News

የአማራ ክልል ምክር ቤት የስራ ኃላፊዎች ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አሰራር ሰፊ ተሞክሮዎችን ማግኘታቸውን ገለጹ

በአማራ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ የተመራ የልዑክ ቡድን ታህሳስ 8 ቀን 2017 ዓ.ም የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤትን አሠራር የጎበኘ ሲሆን የልዑኩ አባላት በጉብኝቱና በተሞክሮ ልውውጡ ወቅት ከዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ጋር በነበራቸው ቆይታ  ሰፊና ጠቃሚ ተሞክሮዎችን ማግኘታቸውን ገልጸዋል፡፡

የልዑክ ቡድኑ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤና ም/አፈ-ጉባኤ፣ የክልሉ ምክር ቤት የበጀት፣ ፋይናንስና ወጪ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና አባላት እንዲሁም የክልሉ ዋና ኦዲተርን ያካተተ ሲሆን የልዑክ ቡድኑ አባላት ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ዋና ኦዲተር ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ደምጤ ለልዑክ ቡድኑ አባላት ስለ ፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የህግ መሠረቶች፣ ተቋማዊ ነጻነት፣ የኦዲት አሠራር፣ ሪፖርት አቀራረብና እርምጃ አወሳሰድ፣ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ስላለው ግንኙነቶች እንዲሁም አጠቃላይ የአዲት ምንነት፣ አሠራሮችና ጠቀሜታን በሚመለከት የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለፃ አድርገዋል፡፡

የክልሉ አፈጉባኤ የተከበሩ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ እና የልዑክ ቡድኑ አባላት በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የተደረገላቸው ገለጻ ሰፊ ግንዛቤ የፈጠረላቸው እና በክልላቸው መስራት ለሚፈልጉት ለውጥ ሰፊ ተሞክሮ የቀሰሙበት እንደሆነ ጠቁመው ለተደረገላቸው ገለጸና ማብራሪያ አመስግነዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በዚህ ደረጃ ልምድ ለመቅሰም አስበው በመምጣታቸው ያላቸውን አክብሮት ገልጸው በቀጣይም መ/ቤቱ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ክልሉን  በሚችለው ሁሉ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከፌዴራል ዋና ኦዲተር በተጨማሪ በኢ .ፌ.ዴ .ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ስብሳቢ የተከበሩ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር ) የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤትና በተለይም የም/ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ  የኦዲት ሪፖርትን መሰረት ባደረገ መልኩ እያከናወነ ስላለው የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎች ለልዑክ ቡድኑ ተጨማሪ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *