የምርመራ ጋዜጠኝነት እንዲጎለብት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የበኩሉን ሚና እንደሚወጣም ክብርት ዋና ኦዲተሯ ተናግረዋል።
“ለፀረ-ሙስና ትግሉ ምርመራ ጋዜጠኛነት” በሚል መሪ ቃል ለሚዲያ አመራሮች፣ ጋዜጠኞችና የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያዎች የምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ ስልጠና ተሰጥቷል።
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የስልጠና ማዕከል አዘጋጅነት የተዘጋጀውን የ2 ቀን የስልጠና መርሃ-ግብር የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በአጋርነት ያዘጋጀ ሲሆን ስለኦዲት ምንነት እና ኦዲት ለፀረ-ሙስና ትግሉ ስለሚጫወተው ሚና የመ/ቤት የኦዲት ጥራት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አህመድኑር ሱሁዋሊ በኩል ገለጻ አቅርቧል።
በመድረኩ የተገኙት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በሰጡት ሀሳብ ሚዲያዎች መንግስትና ህዝብን የሚያገናኙ ድልድዮች መሆናቸውን ጠቁመው ለምርመራ ጋዜጠኝነት የኦዲት ሪፖርቶች ጉልህ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ ብለዋል።
ዋና ኦዲተሯ በንግግራቸው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በየዓመቱ በሁሉም የመንግስት ባለበጀት መ/ቤቶች ላይ የፋይኔሺያል ኦዲት እንደሚያደርግ እና በየዓመቱ 30 የሚደርሱ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርቶችን በመስራት ለህዝብ ይፋ እንደሚያድርግም ጠቁመዋል።
የምርመራ ጋዜጠኞችም እነዚህን የኦዲት ሪፖርቶች መነሻ በማድረግ ቢሰሩ ሙስናን የመዋጋት እና መልካም አስተዳደርን የማስፈን ሥራን የሚያቀሉ መሆናቸውን ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ገልፀው የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የፀረ-ሙስና ትግሉን በምርመራ ጋዜጠኝነትን ለማገዝ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ተናግረዋል።
ለሁለት ቀን በተካሄደው የምርመራ ጋዜጠኝነት የስልጠና እና የውይይት መድረክ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ሃላፊዎች፣ የፌዴራልና የክልል ሬዲዮ፣ ቴሌቪዥንና ህትመት ሚዲያ አመራሮችና አርታኢዎች፣ በአጠቃላይ 150 የሚሆኑ የሚዲያ አካላት እንደተሳተፉ ለማወቅ ተችሏል።