የኦዲት ሥራ ድግግሞሽ፣ የስራ ጫናን አላስፈላጊ የጊዜ ብክነት ለማስወገድ በፓይለት ደረጃ ለአንድ አመት ሲተገበር የቆየው የነጠላ ኦዲት አዋጅ አፈጻጸም ውጤታማ እንደነበረ ተገለጸ።
በመድረኩ የፌዴራል ዋና ኦዲተር /ፌዋኦ/ መ/ቤት ጨምሮ የኦሮሚያ፣ የሲዳማ፣ የደቡብ ልልል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተሮችና ም/ዋና ኦዲተሮች ተሳትፈዋል።
በፌዋኦ መ/ቤት የስልጠና ኢንስትራክተር አቶ ቴዎድሮስ ሽመልስ ስለነጠላ ኦዲት አጠቃላይ ምንነትና ዓላማ፣ በዓመቱ የተሰሩ ሥራዎች፣ ያጋጠሙ ችግሮች እና የተወሰዱ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ዙሪያ ገለጻ አድርገዋል።
በአንድ አመቱ የሙከራ ጊዜ ለአራቱም ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የስራ ኃላፊዎችና ሙያተኞች የነጠላ ኦዲት ላይ ስልጠና መስጠቱን፣ የ2015 በጀት አመት የነጠላ ኦዲት ዕቅድና ሪፖርት የማሰባሰብ እና ክትትል የማድረግ ስራዎች መሰራቱ ተግልጿል።
በመድረኩ የተሳተፉ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተሮች በሰጡት አስተያየት በፓይለት ደረጃ የተጀመረው የነጠላ ኦዲት ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ እንደመደረጉ ጥሩ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸው በቀጣይ ከሎጅስቲክ፣ ከአቅም ግንባታ፣ ከሪፓርት ዝግጅት አንጻር ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እየተፈቱ ሊሄዱ እንደሚገባ አንስተዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው የነጠላ ኦዲት አዋጅ በፓይለት ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን የመጀመሪያውን ቁርጠኝነት ወስደው ተግባራዊ ያደረጉትን 4 ቱን ክልሎች አመስግነው በዚህ አመት የተጀመረው ሥራ በቀጣይ በሁሉም ክልሎች ለመተግበር መስረት የጣለ ነው ብለዋል።
የነጠላ ኦዲት ትግበራ የውጭ ኦዲት ድግግሞሽን ከማስቀረት ባለፈ በክልሎችና በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት መካከል ያለውን ግንኙነት ያጠናከረ፣ በአቅም ግንባታና በኦዲት ጥራት ላይ የሚሰሩ ስራዎች ይበልጥ ያገዘ እንደነበረም ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል።
በሂደቱ ያጋጠሙ ችግሮችን እንደገንዘብ ሚኒስቴር ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሔ ማበጀት ያስፈልጋል ያሉት ክብርት ወ/ሮ መሰረት ዳምጤ ሪፖርት ዝግጅት ያሉ ችግሮችን መቅረፍ፣ ኦዲቱ ባለቤት ኖሮት እንዲመራ ማድረግ እና በየጊዜው ሂደቱን እየገመገሙ አፈጻጸሙ ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ በቀጣይም ተጠናክረው ሊሠሩ የሚገቡ ሥራዎች ናቸው ብለዋል።
የነጠላ ኦዲት አዋጅ በቀጣይ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከክልልና ከከተማ አስተዳደር ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ጋር በሚያደረገው የጋራ ውይይት በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1146/2011 መሰረት መ/ቤቱ ከፌዴራል መንግስት ለክልል መንግስታት የሚሰጠውን ድጋፍና ድጎማ አፈጻጸም ኦዲት የማድረግ ስልጣን ያለው በመሆኑና የክልል መንግስታት ዋና ኦዲተር መ/ቤቶችም ይህንኑ ኦዲት የሚያደርጉበት ሁኔታ የነበረ በመሆኑ በአሠራር ላይ የተፈጠረውን የኦዲት ድግግሞሽ ለማስወገድ ሲባል የነጠላ ኦዲት አዋጅ 1251/2013 እና የአዋጁ ማስፈጸሚያ መመሪያ ቁጥር 2/2014 ወጥቶ 4 ክልሎች በፓይለት ደረጃ ወደ ትግበራ መግባታቸው ይታወቃል፡፡