News

የመ/ቤቱ የ2016/2017 ኦዲት ዓመት አፈጻጸም እቅዱን ያሳካና ለቀጣይ ለ2017/2018 ኦዲት ዓመት እቅድ አፈጻጸም መሠረት የሚሆኑ ክንውኖች የታዩበት መሆኑ ተገለጸ ::

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መ/ቤት አመራሮችና ሠራተኞች የመ/ቤቱን የ2016/2017 ኦዲት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ለመገምገምና እና የ2017/2018 ኦዲት ዓመት ተቋማዊና የየስራ ክፍሎች እቅዶች ለማዘጋጀት የሚያስችል የጋራ የውይይት መድረክ አካሄዱ፡፡

በቢሾፍቱ የኢትዮጵያ ስራ አመራር ኢንስቲቲዩት ከየካቲት 10-14/2017 ዓ.ም ለአምስት ተከታታይ ቀናት የተካደሄውን መድረክ በንግግር የከፈቱት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ የ2016/2017 ኦዲት ዓመት እቅድ አንኳር የአፈጻጸም ስኬቶችን በአኃዝ አስደግፈው ያቀረቡ ሲሆን በኦዲት ዘርፍም ሆነ በድጋፍ ዘርፍ የተመዘገቡት ውጤታማ የእቅድ አፈጻጸሞች በሁሉም የመ/ቤቱ አመራርና ሠራተኞች ቁርጠኛና ያላሰለሰ የተቀናጀ ጥረት የተገኙ በመሆኑ ይህ ስኬት መ/ቤቱን እንደ ተቋም የሚያኮራ ነው ብለዋል፡፡

ያለፈው ኦዲት አመት ዝርዝር የእቅድ አፈጻጸም ለመድረኩ በዝርዝር ቀርቦ በመድረኩ ተሳታፊ አመራሮችና ሠራተኞች ውይይት የተደረገበትና ጠንካራና ደካማ ጎኖች የተለዩበት ሲሆን በመድረኩ ቆይታ ለቀጣዩ ኦዲት ዓመት እቅድ ትግበራ መሠረት የሆኑ የትኩረት አቅጣጫዎች በበላይ አመራሩ ተሰጥተው በስራ ክፍሎች ደረጃ ያሉትን እቅዶች በመ/ቤቱ ከፍተኛ አመራሮች ያልተቋረጠ ክትትልና ድጋፍ በጋራ የቡድን ውይይት የማዘጋጀት ስራ ተከናውኗል፡፡

ከ2017/2018 ኦዲት ዓመት የእቅድ ዝግጅት  በኋላ የካቲት 14 ቀን 2017 ዓ.ም የተጠናቀቀውንና ሁሉም የመ/ቤቱ ሠራተኞች የተሳተፉበትን መድረክ  በማጠቃለያ ንግግር የዘጉት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ክብርት ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ ባለፈው ኦዲት አመት እቅድ አፈጻጸም የታየው ስኬት በመጪው የመ/ቤቱ የእቅድ ክንውን ላይ እንዲደገምና ተቋሙ በስራ አፈጻጸሙም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ያለውን በጎ ስም ማስቀጠል ይገባል ብለዋል፡፡

በመድረኩ ማጠናቀቂያ ላይ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ የሺመቤት ደምሴን (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች የቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ የመ/ቤቱ አመራሮችና መላው ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡

   

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *