የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ከተለያዩ የክልል ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ለመጡ የኦዲት ስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በበጀት አሠራር ግልጸኝነትና ተጠያቂነት ላይ ግንዛቤ ለመስጠት 2ኛ ዙር የጋራ ምክክር አካሄደ፡፡
ቀደም ሲል በመስከረም ወር 2015 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከሌሎች ሶስት ክልሎች ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች ከመጡ የኦዲት የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ተመሳሳይ መድረክ ያካሄደ ሲሆን በዚህ በ2ኛው ዙር መርሀ ግብር ከአማራ፣ ከአፋር፣ ከጋምቤላ፣ ከሶማሌ እና ከደቡብ ምዕራብ ክልላዊ መንግስታት ዋና ኦዲተር መ/ቤቶች የመጡ 23 ተሳታፊዎች ምክክሩን አካሂደዋል፡፡
ህዳር 1 ቀን 2015 ዓ.ም በመ/ቤቱ የስልጠና ማዕከል የተካሄደውን የአንድ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫና የጋራ ምክክር በቦታው በመገኘት ያስጀመሩትና ስለመድረኩ ዓላማና አካሄድ አጠቃላይ ገለጻ ያደረጉት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት ም/ዋና ኦዲተር ክቡር አቶ አበራ ታደሠ ሲሆኑ መድረኩ የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት የክልሎች ዋና ኦዲተር መ/ቤቶችን አቅም ለመገንባት እያደረገ ያለው ጥረት አካል ነው ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል በመስከረም ወር ከሌሎች ክልሎች ጋር የተካሄደውን ተመሳሳይ 1ኛ ዙር የግንዛቤ ማስጨበጫና የጋራ ምክክር ያስታወሱት ም/ዋና ኦዲተሩ የመድረኩ ዓላማ የበጀት ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን ከክልሎች ጋር በጋራ በመስራት በተለያዩ ክልሎች በወረዳ ደረጃ የሚገኙ ተገቢ ባለሙያዎችን አሳትፎ በአገልግሎት አሠጣጥ ላይ ስታንዳርዱን የጠበቀ የበጀት ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት በዕቅድ የያዘውን ይህንኑ የወረዳዎችን የበጀት ግልጸኝነትና ተጠያቂነት የማረጋገጥ ስራ ሙሉ ለሙሉ ለመሸፈን የማይችል በመሆኑ በመ/ቤቱና በወረዳዎች ደረጃ ሊሸፈኑ የሚችሉትን የመለየት ስራ ቀደም ሲል መሰራቱን ክቡር አቶ አበራ ጠቁመዋል፡፡
ይህን ተከትሎም የበጀት ግልጸኝነትና ተጠያቂነት የማረጋገጡን አጠቃላይ ዕቅድ 90% በሀገሪቱ በሚገኙ ወረዳዎች እና 50% በወረዳዎች በሚገኙ የትምህርትና ጤና ጽ/ቤቶች ላይ ለመተግበር መታሰቡንና ቀደም ብለው በመድረኩ የተሳተፉ ክልሎችም ትግበራውን መጀመራቸውን ም/ዋና ኦዲተሩ አስረድተዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች በቆይታቸው ከጋራ ምክክር ባሻገር በየክልሎቻቸው ተመልሰው የትግበራውን ዕቅድ በሚያዘጋጁበት አካሄድ ላይ አቅጣጫ የተሰጠ ሲሆን ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የገንዘብ ሚኒስቴር የመጡ አንድ ባለሙያና የመ/ቤቱ የድጋፍና ድጎማ ኦዲት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ እምሩ ኦሊቃ የግንዛቤ ማስጨበጫ ገለጻዎች አድርገዋል፡፡
በመድረኩ ማጠቃለያ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ተሳታፊዎች የጋራ ምክክሩ የበጀት ግልጸኝነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን የሚያስችል ጠቃሚ ግንዛቤ ያገኙበት መሆኑን በመጥቀስ በወረዳ ደረጃ የሚገኙ ሌሎች ባለሙያዎችን በማብቃትና በማሳተፍ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን ጥረት እንደሚያደርጉ አመላክተዋል፡፡