀይልና አሠራር ለብቻው ስራውን ለመስራት ባለመቻሉና በንብረት አስተዳደርና አያያዝም በኩል በቂ ዕውቀትና ክህሎት ያለው የሰው ሀይል ባለመኖሩ የተፈጠሩ መሆናቸውና በአሁኑ ወቅት የንብረት አስተዳደሩ ራሱን ችሎ በዳይሬክቶሬት ደረጃ በማዋቀር ችግሮቹን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ ይህንንኑ የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት ምላሽ የሚያጠናክሩ ተጨማሪ ሀሳቦችም በሌሎች የዬኒቨርሲቲው አመራሮች ተሰጥተዋል፡፡
በዩኒቨርስቲው አመራሮች የተሰጡት ምላሾች አጥጋቢ ያለመሆናቸውንና ዩኒቨርሲቲው የኦዲት አስተያየት መስጠት የማይቻል (Disclaimer) ውስጥ የሚገኝ በመሆኑና ይህም በርካታ ችግሮች ያሉ መሆኑን ጠቋሚ ስለሆነ በአፋጣኝ የእርምት እርምጃ መውሰድና አሠራሩን ማስተካከል እንደሚገባ ከቋሚ ኮሚቴ አባላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስተየያት ተሰጥቷል፡፡
ክቡር ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ በሰጡት አስተያየት የዩኒቨርቲው የሶስት ተከታታይ ዓመታት የኦዲት ግኝቶች እንደሚያሳዩት ችግሮቹ ተመሳሳይ ባህሪ ያላቸውና ከዓመት ዓመት መሻሻል ያልታየባቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡ በተለይም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ከዩኒቨርሲቲው ምስረታ ጀምሮ የነበሩ ከመሆኑ አንፃር በየዓመቱ በተደጋጋሚ የታዩትን ተመሳሳይ ችግሮች ለማስተካከል ዕድል የነበረ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ኦዲተሩ ሁኔታው ችግሮቹን ለማስተካከል ያለውን የትኩረት ማነስ ያሳያል ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ችግሮችን ለመቅረፍ በሚል ከዚህ በፊት አዘጋጅቶ ለፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የላከው መርሀ ግብር ዝርዝር ሁኔታዎችን የማያሳይና ትክክለኛ ባለመሆኑ እንደገና በዝርዝር ተሰርቶ መላክ እንደሚኖርበትና በተለይም የመንግስትን መመሪያ ባልተከተለ መልኩ በውሎ አበል አከፋፈል እንዲሁም ባልተፈቀደ በጀት ገቢን የመጠቀም አሠራርና ሌሎች ክፍተቶች የጎሉ በመሆናቸው በአስቸኳይ መታረም እንደሚገባቸውና በዚህ ብልሹ አሠራር ተሳታፊ የሆኑ አካላት በህግ መጠየቅ እንሚገባቸውም ክቡር ዋና ኦዲተሩ አሳስበዋል፡፡ በመጨረሻም በዩኒቨርሲቲው የሚታየውን የፋይናንስ አሠራር ክፍተት የገንዘብ ሚኒስቴር ሙያተኞችን ድጋፍ በመጠየቅ በአፋጣኝ ማስተካከል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
የመስሪያ ቤቱ የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው ከኦዲቱ በኋላ ችግሮቹ እየተቀረፉ ስለመሆናቸው ከዩኒቨርሲቲው አመራሮች የተሰጡት ምላሾች ትክክለኛነት በቀጣይ ኦዲት የሚረጋገጥ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በዩኒቨርሲቲው ላይ የታዩ ግኝቶች ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ ያልተሻሻሉና በባህሪም ተመሳሳይነት ያላቸው በመሆናቸው አሁንም ችግሮቹ ስለመቀረፋቸው ማረጋገጥ እንደማይቻል ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ተመሳሳይ ችግሮች በተደጋጋሚ መታየታቸውና በየዓመቱ የሚሰጡ የኦዲት ግኝት አስተያየቶችን ያለመተግበር ችግር ዩኒቨርስቲው በአጥፊዎችና በብልሹ አሠራሮች ላይ እርምጃ ለመውሰድ ያለው ቁርጠኝነት አናሳ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል፡፡ በመሆኑም በፋይናንስ አሠራርም ሆነ በንብረት አስተዳደርና አያያዝ ዙሪያ ለታዩ ስር የሰደዱ ጉድለቶች ትኩረት በመስጠት አፋጣኝ ተግባራዊ የመፍትሔ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ ክብርት ም/ዋና ኦዲተሯ በአፅንኦት አሳስበዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው የፋይናንስ ዘርፍ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ ሶፊያ አልማሙ በበኩላቸው በሪፖረቱ መሰረት ዩኒቨርሲቲው በርካታ የኦዲት ግኝቶች ያሉበት እና የሰው ሀይሉንና ሌሎች አቅሞቹን ችግሮቹን ለመፍታት በአግባቡ ያልተጠቀመ በመሆኑ በቀጣይ በዋና ኦዲተር የሥራ ሀላፊዎች የተሰጡ አስተያየቶችንና ከሌሎች አካላት የሚገኙ ሙያዊ ድጋፎችን በማቀናጀት ችግሮቹን መቅረፍና የተሻሉ አሠራሮችን ማምጣት እንደሚገባ የፋይናንስ ዘርፍ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ አሳስበዋል፡፡
በመጨረሻም የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ መሀመድ ዩሱፍ ባቀረቡት የማጠቃለያ አስተያየት ዩኒቨርስቲው የምርምር ማዕከል እንደመሆኑ ጥናትና ምርምሩን በቅድሚያ ያሉበትን የውስጥ አሠራር ችግሮች ለመፍታት መጠቀም እንደሚገባውና ያለውን ሀብት በአግባቡ በስራ ላይ ማዋል እንደሚኖርበት አመላክተዋል፡፡
የኦዳ ቡልቱም ዩኒቨርስቲ ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ የግብርና እንዲሁም የሙያና ቴክኒክ ተቋም በመሆን ሲያገለግል የነበረና ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ዩኒቨርስቲ ደረጃ ያደገ የትምህርት ተቋም ነው፡፡