News

የተፋሰሱ የውሃ ሀብት አጠቃቀምና አስተዳደር የሚገባውን ያህል ውጤታማ ያለመሆኑ ተገለጸ

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የአዋሽ ተፋሰስ ልማት ጽ/ቤትን ከ2008 አስከ 2013 በጀት ዓመታት የነበረውን የተፋሰሱን የውሃ ሀብት አስተዳደርና አፈጻጸም ቀልጣፋነትና ውጤታማነት ለማረጋገጥ ባካሄደው የክዋኔ ኦዲት በታዩ ግኝቶች ላይ ይፋዊ ህዝባዊ ውይይት አካሂዷል፡፡

በተፋሰሱ የጎርፍ ትንበያና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለመተግበር የሚያስችሉ በድምሩ ከብር 36.9 ሚሊዮን በላይ ገንዘብ የወጣባቸው ጥናቶች ያለመተግበራቸው፣ በድምሩ ከብር 7.4 ሚሊዮን በላይ ወጪ ተደርጎበት ከአምስት አመታት በፊት የተዘጋጀው የውሃ መጠቀሚያ የተሻሻለ ታሪፍ ረቂቅ እስከ አሁን ድረስ ጸድቆ በስራ ላይ ያለመዋሉ እና የወንዝ አቅጣጫ አመራር ስራው የሚመራበት የአሰራር ስርዓት ባለመኖሩ ተፋሰሱን ተከትለው በሚገኙ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የመፈናቀል አደጋና የተለያዩ ሰብሎችን ጨምሮ በርካታ የንብረት ወድመት መድረሱን ኦዲቱ እንደሚያሳይ በውይይት መድረኩ ተነስቷል፡፡

በተፋሰሱ ውስጥ ያሉት የመተሀራና የወንጂ ስኳር ፋብሪካዎች ለመስኖ ስራ ለሁለት አመታት የተጠቀሙበትን የውሃ አገልግሎት ክፍያ ያለመክፈላቸውን ጨምሮ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስርዓት ዝርዝር የአፈጻጸም መመሪያ ያለመዘጋጀቱ፣ አሳታፊና የተቀናጀ የውሃ አጠቃቀም ስርዓት ያለመተግበሩ፣ የሀይድሮሎጂ መረጃ አስተዳደር ስርዓት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ያለመታገዙ እና የተፋሰሱን ስራ ውጤታማ ለማድረግ የተዘረጉ ፕሮጀክቶች አፈጻጸምም ዝቅተኛ መሆኑ ከኦዲት ግኝቶቹ መካከል እንደሚጠቀሱ ተገልጿል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩን ዶ..ር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋና ሌሎች አመራሮች የተነሱትን የኦዲት ግኝቶች አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ግኝቶቹ ትክክለኛና በተፋሰሱ ውስጥ ያሉ ችግሮችን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል፡፡

ከኦዲቱ በኋላ ስድስት የተለያዩ የትግበራ ማዕቀፎችን (Packages) መሰረት ያደረገ የተፋሰስ ዕቅድ በማዘጋጀት የተፋሰሱን ስራ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቀሱት አመራሮቹ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ወደፊት የሚስተካከሉ ክፍተቶች መኖራቸውን በመጥቀስም የቋሚ ኮሚቴውንና የሌሎች ባለድርሻ አካላት እገዛን የሚጠይቁ ስራዎች እንዳሉም ገልጸዋል፡፡

የመድረኩ ተሳታፊ የቋሚ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው የተፋሰሱን ስራ ውጤታማ ለማድረግ በቂ ስራ ያለመሰራቱንና በተለይም በፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ከመተግበር፣  በተፋሰሱ አካባቢ በየጊዜው የሚከሰቱ ሰብኣዊና ቁሳዊ አደጋዎችን ቀድሞ ከመከላከል አንጻር እና በውሃ ሀብት አያያዝና አጠቃቀም ረገድ ዝቅተኛ አፈጻጸም መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የሚከናወኑ ቅንጅታዊ ተግባራት የሚጠበቁ ቢሆንም የተፋሰሱ ጽ/ቤትም ሆነ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ግኝቶቹን የቀጣዩ በጀት ዓመት የዕቅድ አካል በማድረግ በእራስ አቅም የሚሰሩትን ስራዎች አከናውኖ ችግሮቹን መቅረፍ ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል በአባይ እና በስምጥ ሸለቆ ተፋሰሶች ላይ ተመሳሳይ ኦዲት መካሄዱን በማስታወስ ከኦዲቶቹ ግኝቶች ትምህርት መወሰድ ይገባ እንደነበር የጠቀሱት የፌዴራል ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሰ በበኩላቸው ችግሮቹን ለመቅረፍ ቅንጅታዊ ስራ ያለመሰራቱንና በሚሰሩ ስራዎች ላይም የፋይናንስና የፊዚካል አፈጻጸም ያለመጣጣም እንደሚታይ ገልጸው የተፋሰስ ስራ በጀት ስላለ ብቻ የሚከናወን ሳይሆን የአካባቢውን ህብረተሰብና ባለድርሻ አካላት ያሳተፈ ጥረት የሚጠይቅ ነው ብለዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በሰጡት አስተያየት ሶስቱንም ተፋሰሶች ያማከለ የአሠራር መመሪያ አዘጋጅቶ ውጤታማ የውሃ ሀብት አጠቃቀም ሥርዓትን መተግበርና ተፋሰሱን ከብክለት ለመከላከል ያልታከሙ ፍሳሾች የሚወገዱበትን ስረዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

አክለውም በአየር ቅድመ ትንበያ፣ በመረጃ አያያዝ እና በጥናት ውጤቶች ትግበራ ዘላቂ ስራዎችን መስራትና የተራቆቱ መሬቶችን እንዲያገግሙ በማድረግም ህብረተሰቡ ከተፋሰሱ ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክርስትያን ታደለ በሰጡት የማጠቃለያ አስተያየትም ለተፋሰሱ ውጤታማነት በተቋም ደረጃም ሆነ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር የሚሰሩ ስራዎችን የማቀናጀቱ ሃላፊነት የሚኒስቴር መ/ቤቱ በመሆኑ በፕሮጀክቶች አፈጻጸም፣ በመረጃ አያያዝ እና በሌሎች ግኝቶች ዙሪያ የሚታዩ ክፍተቶችን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ገልጸው በ15 ቀናት ውስጥ የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት ያደረገ አዲስ የኦዲት ግኝት ማሻሻያ የድርጊት መርሀ ግብር ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ አቅጣጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *